የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ/6

የቤተ ክርስቲያን ምሥረታ
ቤተ ክርስቲያን እንደትመሠረት ምክንያት የሆነው የአዳም በበደል መውደቅ ነው ። አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፉ ምክንያት ለራሱና ለልጆቹ መከራ አምጥቶአል ። መሪውን የያዘው ሾፌር ወይም ካፒቴን ተሳፋሪውን ያደርሳል ወይም ገደል ይዞ ይገባል ። አዳምም መሪ ነበርና እርሱ ሲስት ትውልዱ ሁሉ የሳተ ሆነ ። አዳም መንገድ እንደ ጠፋውና እንደ ወደቀ እግዚአብሔር አምላክ “ወዴት ነህ ?” በማለት ባሰማው ድምፁ ታውቋል ። ዘፍ. 3፡10 ። ኃጢአት የሚለው ቃል በዕብራይስጡ “ዓላማ መሳት” የሚል ፍቺ አለው ። ለአዳም በቀጥታ ትእዛዝ የሰጠው ራሱ እግዚአብሔር ሲሆን ሔዋንን በቀጥታ ያማከረው ደግሞ ራሱ ሰይጣን ነው ። አዳም ከእግዚአብሔር የሰማውን በትክክልና በሰማበት ሙቀት ለሔዋን አልነገራትም ፣ ሔዋን ግን ከሰይጣን የሰማችውን በሰማችበት ግለት ነገረችው ፣ መንገድ አጋምሳም ጠራችው ። ትእዛዝ ዋጋ የሚኖረው ሲፈጽሙት ሰላም ፣ ካልፈጸሙት ቅጣት ሲኖረው ነው ። አዳም እንዲሁ ቢታለፍ እግዚአብሔር የገዛ ትእዛዙን እንደ ናቀ ይቆጠራል ። ራሱን የማይክድ ፍትሐ ጽድቅ ያለው እግዚአብሔር በአዳም ላይ ሞትን ፈረደበት ። ልጅ የአባቱን ሀብት ብቻ ሳይሆን ዕዳም ይወርሳልና የአዳም ልጆች ከአዳም የሞትን ዕዳ ወረሱ ።

እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከገነት ሳያስወጣው ወደ ገነት እንደሚመለስ ተስፋ ሰጠው ። ዘፍ. 3፡15 ። ከዚህ በኋላ እርሱ የሚመራው የሰው ልጅ ማኅበር ማኅበረ ሙታን ስለሚሆን የሕያዋን ማኅበር የምትሆን ቤተ ክርስቲያን እንደምትመሠረት ተስፋ ሰጠው ። ይህም ዳግማዊ አዳም ሁኖ በሚመጣው በክርስቶስ የሚፈጸም ነው ። ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም የአዲሲቱ ዓለም የቤተ ክርስቲያን መሥራችና ራስ ነው ። የቤተ ክርስቲያን ምሥረታ በገነት የተነገረ ሲሆን አዳም ገነትን በአካል ለቆ ቤተ ክርስቲያንን በልቡ ይዞ ወጣ ።
ይህ ታላቅ ተስፋ የተነገረው ለሰይጣን ነው ። አዳምና ሔዋንን በመጣሉ ፈጽሞ ደስ እንዳይለው በተስፋ ቃል ደስታውን አቋረጠው ። ሰይጣንም አዳኙ ዘር የሚወጣበትን ወገን ለማጥቃት ከጠዋቱ ውጊያና ሰልፍ ጀመረ ። ያ አዳኝ ዘር ከማን እንደሚወለድ መንገዱ ጥርት ብሎ መታየት የጀመረው አብርሃም በተጠራ ጊዜ ነው ። ዘፍ. 12፡1 ። መሢሑ የሚወጣበት ዘር አውራ ጎዳናው ታየ ። አብርሃም ይስሐቅን ወለደ ፣ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ ። ያዕቆብም የእስራኤል መሥራች የነበሩትን አሥራ ሁለት የነገድ አለቆች ወለደ ። ያዕቆብ ሰባ ነፍስ ሁኖ ወደ ግብጽ ገብቶ ነበር ። ከ215 ዓመታት በኋላ ግን ሕዝቡ ግማሽ ሚሊየን አለፈ ። እግዚአብሔርም በታላቁ የነጻነት ታጋይ በሙሴ በኩል እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነጻ አወጣ ። አገር አልባ ሁነው የኖሩበት ጠቅላላው ዘመን 430 ዓመት ሲሆን በግብጽ የቆዩት ግን 215 ዘመን ነው ። የ430 ዓመታት የባርነትና የስደተኛነት ዘመን አበቃ ። ባለማመናቸው ምክንያት የአርባ ቀኑ መንገድ አርባ ዓመት ፈጀባቸው ። በሙሴ የተጀመረው የተስፋይቱ አገር ጉዞ በኢያሱ ተጠናቀቀ ። ኢያሱ ርስትን አካፍሎ ሁለተኛው መስፍን ሆነ ። ከኢያሱ ሞት በኋላ 13 የሚሆኑ መሳፍንት አስተዳደሩአቸው ። ይህም ለ300 ዓመታት መሆኑ ነው ። ዘመነ መሳፍንት እንዳለፈ “ዘመነ ነገሥት” መጣ ። የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል ሲሆን ሁለተኛው የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት ነው ። ዳዊትም መሢሑ የሚወጣበት ዘር በመሆኑ ከአብርሃም በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ መሢሑ የሚወጣበት አውራ ጎዳና ፍንትው ብሎ ታየ ።
ከዳዊት በኋላ እስራኤልን ያስተዳደረው ጠቢቡ ሰሎሞን ነው ። ከሰሎሞን በኋላ ልጁ ሮብዓም ነገሠ ። እስራኤልም ቀንበር እንዲያቀልላቸው ጠየቁት፤ እርሱ ግን ከቢጤዎቹ ጋር በመምከሩ በእልህ እስራኤል ለሁለት ተከፈለች ። /1ነገሥ.12 ።/ አሥሩ ነገድ ከዳዊት ሥርወ መንግሥት ተነጥሎ የንግሥና ዘር ያልነበረውን ኢዮርብዓምን አነገሠ ። የግዛቱ ስም እስራኤል ፣ የግዛቱ አውራጃ ሰማርያ ፣ መናገሻ ከተማውም ሴኬም ሆነ ። ለዳዊት ቤት ሁለት ነገድ ቀረ ። የይሁዳና የብንያም ነገድ ። በዚህም የደቡብ ግዛት ይሁዳ ፣ መንግሥቱም የይሁዳ መንግሥት ተባለ ። መናገሻ ከተማዋም ኢየሩሳሌም ነበረች ።መለያየት ግን ጥፋትን እንጂ ልማትን አምጥቶ አያውቅምና  ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ722 ዓመት የሰማርያ ግዛት ወይም የእስራኤል መንግሥት በአሦራውያን ተወረረ ። አሦራውያን የአገራቸውን ዱርዬዎች አምጥተው በሰማርያ አፈሰሱ ። የእስራኤልን ክብር የሚያውቁ ፣ ታሪክ አዋቂ ሽማግሌና ምሁራንን ማርከው ወደ አሦር ወሰዱ ። የቀረው ሕዝብ ከአሦራውያን ጋር በጋብቻ ተቀላቀለ ። ማንነቱን እንዳያውቅ ምሁር አልባ ሆነ ። በዚህም ሳምራውያን ቅይጥ ሕዝቦች ተብለው በደቡብ ከሚኖሩት ጋር በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትም ተለያዩ ።
የሰሜኑ ዕጣ በደቡቡ ደረሰ ። በ586 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ባቢሎናውያን የይሁዳን መንግሥት አፍርሰው ፣ ታላቁን መቅደስ አቃጥለው ፣ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንዳልነበር አድርገው ሕዝቡን ማርከው ወሰዱት ። የምርኮው ዘመናት ሰባ ዓመታት ፈጀ ። ከሰባ ዓመታት በኋላ መቅደሱን እንደገና ሠሩ ። የመጀመሪያው በሰሎሞን ፊታውራሪነት ስለተሠራ “የሰሎሞን መቅደስ” ይባል ነበር ። ሁለተኛው መቅደስ በዘሩባቤል መሪነት ስለ ተሠራ “የዘሩባቤል መቅደስ” ይባላል ። ኢየሩሳሌምም ቅጥሯ ታድሶ ብትኖርም መንግሥቷን መመሥረት ግን አልቻለችም ነበር ። እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ያስተዳድሩ የነበሩት ካህናት ነበሩና ጊዜው “ዘመነ ካህናት” ተብሎ ይጠራል ። የዓለም ፖለቲካም በየጊዜው እየተለዋወጠ ተረኛ ኃይለኛ ሲመጣ እስራኤልን አላለፋትም ። የባቢሎን አገዛዝ እንደ ወደቀ የፋርስና የሜዶን ጥምር መንግሥት ቀጠለ ፣ ከዚያም የታላቁ እስክንድር ግሪካዊ መንግሥት በዓለም ላይ ተንሠራፋ ። እስራኤል አሁን በግሪካውያን እጅ ወደቀች ። የግሪካውያን ተራ ሲያበቃ የሮማውያን አገዛዝ ሰፈነ ። ታላቁ እስክንድር ለጥበብ ያደላ ነበርና የአይሁድ እምነት ባለ መጽሐፍ በመሆኑ ፣ በአደረጃጀቱም እንከን አልባ በመሆኑ እውቅና ሰጥቶት ነበር ። ሮማውያንም ያንን እውቅና ተቀብለው አክበረዋቸዋል ። ነገር ግን ቅኝ አድርገው መግዛታቸው አልቀረም ። ለአጥቢያውም ሹም እንዲሆን ታማኝነትን ያሳየውን ኤዶማዊውን ሄሮድስን የሮሙ ቄሣር ሮም ላይ ቀባው ። የሄሮድሳውያን መንግሥትም ከክርስቶስ ልደት 37 ዓመት ቀደም ብሎ ጀመረ ። የአይሁድን ሃይማኖት ተቀብለው ነበርና ትልቁ ሄሮድስ የዘሩባቤል መቅደስ እንዲስፋፋና እንዲጠገን ሥራ ጀመረ ። በዚህም የአይሁድን ቀልብ የሳበ ይመስላል ። ጌታችን በምድር ላይ ሲመጣ ይህ መቅደስ በእድሳት ላይ ነበረ ። መቅደሱም እድሳቱ አልቆ የተመረቀው በ64 ዓ.ም. ነው ። የሚገርመው በ70 ዓ.ም. በሮማውያን ተደመሰሰ ።
ሮማውያን ግዛታቸውን በመላው ዓለም አስፍነው ሳለ ጌታችን ተወለደ ። ማደሪያው ትሆነው ዘንድ የመረጣት በሁለት ወገን ድንግል የሆነችውን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው ። የሔዋን አለመታዝዝ ሁልጊዜ እንዳይወራ የድንግል ማርያም መታዘዝ እንደ ገታው እንረዳለን ። እርሷም ሰማይና ምድር የማይችሉትን ጌታ በማኅፀኗ ተሸከመችው ። ታላቅም ተአምርና ሊነገር የማይችል ምሥጢር በድንግል ማርያም ላይ ተከናወነ ። ይህም ምሥጢር ወንጌል በተነገረበት ስፍራና ዘመን ሁሉ ሲወሳ ይኖራል ። ከብፅዕት ድንግል በቤተ ልሔም የተወለደው ጌታ ለዕድገቱ የሽፍቶቹን ከተማ ናዝሬት መረጠ ። ሞቱም በኢየሩሳሌም ሆነ ። በቀራንዮ ገድለውት እርሱ ግን በጎልጎታ ተነሣ ። እያዩትም ሽቅብ ወደ ሰማይ ዐረገ ። እርሱ የአዲሲቱ ዓለም መሥራች ነውና “ዳግማዊ አዳም” ይባላል /1ቆሮ. 15፡45/ ። የአዲሲቱ እስራኤል መሪ ነውና በያዕቆብ ወገን ላይ ለዘላለም ይነግሣል ተባለለት ። /ሉቃ. 1፡33/።
እስራኤላውያን መንግሥታቸው ከፈረሰ 400 ዓመታት በላይ ሆነ ። ይህ ዘመንም ነቢያት ያልተነሡበት ዘመን ነበር ። ነቢያት የሚላኩት ለአገራዊ አጀንዳ እንጂ ለሽሮና ለበርበሬ ስላልሆነ መንገሥት ሲፈርስ የነቢያት አገልግሎትም ቆመ ። አስራኤልም አንድ ተስፋ ብቻ በልባቸው ቀረ ። መሢሑ ሲመጣ የጦር ሰዎችን አሰባስቦ ከሮማውያን ጋር ተዋግቶ ነጻ ያወጣናል ። እኛን የቅርብ ባለሟሎቹ አድርጎ በመላው ዓለም ይነግሣል እያሉ መጠበቅ ጀመሩ ። “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እንዲሉ ። መሢሑን ያልተቀበሉት እንደ ጠበቁት ስላልተገለጠ ነው ።
እስራኤል በአሥራ ሁለት የነገድ አለቆች እንደ ተመሠረተች ቤተ ክርስቲያንም በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ተመሠረተች ። የልደት ቀኗንም በበዓለ ሃምሳ የመንፈስ ቅዱስ ድግስ አክብራ ሥራዋን ጀመረች ። የተነሣቸው የምድርን ዳርቻ የግዛት ጠረፍ አድርጋ በመሆኑ ዓለም አቀፋዊት ናት ። ሥራዋንም መሥራቿ የሆነው ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ እስከ ዓለም ፍጻሜ ትቀጥላለች ። /ማቴ. 28፡20/
የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስምና አገልግሎት በአጭሩ ምን ይመስላል ?
ይቀጥላል
አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!
ዲአመ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ