መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የቤተልሔሙ ሕፃን

የትምህርቱ ርዕስ | የቤተልሔሙ ሕፃን

እንኳን ለ2018 ዓ.ም. የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ!

“በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች።” ሉቃ. 2፡1 ።

የጌታችን ሰው መሆን መላእክት ለዘላለም የሚማሩት ትምህርት ነው ። የአማንያን ትልቅ ሳይንስና የዘወትር ዝማሬ ነው ። የጌታችን በትሕትና መወለድ የሚያስደንቅ ነው ። ሰይጣን በዓለመ መላእክት ላይ ሐሰተኛ ክስ ዘርቶ ነበር ። እግዚአብሔርን እንደ ንፉግ አምላክ ስሎት ነበር ። በዚህም ስህተቱ የተሳቡ የወደቁ መላእክት ተባሉ ። የሰው ልጅ የሆነው አዳምም በሰይጣን ምክር እግዚአብሔርን ፍቅር አልባ ፣ ለሥልጣኑ ስሱና ስጋት ያለው አድርጎ ተቀብሎ ነበር ። የጌታችን ሰው መሆን ለመላእክትም ለሰው ዘርም የእግዚአብሔርን ጠባይ የገለጠ ነው ። እግዚአብሔርን ከእግዚአብሔር በቀር የሚገልጠው የለምና ክርስቶስ ሰው ሆነ ። እግዚአብሔርን በዘላለማዊ ብርሃኑ ማንም ሊያየውና ሊቀርበው ስለማይችል ራሱን በሰው መልክ ገለጠ ። በመምሰል ሳይሆን በመሆን መጣ ። በዚህ ለመላእክትም ታየ ። በማመን እንጂ በማየት አያመልኩትም ነበርና ሰው በሆነ ጊዜ አዩት ። “ለመላእክት የታየ” ተብሎ ተጽፎአል (1ጢሞ. 3፡16) ። እርሱ ሰዎች ይቀርቡት ዘንድ በራሳቸው መልክ መጣ ። እንደ ባዕድ ቢቆጥሩት ኖሮ አእምሮአቸውን በትምህርት ፣ ሰንካላነታቸውን በፈውስ ፣ ነፍሳቸውን በቤዛነት አያድንም ነበር ። እግዚአብሔር ታውቆ የሚኖር አምላክ ቢሆንም ታውቆ ግን ሊፈጸም አይቻልም ። ዓለማትን ያለ መያዣ ያንጠለጠለው ፣ ምድርን በውበት ፣ በስጦታ አበባ ያንቆጠቆጠው እርሱ ነው ። አንድ ዘለላ አበባ ለሰጠ በደስታ አመሰግናለሁ የሚለው የሰው ልጅ ይህን ሁሉ ጌጥ በምድር ላይ ለበተነው ጌታ ምስጋና እያቀረበ አይደለም ። እንኳን ስለ መዳናችን ስለ ቆምንባት ምድር ጠንቅቀን አናውቅም ። ሕይወት የሚሰጠውን አየር በነጻ ናኘ ፣ በአየር ላይ ዜማ አለ ። የምንተነፍሰው አየር ውስጥ አስደሳች ድምፆች አሉ ። በመታከሚያ ስፍራዎች አየር የሚስቡት በክፍያ ነው ። ደስ እያለው እንዲስብ በማለት ምንም ዜማ አይጠቀሙም ፣ ጌታችን ግን አየሩን በዜማ ሰጠን ። ከዚህ ሁሉ በላይ ሰው ሆኖ እኛን ማዳኑ ተሰብኮ የማያበቃ ምሥጢር ነው ።

እርሱ ከአብ ዘንድ ባለው ክብር ቢገለጥ መለኮታዊ ብርሃኑን ማየት ሁላችንም አንችልም ነበር ። እናየው ዘንድ ፣ ዳስሰነውም እንድን ዘንድ በሥጋ ማርያም ተገለጠ ። ሞት የመጣው በትዕቢት ነው ። ትዕቢት ውድቀት እንዳላት ከዓለመ መላእክት ወደ እንጦሮጦስ የወደቀው ሰይጣን ይነግረናል ። ትዕቢት ባለን ነገር አለማመስገን ፣ የሌለንን ነገር እንዳለን አድርጎ መኩራራት ነው ። ውጤቱ የሌለንን ላናገኝ ያለንን ማጣት ነው ። ሰይጣን አምላክነትን ሲሻ መልአክነትን አጣ ። አዳም የሌለውን ጌትነት ሲናፍቅ በከበረባት ገነት ተሸማቆ ወጣ ። ትዕቢት ያለ እግዚአብሔር በራስ የመክበር ጥረት ነው ። ሊቀ ካህናት የተጌጠ ልብስ ለብሶ ፣ ወርቀ ዘቦ ተሸልሞ መሥዋዕት ያቀርባል ። ሊቀ ካህናት ከራሱ ውጭ ያለው እንስሳ ላይ ጨክኖ መሥዋዕት ያሳርጋል ። ዕርቃኑን ሁኖ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ ትልቁ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። እርሱ መሥዋዕት የሚሆንበትን ሥጋ ለራሱ አዘጋጀ ። ስለዚህ ልደቱና መስቀሉ ተመጋጋቢ ናቸው ። ሰው በመሆኑም ሰውነትን ቀደሰ ። በእግዚአብሔር ከተማም ሰውነት እንደ ገና ከበረ ።

ጌታችን የተወለደው ዓለም ሁሉ አንዲጻፍ ትእዛዝ በወጣበት ዘመን ነው ። እርሱ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ ተቆጠረ ። ይህም ታሪክ ሳይሆን ለአማንያን ምሥጢር ነው ። በሕይወት መጽሐፍ ላይ ሊቆጥረን በእኛ መጽሐፍ ተቆጠረ ፣ በልቡ የጻፈን በብዕራችን ተጻፈ ። ሮማዊ ቄሣር የሚያውቀው ዜጋን እንደሚቆጥር ነበር ፣ በቆጠረው ውስጥ ግን ዘላለማዊ ንጉሥ ተቆጠረ ። በመስቀል ላይ ከዓመፀኞች እንደ አንዱ የሚቆጠረው ዛሬ ከሰው ልጆች እንደ አንዱ ተቆጠረ ። ሕግንና ሥርዓትን የሠራው እርሱ የነገሥታትን ሕግ አክብሮ ሊቆጠር ሄደ ። ነገሥታት ሳያውቁተ የትንቢት መፈጸሚያ ፣ የአምላክ ሥራ አስፈጻሚ ይሆናሉ ። ለእግዚአብሔር በሦስት መንገድ መታዘዝ አለ ። ስለተፈጠረ የሚታዘዝ ፣ ስለ ተሾመ የሚታዘዝ ፣ ስለ ዳነ የሚታዘዝ ናቸው ። ስለተፈጠረ የሚታዘዝ ለልደትና ለሞት ታዛዥ ይሆናል ። የተሾመ ሁሉ ደስ ብሎት የሚታዘዝ አይደለም ፣ ግድ ሆኖበትም ነው ። ስለተሾሙ ብቻ ለአምላክ የሚታዘዙ አሉ ። በረከት ያለው ትእዛዝ በዳነች ነፍስ እግዚአብሔርን እሺ ማለት ነው ። አውግስጦስ ቄሣር በዚያች የጌታ ልደት ዋዜማ ይህን አስገዳጅ ትእዛዝ ማምጣቱ አረጋዊው ዮሴፍና ድንግል ማርያም ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄዱ ነው ። ምክንያቱም በይሁዳ አውራጃ በቤተ ልሔም በመወለድ ትንቢቱን መፈጸም ነበረበት (ሚክ. 5፡2)።

ክርስቶስም ንጉሥ ነውና ሕዝቡን ይቆጥራል ። ቄሣር ሕዝቡን የቆጠረው ግብር ለማስከፈል ፣ የሚሞትለት ወታደር ለመመልመል ነው ። ክርስቶስ ግን የሚቆጥረን በጸጋ ሊሰጠን ደግሞም ሊሞትልን ነው ። ቄሣር ቆጠራው ጊዜያዊ ነውና በተወሰነ ጊዜ ይደገማል ፣ ክርስቶስ ግን ለዘላለም ይቆጥራል ። የቄሣር ቆጠራ በግዳጅ ነው ፣ ክርስቶስ ግን በፈቃድ ይቆጥራል ። ቄሣር ለቆጠራ እንደሚጠራ በክርስቶስ ዘንድ ቀድሞ የታወቀ ፣ ልቡንም ያነሣሣው ሰማያዊ መሻት ነው ። ትንቢቱን ለመፈጸም ዓለም በሙሉ አገለገለ ። ቃሉ አይወድቅምና ። የዓለም ንጉሥ እውነተኛው ጌታ ነገሥታትን አከበረ፣ እኛም የእርሱን አርአያ መከተል ይገባናል ። ሰዎች የሚያደርጉት በጎ ነገር ፣ አንዳንዴ የነገሥታት አዋጆች የእግዚአብሔርን ዕቅድ ሳያውቁት የሚፈጽሙበት ነው ።

ክርስቶስ በልባችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በታሪካችን ውስጥ ገባ ። ታሪክና የነገሥታት መዝገብ ክርስቶስን ያውቀዋል ። እኛ ግን በጌትነት ክብሩ ፣ በአዳኝነት ፍቅሩ እናውቀዋለን ።

ተመስገን !!!

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ !

#ዲያቆን #አሸናፊ #መኰንን
ታኅሣሥ 28 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ