የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /8

የመዘጋጀት ዘመን ያደረገው አስተዋጽዖ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ የነበሩት ምቹ ሁኔታዎች ወንጌል በዓለም ሁሉ እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል ። ዓለም አይሁድና አሕዛብ ተብሎ በሁለት የተከፈለበት ዘመን ነበር ። አይሁድ የሚባሉት አንድ አምላክን የሚያመልኩና በመገለጥና በመጽሐፍ የሆነ እምነት ያላቸው ሲሆኑ አሕዛብ ደግሞ ከእነርሱ የሚያንሱ ፍጥረታትን የሚያመልኩ እምነታቸውንም በተረትና በፈጠራ ላይ የመሠረቱ ነበሩ ። እግዚአብሔር ትክክለኛ ጊዜን የሚያውቅ የጊዜ ድሀም ያልሆነ አምላክ ነው ። ጌታችን በሥጋ ሲመጣ የነበሩት መዘጋጃዎች፡-

1- የሮም መንግሥት በዓለም ላይ መስፋፋት
  በዓለም ላይ ሰልጥኖ የነበረው የግሪክ መንግሥት እየተዳከመና እየተከፋፈለ ሲመጣ የተካው ተረኛ ኃያል የሮም መንግሥት ነበር ። የሮሙ ጀነራል ፖምፔ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ63 ዓመት ኢየሩሳሌምን ተቆጣጥሮ ይሁዳን የሮም አካል ሲያደርግ ያን ጊዜ የሮም መንግሥት በዓለም ላይ ማንሠራራት ጀመረ ። ይህም መንግሥትም እስከ 476 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት መቶ ዓመታት ያህል የቆየ ነው ። በርግጥ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ምሥራቅና ምዕራብ ተብሎ ለሁለት የተከፈለ መሆኑን አንረሳም ። የሮም መንግሥት ለዓለም ሰላም አስገኝቻለሁ ብሎ የሚያምን ሲሆን በርግጥም ሰላምን በማስገኘቱ የተመሰገነ ነበር ። መላውን ዓለም በመንገድ ፣ በባሕር መጓጓዣ አገናኝቶት ስለነበር በቀላሉ ካንዱ አገር ወደ አንዱ አገር መሄድ ይቻል ነበር ። የይለፍ ወረቀትም ስለማይጠየቅ ወደ ፈለጉበት አገር ያለ ጠያቂ መንቀሳቀስ ይቻል ነበር ። ሐዋርያት በዓለም ላይ ዞረው ወንጌልን ለመስበክ ምቹ መንገዶችና ድንበር አለመኖሩ በብርቱ አግዟቸዋል ። ዛሬ ቢሆን ኑሮ ጳውሎስና ጴጥሮስ ወንጌል ለመስበክ የቪዛ ማመልከቻ መጠየቅ ያስፈልጋቸው ነበር ። እግዚአብሔር ግን ጊዜን የሚያውቅ በመሆኑ በዚያ ጊዜ በሥጋ መጣ ። ሐዋርያትንም ወደ ዓለም ላከ ።
2-  የዓለም ቋንቋ አንድ መሆኑ

የግሪክ መንግሥት ቢወድቅም ቋንቋውና የፍልስፍናው ተጽእኖ ግን እንደ ቀጠለ ነበር ። ውጫዊ የሆነ አገዛዙ ቢወድቅም ረቂቅ አገዛዙ ግን ዘመን ተሻግሮ ነበር ። ታላቁ እስክንድር የሄደው በጦር ኃይል ብቻ ሳይሆን በጥበብም ነበር ። የግሪክ ቋንቋ እንደ ዛሬው እንግሊዝኛ የመላው ዓለም መግባቢያ ሁኖ ነበር ። አዲስ ኪዳንም ከማቴዎስ ወንጌል ውጭ በግሪክኛ ተጽፎአል ። የሚበዛው የዓለም ሕዝብ ግሪክኛ ተናጋሪ መሆኑ ለመዘጋጃው ዘመን አስተዋጽዖ አድርጓል ።
3-  የቅዱሳን መጻሕፍት መተርጎም

   ከክርስቶስ ልደት 284 ዓመት ቀደም ብሎ በታላቁ እስክንድር በተሰየመችው ላዕላይ ግብጽ እስክንድርያ በተባለችው የወደብ ከተማ ብሉይ ኪዳን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ተተርጉሟል ። በእስክንድርያ ተቀምጠው የተረጎሙት ሰባ የአይሁድ ሊቃውንት ሲሆኑ ትርጉሙም “የሰባ ሊቃናት ትርጉም” ተብሎ ይጠራል ። በእስክንድርያ ከተማ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ተቋቁሞ የመላው ዓለም ጽሑፎች ተቀምጠውበት ነበር ። በዚህ ቤተ መጻሕፍትም ከ700 ሺህ በላይ መጻሕፍት ተቀምጠው ነበር ። በዚህ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የብሉይ ኪዳን ቅጂ አለመኖሩ ስላሳሰባቸው ሰባ የአይሁድ ሊቃውንት ተሰብስበው ብሉይ ኪዳንን ወደ ግሪክ ቋንቋ ተርጉመዋል ። በዚህም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በዓለም መነበብ ጀመሩ ። አሕዛብም ስለ አንዱ አምላክና ስለ ክርስቶስ መምጣት ማሰብ ጀመሩ ። ይህም ለአዲሱ ኪዳን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነበር ።

4- የአይሁድ በመላው ዓለም መበተን

    አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ከአገራቸው ውጭ መኖር ጀምረው ነበር ። የአምልኮ ማዕከላቸው መቅደሱ ስለ ነበር ወደ ኢየሩሳሌም ሦስቱን በዓላት ለማክበር ይመለሱ ነበር ። በ70 ዓ.ም መቅደሱ በመደምሰሱ ግን የአምልኮ ማዕከላቸው የሆነው ኦሪት ነበር ። በአገሩ ከሚኖረው አይሁዳዊ በዝርወት የሚኖረው አይሁዳዊ በልጦ ነበር ። አይሁዳውያን በሚሄዱበት አገር ባሕላቸውንና ሃይማኖታቸውን ይዘው ስለሚሄዱ አሕዛብ ስለ አንዱ አምላክ የማወቅ ዕድል አግኝተዋል ። ይህም መልካም የመዘጋጃ ዘመን ሁኖ የአዲስ ኪዳንን አገልግሎት አቅልሎታል ።
 ጌታችን በሥጋ በተገለጠበት ዘመን የነበረው የዓለም ሁኔታ ባዕድ አምልኮ የተስፋፋበት ዘመን ነበር ። ለእያንዳንዱ ፍጥረት በነፍስ ወከፍ አምላክ እየሰጡ የፀሐይ አምላክ ፣ የዝናብ አምላክ ፣ የጦርነት አምላክ እያሉ የሚያመልኩበት ዘመን ነበር ። የአምልኮ ምንዝርና በብርቱ የነገሠበት ዘመን ነበር ። በዚህም ጣዖት በመጥረብ የሚተዳደሩ ብዙ ሠራተኞችን ፈጥሮ ነበር ። ከአምልኮ ምንዝርና ባሻገር የጌታና የባሪያ ሥርዓት በዓለም ላይ ሰፍኖ ነበር ። ባሮች ሰውነታቸው ተዘንግቶ እንደ ከብት ይሸጡ ይለወጡ ነበር ። ሰውም ሀብቱን የሚለካው ይህን ያህል ባሪያ አለኝ በማለት ነበር ። ባሪያው የጌታው ዕቃ ስለሆነ ጌታው ቢገድለው ንብረቱ ስለሆነ አይጠየቅም ነበር ። ሴቶችም እንደ ተንቀሳቃሽ ዕቃ ይታዩ ነበር እንጂ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ክብረት ገና አልታወቀም ነበር ። ሐዋርያው፡- ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” ብሎ መናገሩ የራሱ ምሥጢርም ነበረው ። /ገላ. 4፡4/ በዚያ ዘመን ፍልስፍና ሴት ልጅ ፣ ልጅን በማስገኘት ሂደት ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላት ማኅፀኗ እንደ ኪራይ ቤት ብቻ ይታሰብ ነበር ። ጌታችን የሴት ዘር ሁኖ መምጣቱ ይህን ፍልስፍና ጭምር ድል የነሣ ነው ።
 ጌታችን በሥጋ በተገለጠበት ዘመን በምድረ እስራኤል የነበረው ሁኔታ ተስፋ የማይጣልበት ፣ ሕዝብ በሥራ አጥነትና በፍርድ መዛባት የሚያለቅስበት ዘመን ነበር ። የአእምሮ ጭንቀትም በብዙ ተስፋፍቶ ነበር ። የሃይማኖት ቡድኖች ቊጥራቸው ቢበዛም አንዳቸውም ዕረፍትን ማምጣት አልቻሉም ነበር ። በሃይማኖት ቡድኖች መካከል የሚነሣው ፍጭትም ሕዝቡን ሜዳ አድርጎ የሚከናወን በመሆኑ አብዛኛው ወገን የመንፈስ ዝለት ገጥሞት ነበር ። ጌታችን ሲመጣ የነበሩት የሃይማኖት ቡድኖች እነማን ናቸው ?
ይቀጥላል
አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ