የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /13

/አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!/
የሐዋርያው ጳውሎስ ሐዋርያዊ ጉዞ
ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ አራት የሚጠጉ ሐዋርያዊ ጉዞዎች እንዳደረገ በመጽሐፍ ቅዱስና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል ። ጉዞው ከ48 ዓ.ም. እስከ 58 ዓ.ም. ውስጥ ባሉት 10 ዓመታት ውስጥ የተፈጸመ ይመስላል። የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞ ከተደረገ በኋላ ወዲያው የ50 ዓ.ም. የኢየሩሳሌም ጉባዔ የመጀመሪያው የሐዋርያት ሲኖዶስ ተካሂዷል ። /የሐዋ. 15/ ። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ለአይሁድ ክርስቲያኖች እንደ መነሻ ነበረች ፤ እንዲሁም የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያንም ለአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት መነሻ ነበረች ። የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ጉዞም አንጾኪያን መነሻና መድረሻ ያደርግ ነበር ። በጉዞው መጨረሻም ሪፖርት ያቀርብ ነበር ። የሐዋርያዊ ጉዞዎቹ ዓላማ፡-

1-  መትከል፡- ዱሩን መንጥሮ የወንጌልን ዘር መዝራት ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን መመሥረት ፤
2-  ማጽናት፡- የተተከሉትን አብያተ ክርስቲያናት ማበረታታት፤ የሐዋ. 15፡36 እንደሚነግረን፡- ከጥቂት ቀንም በኋላ ጳውሎስ በርናባስን፡- ተመልሰን የጌታን ቃል በተናገርንበት በየከተማው ሁሉ ወንድሞችን እንጐብኛቸው፥ እንዴት እንዳሉም እንወቅ አለው ።
3-  ማነሣሣት፡- ለድሆች የሚሆኑ መዋጮዎችን ማሰባሰብና ማድረስ ፤
የመጀመሪያው የሐዋርያው ጳውሎስ ጉዞ
በ48 ዓ.ም ገደማ የተካሄደ ሲሆን ይህ ጉዞም በሐዋ. 13 እስከ 14 ተጽፎ ይገኛል ። በመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉዞው ሴሌውቅያ ፣ ቆጵሮስ ፣ ስልማና ፣ ጳፉ ፣ ጵንፍልያ ፣ ጴርጌን ፣ ጲስድያ ፣ ኢቆንዮን ፣ ልስጥራን ፣ ደርቤን ፣ ጵንፍልያ ፣ ጴርጌን ፣ አጣልያን የሸፈነ ነው ። በዚህ ጉዞ አሥራ ሦስት አገሮችንና ከተሞችን አገልግሏል ። በጉዞው አብሮት የነበረው በርናባስ ነው ። ይህ ጉዞም 2 ሺህ ኪሎ ሜትሮች የሚደርስ ሲሆን አብዛኛውን ጉዞ በእግራቸው ተጉዘዋል ።
ሁለተኛው የሐዋርያው ጳውሎስ ጉዞ
በአንደኛውና በሁለተኛው ጉዞ መካከል የመጀመሪያው የሐዋርያት ሲኖዶስ እንደ ተካሄደ የሐዋ. ምዕራፍ 15 ይነግረናል ። ሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ በሐዋ. 15፡36 እስከ ምዕራፍ 18፡22 ተመዝግቦ ተቀምጧል ። በዚህ ጉዞ ጳውሎስና ሲላስ አብረው ለወንጌል ሥራ የዘመቱበት ነው ። ማርቆስ እናቱ ስለናፈቀችው በመንገድ ጵንፍልያ ላይ ተለይቷቸው ነበርና በርናባስ ማርቆስን ይዞ ሲመጣ ጳውሎስ ግን ፈቃደኛ አልነበረም ። ስለዚህ በርናባስ ከማርቆስ ጋር ጳውሎስም ከሲላስ ጋር በሁለት ወገን ሄዱ ። በዚህም ነገሩ ለበጎ ሁኖ ሁለት ሐዋርያዊ ቡድን ተመሠረተ ። በርናባስና ማርቆስ ወደ ቆጵሮስ ሲሄዱ ፣ ጳውሎስና ሲላስ ደግሞ ወደ ግሪክ ሂደዋል ። የግሪክ አብያተ ክርስቲያናት የተመሠረቱት በዚህ ጊዜ ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ጉዞው መነሻ ያደረገው አንጾኪያን ነበር ። ጢሞቴዎስ የተገኘው በዚህ በሁለተኛው ጉዞ ነው ። ጉዞው ሶርያ ፣ ኪልቅያ ፣ ደርቤን ፣ ልስጥራን ፣ ፍርግያ ፣ ገላትያ ፣ ጢሮአዳ ፣ ሳሞትራቄ ፣ ናጱሌ ፣ ፊልጵስዩስ ፣ አንፊጶልያ ፣ አጶሎንያስ ፣ ተሰሎንቄ ፣ ቤርያ ፣ አቴና  ፣ ቆሮንቶስ  የተደረገ ነው ። በዚህ ጉዞው 16 ከተሞችን በወንጌል አገልግሏል ። ጉዞው የተካሄደው በ50 ዓ.ም ነው ። በዚህ ጉዞ የፊልጵስዩስ ፣ የተሰሎንቄና የቆሮንቶስ አብያተ ክርስቲያናት ተመሠረቱ።
ሦስተኛው የሐዋርያው ጳውሎስ ጉዞ
በሐዋ. 18፡23 እስከ ምዕራፍ 21፡16 የተመዘገበ ነው ።  የሐዋርያው ጳውሎስ መነሻው አሁንም አንጾኪያ ናት ። በዚህ ጉዞው ገላትያ ፣ ፍርግያን ፣ አሶን ፣ ሚሊጢን ፣ ኤፌሶን ፣ ቆስ ፣ ሩድ ፣ ጳጥራ ፣ ጢሮስ ፣ አካ ፣ ቂሣርያ ፣ በመጨረሻ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞውን ቀጠለ ። በዚህ ጉዞው 12 አገሮችንና ከተሞችን በወንጌል አገልግሏል ። ወደ ኢየሩሳሌም የሄደበት ዋነኛ ምክንያትም ከአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ያሰባሰበውን የገንዘብ እርዳታ ለማስረከብ ነው ። በዚያም በተነሣ ሁከት ታስሮ በ58 ዓ.ም ወደ ሮም ተወሰደ ። በሮምም የቁም እስረኛ ሁኖ ለሁለት ዓመታት ያህል ከቆየ በኋላ በቄሣር ችሎት ነጻ ነው ተብሎ ተለቀቀ ። ከዚህ ጊዜ በኋላ አራተኛውን ሐዋርያዊ ጉዞ እንዳደረገ ይነገራል ። እስጳንያን እንደጎበኘም ይታመናል ። በ64 ዓ.ም ኔሮን ቄሣር ሮምን ራሱ አቃጥሎ በክርስቲያኖች ላይ ስላሳበበ በ65 ዓ.ም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገና ለእስር ተዳርጎ ከሁለት ዓመት እስር በኋላ በ67 ዓ.ም. ሐምሌ አምስት ቀን በሮም ተሰይፏል ። በረከቱ አይለየን ! 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ