የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ/2

የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማወቅ ምን ይጠቅማል ?
ሊቀ ነቢያት ሙሴ፡- “የዱሮውን ዘመን አስብ ፣ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል ፤ አባትህን ጠይቅ፣ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችንም ጠይቅ ፣ ይነግሩህማል” ብሏል ። ዘዳ. 32፡7። የሺህ ዓመታትን ታሪክ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በመጨረሻው ቡራኬና ምክሩ ተናግሯል ። ታሪክን መመርመር የእግዚአብሔር ሕዝብ የተጣለበት አደራና ግዴታ ነው ። ሊቀ ነቢያት ሙሴ በአማራጭ ሳይሆን በትእዛዝ አንቀጽ መናገሩን ማስተዋል ያስፈልገናል። የታሪክ ምንጭ ከሆኑት ውስጥ በመኖር የሚቀድሙ አባቶችና ሽማግሌዎችን ይጠቁማል።

ሁላችንም የታሪክ ውጤቶች ነን ። ብዙ ሰዎች ታሪክን ማጥናት ትርፍ ነገር እንደሆነ ያስባሉ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ራሱ እግዚአብሔር ሥጋ ለብሶ የሠራውና በቅዱሳን አባቶች አድሮ መንፈስ ቅዱስ ያከናወነው ተግባር የሚጠናበት ነው። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያለፈውን ለማወቅ ፣ ያለውን ለማስተዋል ፣ የሚመጣውን ገምቶ የራስን ድርሻ ለማስቀመጥ የሚረዳ ነው። ሁለት ዓይነት ታሪክ አለ ፤ አምላካዊና ሰብአዊ።ታሪክን ከክርስትና ውጭ ማድረግ ተገቢ አይደለም ። ዋናው ክርስትና ነው ቢባልም ክርስትና እኛ ጋ የደረሰው በታሪክ ውስጥ አልፎ ነው ። ታሪክን አለመጠየቅና አለመማር ትእዛዘ እግዚአብሔርን መተላለፍ መሆኑን በነቢዩ ሙሴ የተነገረው ያሳየናል ። በዚህ ክፍል ላይም የታሪክ ምንጮች ሽማግሌዎች ናቸው ። የቀዳሚ ሰማዕት እስጢፋኖስና የንዋየ ኅሩይ የጳውሎስን ትረካ ያጣፈጠው ታሪክን ጠቅሰው በመናገራቸው ነው ። /የሐዋ. 7፡2-53፤ 22፡2-21/ ። ታሪክን ማወቅ የሰሚዎችን ጆሮ ይከፍታል ። አንድ ፈረንጅ መጥቶ ስለ አክሱምና ስለ ላሊበላ ቢነግረን ታሪኩን ብናውቀው እንኳ ውስጣችን ደስ ይለዋል ። ያንንም ሰው እንደ ባዕድ ከማየት ቤተኛ አድርገን እንመለከተዋለን ። ታሪክን ማወቅ ቤተሰብ ይፈጥራል ።
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምንድነው ?
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ ነው ። በሚታየው የምድር መንግሥታት ጉዞ ውስጥ የማይታይ አንድ መንግሥት አለ ፣ እርሱም የእግዚአብሔር መንግሥት ነው ። ቤተ ክርስቲያን የዚህ ሰማያዊ መንግሥት ቋሚና ተጠሪ ናት ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መሠረትም የወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ነው ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስፋትም ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ስበኩ የሚለው ታላቅ ተልእኮ ነው ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፡-
1-  ስለ ክርስትና የሚያጠና የትምህርት ዘርፍ ነው ።
2-  ቤተ ክርስቲያን ያደገችበትን ሁኔታ ያጠናል ።
የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማጥናት፡-
1-  እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ያደረገውን ለማድነቅ ፣
2-  የወደቅንበትን ቦታ እያየን ከማዘን ለማስተካከል ይረዳል ።
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጠናቀቀ ሳይሆን ክርስቶስ ዳግመኛ እስኪመጣ ድረስ የሚቀጥል ነው ። እኛም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሆንን ማወቅ ያስፈልጋል ። የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማወቅ አለመፈለግ ስለራሳችን ማወቅ አለመፈለግ ነው ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከቤተ ልሔም እስከ ቀራንዮ ፣ ከሰማዕታት ዋሻ /ካታኮምብ/ ፣ እስካለንበት ዘመን ድረስ ያለውን የምናይበት ነው ። የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ለምን እናጠናለን ካልን፡-
1-  የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማወቅ ለእምነታችን ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል ። ስለምናምነው እምነት በታሪክ ውስጥ ያለውን የመረጃ ክምችት እናውቃለን ።
2-  ለመጽናት በጣም ይጠቅመናል ። ሐዋርያው በዕብራውያን 11 ላይ ገድለ ቅዱሳንን ተረከና እነዚህ ሁሉ ለእምነት ጽናታችን ጠቃሚ እንደሆኑ ሲገልጽ እንዲህ አለ፡- እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን…ዕብ. 12፡1
3-  ቤተ ክርስቲያን የምታምንባቸው የነገረ መለኮት ትምህርቶች በቅርጽ የተቀመጡት በታሪክ ውስጥ በተነሣ ግጭት ነው ። አንዳንድ የሃይማኖት አንቀጾች ታሪክን ካላወቅን የምንረዳቸው አይደሉም ።
4-  የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም በጣም አስፈላጊ ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር አሳብ ቢሆንም በሰው ቋንቋ ፣ ባሕልና ታሪክ ውስጥ የተገለጠ ነው ።
5-  የእግዚአብሔርን ሥራ ያሳያል ። ቤተ ክርስቲያን ስትደክም እንድትበረታ ያደርጋል ። እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሠራው ሥራ አለና ።
     
ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ሦስት ነገሮችን ማወቅ አስፈላጊ ነው ። የመጀመሪያው መሠረተ እምነቷን ማወቅ ነው ። ሁለተኛው ታሪኳን ማወቅ ነው ። ሦስተኛው ፈተናዋን ማወቅ ነው ። ታሪክን የማያውቅ ሰው ሁሉም ነገር ዛሬ የጀመረ እየመሰለው ይደነግጣል ። በመደነቅም ጉልበቱን ይጨርሳል ። የሚሆነው ሲሆን የነበረ መሆኑን የምንገነዘበው ታሪክን ስናውቅ ብቻ ነው ። ታሪክ ያለፈውን ሃይማኖታዊ ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ ክስተቶችን የምናጠናበት ዐውድ ነው ። ሰው በጊዜ የተወሰነ ፍጡር ነውና ያልፋል ፣ ያለፈውን አውቆ የራሱን ጨምሮ ለመሄድ ታሪክን ማወቅ አስፈላጊው ነው ። ትውልድ የዛሬ ክስተት ሳይሆን ሰንሰለታዊ መስመር ነው ። ሕይወት ወደፊት እልፍ የምናደርገው ጋራ ሥዕል ሲሆን ይህ ሥዕል የሚጠናቀቀው በመጨረሻው ቀን ነው ። የድርሻችንን የምንፈጽመው እንጂ እኛ ጀምረን የምንጨርሰው ተግባር ፣ ወይም በሙሉነት የምንቀርፈው ችግር የለም ። ችግርን ለመቀነስ እንጂ ለመጨረስ የምንሠራ አይደለንም ። ታሪክን ጣዕም ያለው ያደረገው ደረቅ ሁነት ሳይሆን ዛሬም የሚሠራ ሐቅ መሆኑ ነው ።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወሎ ተርቦ ለልደት ቀናቸው ኬክ ከእንግሊዝ አገር አዝዘው አስመጡ የሚል የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ ሲወራ ነበር ። የ1966ቱን አብዮት በዚህና በሌላም ነገር ያደመቁት ወገኖች በ1977 ዓ.ም. ሰው በታላቅ ረሀብ እየረገፈ ዐሥረኛውን የአብዮት በዓል ለማክበር ውስኪ በመርከብ አስጭነው አስመጥተው ነበር ። ታሪክ ካልተጠነቀቁት ይደገማል ። ታሪክ በጥንቃቄ ካጠኑትና ካስተዋሉት መንገድ የመምራት አቅሙ ከፍተኛ ነው ።
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብለን ስንናገር የዓለም ግማሽ ታሪክ ብለን መናገራችን ነው ። በዓለም ላይ የታየው ሥነ ጽሑፍ ፣ ኪነ ጥበብ ፣ ኪነ ሕንፃ ፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ፣ የነገሥታት በቤተ ክርስቲያን አደባባይ መንገሥ ፣ የነጻነት ታሪክ … ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የተከናወነ አይደለም ። ቤተ ክርስቲያን ያልነበረችበትን ክስተት ለይቶ ለማውጣት አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ ያለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የዓለም ግማሽ ታሪክ ሁናለች ። በአገራችን እንኳ አክሱምን ፣ ላሊበላን ፣ ፋሲለደስን ፣ ገዳማተ ጣናን ፣ … ስናስብ ቤተ ክርስቲያን ለአገርና ለዓለም ያበረከተችውን አስተዋፅዖ መረዳት እንችላለን ። ቤተ ክርስቲያን ለአገር እንኳ በቱሪስት መስህቧ እንጀራ ናት ።በእንጀራነቷ እንኳ መከበር አለመቻሏ ፣ በግራና በቀኝ እርስዋን ለማፍረስ በጠላት መከበቧ እያደር የሚገርም ሁኗል ። ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሌለች ኢትዮጵያ ታሪክ የሌላት አገር ትሆናለች ። ፊደልን ቀርጻ የሰጠች ፣ የአገር ፍቅርን ፣ የባንዲራ ክብርን ያስተማረች ቤተ ክርስቲያን ናት ። ከአፍሪካ ብቸኛ የምንሆንበት የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች የሆንነው በቤተ ክርስቲያን ነው ።
በዓለማችን ላይ የሚታዩት ትልልቅና ጥንታዊ የትምህርት ተቋማት አስቀድመው ገዳማት እንደነበሩ ይታወቃል ። ቤተ ክርስቲያን የእውቀት ምንጭ ናትና ። ገዳማውያኑ ያስተማሯቸውን ተማሪዎች ለማስመረቅ ሲያስቡ ምን አልብሰን እናስመርቃቸው ሲሉ የራሳቸውን የምንኩስና ልብስ አልብሰው ስላስመረቋቸው ዛሬ የምናየው የተማሪዎች የመመረቂያ ልብስ ተገኝቷል ። በአጭር ቋንቋ በመነኮሳት ልብስ የሚመረቁ አዋቂዎች ቤተ ክርስቲያንን ማወቅና ማክበር ይገባቸዋል ።
የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ስናጠና ሁለት ነገሮችን መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው ።የመጀመሪያው ፍጹምነትን መፈለግና ሁለተኛው ታሪክ አያስፈልገንም ብሎ ማሰብ ነው ።
ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ናት ። ተልእኮዋንም በጊዜና በቦታ ስለምታከናውን የራሷ ታሪክ አላት ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምንጮች ምንድናቸው፡-
1-  ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን
2-  መጻሕፍተ ሊቃውንትና ዓለም አቀፍ ጉባዔያት
3-  የነገሥታት አዋጅ
4-  ትውፊቶች
5- የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊዎች ፣ /አውሳብዮስ፣ ሶቅራጥስ፣ ሩፊኖስ፣…ይጠቀሳሉ/ 
6- በየጊዜው እየተገኙ ያሉ መቃብሮች ፣ ሥዕሎች ፣ ገንዘቦች ፣ መቅደሶች በአጠቃላይ የሥነ ምድር ቁፋሮ ወይም የአርኪዎሎጂ ግኝቶች
7-  የተለያዩ ቅርሶች የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምንጭ ናቸው ።
ይቀጥላል
እባካችሁ ሰዎች እንዲያውቁ የበኩላችሁን ተወጡ
ዲአመ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ