የቤተ ክርስቲያን ስያሜ
ቤተ ክርስቲያን ተብሎ በግእዝ የተተረጎመው ቃል በግሪኩ “አቅሌስያ” ይባላል ። አቅሌስያ ማለት “የተጠሩና የተመረጡ የመፍትሔ አፈላላጊዎች ሸንጎ” ማለት ነው ። የጥንት ግሪካውያን በአገር ፣ በመንደሩ አንድ ችግር ሲከሰት ያንን ለመፍታት የተጠሩና የተመረጡ ሰዎች ስብስብ “አቅሌስያ” በማለት ይጠሩት ነበር ። “አቅሌስያ” መንፈሳዊ ትርጉሙን ሲያገኝም ኅሩያነ እግዚአብሔርን ወይም የእግዚአብሔር ምርጦችን ለመግለጥ ውሏል ። ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል መሠረቱ አቅሌስያ ከሆነ ለአቅሌስያም እንደ መነሻ የሚሆነው የዕብራይስጡ “ኤዳህ” እና “ካሃል” የሚሉት ስያሜ ናቸው ። “ኤዳህ” የሚለው ስያሜ ጥቅም ላይ የዋለው እግዚአብሔርን ለማምለክ የተሰበሰበን ሕዝብ ለመግለጽ ነው ። “ካሃል” የሚለው በብሉይ ኪዳን 123 ጊዜ በላይ የተጠቀሰ ሲሆን ጉባዔ /ማኅበር/ በሚል ትርጉም ይታወቃል ። “ካሃል” ሃይማኖታዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለተፈለገ ዓላማ የተሰበሰበን ሕዝብ ለመግለጥ ተጠቅመውበታል ።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ284 ዓመት ብሉይ ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሌላ ቋንቋ ተተረጎመ ። የተረጎሙትም በእስክንድርያ የተገኙት ሰባ የአይሁድ ሊቃውንት ናቸው ። የእነርሱም ትርጉም የሰባ ሊቃናት ትርጉም ተብሎ ይጠራል ። እነርሱም “ካሃል” የሚል ሲያገኙ አቅሌስያ በማለት ተርጉመውታል ። “አቅሌስያ” ከሁለት ጥምር ቃላት የተገኘ ግሪክኛ ሲሆን “ኤክ” እና ካልዮ ከሚሉት ቃላት በመውጣት ሲሰየም “ኤክ” ማለት የወጡ ሲሆን “ካልዮ” ደግሞ የተጠሩ ማለት ነው ። በአንድነትም ስናነብ ተጠርተው የወጡ ምርጦች ማለት ነው ። “አቅሌስያ” የሚለው የግሪክ ቃል በአዲስ ኪዳን 113 ጊዜ በላይ የተጻፈ ሲሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትም ሁለት ጊዜ ብቻ ተጠቅሷል ። ማቴ. 16፡16 ፤ 18፡19 ። ማኅበር በማለት የተጠቀሱት ሁሉ “አቅሌስያ” ተብለው እንደተተረጎሙ በደንብ ማየት ይቻላል ።
“ቤተ ክርስቲያን” ተብሎ ወደ ግእዝ የተተረጎመው አቅሌስያን የተካ ቃል ነው ። ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ሲጠራም ሦስት ነገሮችን አመልካች ነው፡-
1- ወገንን አመልካች ነው ። ቤተ እስራኤል ማለት የእስራኤል ወገን ፣ ቤተ አሮን ማለት የአሮን ወገን ማለት እንደሆነ ቤተ ክርስቲያን ማለትም የክርስቲያን ወገን ፣ የክርስቶስ ወገን ፣ ዘክርስቶስ እንደማለት ነው ። ይህም የተስፋውና የመንግሥቱ ወራሾች የሆኑትን ምእመናን የሚገልጥ ነው ። ክርስቲያን የሚለው ስያሜ የወጣው ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ ነው ። ክርስቲያን ማለትም የክርስቶስ ተከታይ ፣ የክርስቶስ ወገን ፣ በመንፈስ ቅዱስ የከበረ ፣ መሢሓዊ ፣ ክርስቶሳዊ ፣ ዘክርስቶስ ማለት ነው። ቅዱስ አውስጢኖስ፡- “ክርስቲያን ማለት ሌላው ክርስቶስ ማለት ነው” ያለው ለዚህ ነው ።
2- የክርስቲያኖች ስብስብ ቤተ ክርስቲያን በመባል ተጠርቷል ። “ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።” 1ጴጥ. 5፡13 ። ሰላምታ የምታቀርበዋ ቤተ ክርስቲያን በባቢሎን ያለች ማኅበረ ምእመናን ናት ። በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያን ዘኤፌሶን ፣ ቤተ ክርስቲያን ዘሎዶቅያ ፣ ቤተ ክርስቲያን ዘኢትዮጵያ ይባላል ።
3- መሰብሰቢያ ቦታን አመልካች ነው ። “ቤተ ክርስቲያን እንሂድ” እንዲሉ ። ምእመናን የሚሰባሰቡባት ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን የሚቀበሉበት ቦታ “ቤተ ክርስቲያን” ተብላ ትጠራለች ። በእንግሊዝኛው “ቸርች” የሚለው ቃል የተወሰደው ከላቲን ሲሆን ትርጉሙም “የጌታ ሀብት” ማለት ነው ። ይህም ቤተ ክርስቲያን የሰው አለመሆኗን ለመግለጥ የዋለ ቃል ነው ።
የቤተ ክርስቲያን ባሕርይዋ
ባሕርይ አይቀየርም ፣ ጠባይ ግን ይቀየራል ። ቤተ ክርስቲያን የማይቀየሩ አራት ባሕርያት አሏት ። ጸሎተ ሃይማኖት ብለን የምንጠራው የሁለቱ ታላላቅ ጉባዔያት ማለትም የኒቅያ /325 ዓ.ም/ እና የቊስጥንጥንያ /381 ዓ.ም/ ጉባዔ መግለጫ ነው ። “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ ዘሠረጸ እምአብ” ከሚለው ጀምሮ ያለው የቊስጥንጥንያ ጉባዔ መግለጫ ነው ። የቊስጥንጥንያ ጉባዔ መግለጫም የቤተ ክርስቲያንን ባሕርይ የሚገልጹ ውሳኔዎችን አስተላልፏል ። “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት” ማለትም “በአንዲት ፣ ቅድስትና በሁሉ ባለች ሐዋርያት በሰበሰቧት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” የሚል ነው ። በዚህ መሠረት ቤተ ክርስቲያን አራት መገለጫዎች አሏት እንላለን፡-
1- አንዲት፡- ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት ። አንድ ራስ ብዙ አካሎች የሉትምና የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው አንዱ ክርስቶስ አንዲት ቤተ ክርስቲያን አለችው ። የኒቅያ ጉባዔ የቤተ ክርስቲያን አንድነት የታየበት ጉባዔ ስለነበር ዓለምና ነገሥታት አክብረውታል ። የኬልቄዶን ጉባዔ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የተለያየችበት ስለነበር ዓለም ንቀቱን ፣ ነገሥታቱ እነመርቅያል ድፍረታቸውን ያሳዩበት ኋላም ለመሐመዳውያን በር የከፈተ ሁኗል ። የኒቅያ ጉባዔ በዓለም ላይ አራት መንበሮችን ሰይሞ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናት ጥሯል ። ለምዕራቡ የሮምን ፣ ለሰሜን ኤፌሶንን ፣ ለምሥራቁ አንጾኪያን ፣ ለደቡቡ እስክንድርያን ሰይሟል ። በእነዚህ አቅራቢያ ያሉ በሚቀርባቸው መንበሩ ሥር በመሆን አንዲቷን ቤተ ክርስቲያን ይጠብቃሉ ።
2- ቅድስት፡- የቅዱሱ የክርስቶስ አካል ናትና ቅድስት ናት ። ወደ እርስዋ የሚመጡ ታሪካቸውና ስማቸው ይለወጣልና ቅድስት ናት ።ከዓለም ስለመለየትና ክርስቶስን ስለመምሰል ታስተምራለችና ቅድስት ናት ።
3- ዓለም አቀፋዊት /ኩላዊት/ ፡- ወደ ምዕራቡ የሄደችው ቤተ ክርስቲያን ራሷን “ካቶሊክ” ማለቷ የሁሉም ነኝ ለማለት ብቻ ሳይሆን ኩላዊት ነኝ በሁሉ ያለሁ ነኝ ለማለትም ነው ። “እንተ ላዕለ ኩሉ” የሚለው ስያሜ ግን የአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን መጠሪያ ነው ። ቤተ ክርስቲያን በሁሉና ለሁሉ ያለች ናት ። የዘር ፣ የቀለም ፣ የቋንቋ ግርዶሽ የለባትም ።
4- ሐዋርያዊት፡- በሐዋርያት ትምህርት ላይ የተመሠረተች ፣ በተመሠረተው ላይ የተካበች ፣ ዘላለማዊነትን እንጂ ዘመናዊነትን ያልተከተለች ናት ። ከጌታችን ለሐዋርያት ፣ ከሐዋርያት ለሊቃውንት ሲተላለፍ የኖረው የአንብሮተ ዕድ ወይም እጅ የመጫን ሰንሰለታማ ጉዞ ያለባት ናት ። ዛሬ የምናየው አንድ ሊቀ ጳጳስ በአንብሮተ ዕድ ቅብብሎሹ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ይገናኛል ። ከዚያም ከጌታ ጋር ይገናኛል ። ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ስብከቷ ፣ የክህነት ቅብብሎሽዋ ያልተቋረጠ ሲሆን ብቻ ሐዋርያዊት ትባላለች።
ይቀጥላል
አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!
ዲአመ