“ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል ።” ኤፌ. 4 ፡ 16 ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው ። ራስ አካል ፣ ሙሽራም ሙሽራይት አሉት ። ጌታችንም አካሉ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ፣ ሙሽራይት የሆነች ምእመን አለችው ። ራስ አካሉን ይንከባከባል ። ጌታችንም አካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በጸጋ ፣ በምሥጢራት ፣ በአገልጋዮች ይንከባከባታል ። ራስ አካሉን ያድናል ፣ ጌታችንም አካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን አድኗታል ። ራስ የአካሉ ሕመም ይሰማዋል ፣ ጌታችንም የቤተ ክርስቲያን ነገር ገና ከጀርባው ያልወረደ መስቀሉ ነው ። ራስ ከአካሉ አይለይም ፣ ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን ለዘላለም ወዷታል ። ራስ አካሉን ይሸፍናል ፣ ጌታችንም ለቤተ ክርስቲያን ማጌጥ በአደባባይ ተራቁታል ። ራስ አካሉን ያፈቅራል ፣ ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን በአጋፔ ፍቅር ወዶአታል ። ሰው እጁን የሚወደው ስለ ሠራ ፣ እግሩን የሚወደው በሩጫ ድል ስላመጣለት አይደለም ። አካሉ ስለሆነ ያለ ቅድመ ሁኔታ ይወደዋል ። ጌታችንም ቤተ ክርስቲያንን እንዲሁ ወዶአታል ። ራስ አካሉን ያነጻል ፣ ጌታችንም ቤተ ክርስቲያንን በደሙ ቀድሶአል ። ቤተ ክርስቲያን የተባለችም የዳነች የምእመናን ስብስብ ፣ ሕያዊት አካል ናት ።
ጌታችን ሙሽራይት አለችው ። ሙሽራ ነውና ። ደቀ መዛሙርትም በአማኝነታቸው ሙሽራይት ፣ በአገልጋይነታቸው ሚዜዎች ናቸው ። ሙሽራ የሰርጉን ቀን ይናፍቃል ፣ ጌታችንም ዳግም እስኪወስደን ቀጠሮ ሰጥቶናል ። ሙሽራ ሚዜዎች ያዘጋጃል ፣ ጌታችንም አገልጋዮችን ሾሞልናል ። ሙሽራ ሽማግሌ ይልካል ፣ ጌታችንም የልባችንን ደጃፍ ያንኳኳል ። በ40 እና በ80 ቀን ስንጠመቅም ለቤተሰቦቻችን ሽማግሌ እንደላከ ማሳያ ነው ። ወላጆች “ልጄን ለልጅህ” ይላሉ ። እንዲሁም አማኝ ሲሆኑ “ልጄን ለክርስቶስ” በማለት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ያሰጣሉ ። ሙሽራ ሁሉን አዘጋጅቶ ሙሽራይትን ይጠብቃል ፣ ጌታችንም ስፍራ ሊያዘጋጅ ወደ ሰማይ ሂዷል ። ሙሽራ ወደ አባቱ ቤት ሙሽራይትን ይዞ ይመጣል ፣ ጌታችንም በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ ብሎ ለምእመን ነግሮአታል ። ሙሽራ ማጫ ያመጣል ፣ ጌታችንም ለወንጌል ሙሽራይት ኦሪትን ማጫ አድርጎ ሰጥቷል ። ሙሽራ የሰርግ ቀን አለው ፣ ጌታችንም በዳግም ምጽአት ታላቅ እራት አዘጋጅቷል ። ሙሽራ ለሙሽራይት ራሱን ይሰጣል ፣ ጌታችንም ለምእመን በአደባባይ ተሰቅሏል ። አንድ ሙሽራ አንዲት ሙሽራይት አለችው ፣ ጌታችንም አንዲት ቤተ ክርስቲያን አለችው ። ሙሽራይትም አንድ ሙሽራ አላት ፣ ቤተ ክርስቲያንም አንድ ጌታ አላት ። ሙሽራ ሲመጣ ዜማው በሩቅ ይሰማል ፣ ጌታችንም የመምጣቱ ደወል እየተሰማ ነው ። ሙሽራ ሙሽራይትን ከወላጆችዋ ቤት ወስዶ ወላጅ ይሆናታል ፣ ጌታችንም ቤተ ክርስቲያንን ከምድራዊ ኑሮ ፣ ከሥጋ ስሌት አድኗታል ። ሙሽራ ሙሽራይቱን ይቀልባታል ፣ ጌታችንም ቤተ ክርስቲያንን ለምትበይው ለምትጠጭው አትጨነቂ ብሏታል ። ሙሽራ ጓዙን አስቀድሞ እርሱ ይመጣል ፣ ጌታችንም የዘመን ምልክቱን አስቀድሞ ይመጣል ። ሙሽራ ሙሽራይትን ያበላል ፣ ጌታችንም ሥጋና ደሙን ለምእመን ሰጥቷል ።
የመንፈሳዊ ዕድገት ልኩ ክርስቶስ ነው ። እንደ እገሌ ሳይሆን ክርስቶስን ለመምሰል ተጠርተናል ። ክርስቶስን የምንመስለው በአምላክነቱ ሳይሆን አርአያ ሁኖ ያሳየንን የኑሮ ልክ ለዓለም መግለጥ አለብን ። ለዚህች ዓለም ተጨማሪ ችግር ሳይሆን መፍትሔ ልንሆን ይገባናል ። ለጨለማው ዓለም ብርሃን ፣ ለአልጫው ዓለም ጨው አድርጎናል ። እርሱ አባቱን ለማክበር እንደኖረ እኛም ለእርሱ ክብር መኖር አለብን ። ሕይወታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚያመጣ መሆን አለበት ። በሠራናቸው ጥቃቅን መልካምነቶች የምንረካ ከሆነ የዕድገታችን ልኩ ክርስቶስ ነውና እስከ ዘላለም በዕድገት ውስጥ ነን ። መቼም ቢሆን ክርስቶስን አንመስልምና ። ክርስትና ሁልጊዜ ተማሪነት ፣ ሁልጊዜ ነዋሪነት ነው ። ወደ ዕድገት የምንወጣበት መሰላልም እውነትን በፍቅር መያዝ ነው ። እውነትን በፍቅር ስንይዝ መሆን ያለብንን እየሆንን እንመጣለን ።
እኛ ሁላችን የአካሉ ክፍል ስንሆን እያንዳንዳችን የአካሉ ክፍልፋይ ነን ። በአንድ ራስ ሥር ፣ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉ ። የተለያየ ስም ፣ ክፍል ፣ ግብር ያላቸው የአካል ክፍልፋዮች በራሱ አንድ እንደሆኑ እኛም በክርስቶስ አንድ ነን ። እጅ የእጅነት ድርሻን ሳይጨነቅም ሳይሳነፍም መያዝ ግዴታው ነው ። ሁሉም የልኩን ከሠራ ተግባር ሙሉ ይሆናል ። ጅማትም አካልን እንደሚያስተሳስር ፣ የአካልም ሕያውነት በጅማቱ በሚመጣው የተጣራ ምግብና አየር ሕያው እንደሚሆን የምእመናን ማስተሳሰሪያው የተመሠረቱበት እውነትና የሚያድጉበት ፍቅር ነው ። ተነጣጥሎ የሚኖር የአካል ክፍል የለም ፤ አንድ ጡብ ያለ ሌላው በራሱ ቤት መሆን አይችልምና ኅብረት ያስፈልገናል ። በክርስትና ኅብረት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው ።
ሐዋርያው፡- “ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል ።” ይላል ። ቤተ ክርስቲያን በአካል ፣ በሙሽራይት ፣ በሕንጻ ተመስላለች ። ሕንጻ ከመሠረት እስከ ጉልላት የራሱ የሆኑ ሂደቶች አሉት ። ቤተ ክርስቲያንም በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻ እስከ ምጽአት ድረስ በነፍሳት ጡብነት ታድጋለች ። ወታደር በጀግንነቱ ፣ ገበሬ በምርቱ ፣ መምህር በትምህርቱ ሲታወቅ ክርስቲያን የሚታወቀው በፍቅር ነው ። መታወቂያውን የጣለ ሰው እንኳን ለኑሮ ለቀብርም አስቸጋሪ ነው ። ፍቅርን የጣለ ክርስቲያንም በኀዘን ኖሮ ፣ በፍርሃት የሚሞት ነው ።
ፍቅር ቀዝቅዞ ፣ ኅብረት ወደ ቡድን ተለውጦ ፣ አብሮ የጸለየ ተራርቆ እየተወራወረ ፣ አብሮ ያስቀደሰ በዘር በቋንቋ እየተናቆረ ነውና እውነትን በፍቅር ለመያዝ ጊዜው አሁን ነው ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም.