“ቀሚሱ ዕጣ ሲጣልበት ፣
ተገፎ ዓለም አጌጠበት ።”
ለሕይወት ትርጉም የለሽ መሆን የዘመናችን ፈተና ነው ። ረሀቡ ረሀብ ሲሆን ዳቦ ጥጋቡ ነው ፣ ጥጋቡ ረሀብ ሲሆን ግን መጥገቢያው ምንድነው ? አህያ ጭነትን ፣ ፈረስ ሰውን ቢሸከሙ ግድ ስለሆነባቸው እንጂ ስለፈለጉ አይደለም ። ግድ ስለሆነበት የሚኖር ፣ ግድ ስለሆነበት በሥልጣን የሚቆይ ብዙ ነው ። ሊያስተውለው ባልቻለው ድባቴ ውስጥ ገብቶ እያንዳንዱ ቀን ተራራን መግፋት የሆነበት ብዙ ወገን አለ ። ሁሉም በራሱ ችግር ስለተወጠረ ጎረቤቱን ማስተዋል አልቻለም ። “ዛሬ ፊትህ ጥሩ አይደለም ፣ እንቅልፍ ተኝተሃል ወይ ? ምግብ በልተሃል ወይ ?” የሚሉ ጥያቄዎች የሰው ልጆች መዋከብ ውስጥ ሳይገቡ የነበሩ ናቸው ። ተጨናቂው ጥቂት ስለ ነበር ብዙኃኑ ይታደጉታል ። ያለፈው ዘመን ቸገረኝ እንጂ ጨነቀኝ የሚል አልነበረም ። ችግር የአቅርቦት እጥረት ሲሆን ጭንቀት ግን አጥተውም አግኝተውም የሚገጥም የሕይወት ጥያቄ ነው ። አዎ ከፍ ባሉ ቍጥር አየር ያጥራል ። የቤቱ ገቢ ፣ የኑሮው ደረጃ ፣ የውሎው መሰላል ከፍ ባለ ቍጥር ጭንቀቱም አብሮ ከፍ ይላል ። ለነገሮች ትርጉም ማጣት የያዙትን ነገር በዋጋው ማየት አለመቻል ፣ ልጣለው ልያዘው የሚል ማመንታት ውስጥ መግባት ነው ። ብዙ ሰዎች በትዳራቸው ላይ ረባሽ የሚሆኑት የተሻለ ፍለጋ ውስጥ ገብተው ሳይሆን ትርጉም የለሽነት ፈተና ሆኖ ስለመጣባቸው ነው ።
ሰውዬው ርቦት የሚጠግብ ስላልመሰለው በሬ አረደ ። ትንሽ እንደ ጎረሰ ጠገበ ። “ለዚህ ነው ወይ በሬዬን ያረድሁት(” አለ ይባላል ። በሕይወት ውስጥ የሚያስፈልገው ጥቂት ፣ የምንጨነቀው ግን ብዙ ነው ። በዚህ ዘመን አንድ እንጀራ በቅጡ የሚጨርስ ሰው ጥቂት ነው ። ለመሰብሰብ ያለን ፍላጎት ግን ብዙ ነው ። ገንዘብን የሕይወት ዋስትና ስናደርግ የሰበሰብነው ነገር ራሱ ያውከናል ። ገንዘብ ለሚገዛለት ክፉ ጌታ ነው ። በእጃችን ያለው ክቡር ነገር ቢሆን እንኳ ጥቅሙ ምን መሆኑን ካላወቅን በረከት አይሆነንም ። ማሩ የመረራቸው ፣ ወተቱ ጥቁር ሁኖ የታያቸውን መመለስ ከባድ ነው ። ለነገሮች ትርጉም ማጣት የኖሩበትን ዘመን በዜሮ ማባዛትን ያመጣል ። ወደፊት እኖራለሁ የሚል ተስፋን ያሟጥጣል ። ከሁሉ በላይ መኖር አለመፈለግን ይከስታል ። ትርጉም ያግባባል ። ብዙ ዋጋ ከሚያስከፍሉ ቢሮዎች አንዱ የትርጉም ሥራ የሚሠሩ ናቸው ። ትርጉም ሕጋዊነትና ተጠያቂነት ባላቸው ሰዎች የሚሠራ ነው ። ትርጉሙን የጠየቀው ወገንም በእምነት ይቀበላል ። ሕይወት ይህን አስተርጉመህ አምጣ ስትለን ውድ ዋጋ እንከፍላለን ። ገንዘብን ፣ ትዳርን ፣ ልጅን ፣ ሥልጣንን አስተርጉመህ አምጣልኝ ስትለን ግራ እንጋባለን ። ትርጉሙን ለማግኘት እግዚአብሔር የሰጠንን ሰዎች ማክበር አለብን ። እግዚአብሔር በሰዎች በኩል እንደሚናገር ማመን ያስፈልጋል ። ብሉይና ሐዲስ በነቢያትና በሐዋርያት የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው ። ትልቁ ችግራችን ሰዎችን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ክብር መግፈፍና እግዚአብሔር ያልሰጣቸውን ክብር ማልበስ ነው ።
ለጥያቄዎቻችን መልስ የሚሰጡን የተሟላ እውቀት ያላቸው ሰዎች ሊሆኑ ይገባቸዋል ። በምድር ላይ ስለቆዩ ሰዎች የሕይወት አማካሪ ፣ በትዳር ውስጥ እያለፉ ስለሆነ የትዳር አስተማሪ መሆን አይችሉም ። ብዙ ጊዜ ስለታመመም በሽተኛ ሐኪም መሆን አይችልም ። እነዚህ መጠነኛ መረጃ ይሰጡናል ። እውቀትን ግን ከምንጩ መቅዳት ያስፈልገናል ። ትክክለኛውን ትርጉም የሚሰጡን ፣ ሕልማችንን በቅንነት የሚፈቱ ሰዎች ያሹናል ። መንገደኛን ሳይሆን ነገም ልናማክራቸው የምንችላቸውን መምህራን መፈለግ ተገቢ ነው ። የሕይወት ጥያቄ መልሱን ሲያገኝ ወዲያው ይታገሣል ። መልሱ የተገኘለት ጥያቄ ደግሞ ላይመጣ ይችላል ። ሕይወት በሌላ ጥያቄ እስክንገናኝ ደኅና ዋሉ ብላ ትሄዳለች ።
ለሕይወት ትርጉም ማጣት ሲገጥማችሁ አትደንግጡ ። ይህ ስሜት ታላላቅ የሚባሉ የእግዚአብሔር ሰዎችም ተሰምቷቸዋል ። ነቢዩ ኤልያስ፡- “ይበቃኛል አሁንም ፥ አቤቱ ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ” ተብሎ ተጽፎአል ። 1ነገሥ. 19 ፡ 4 ። ነቢዩ ኤልያስ በረሀብና በጥማት ዘመን ፣ በብቸኝነትና በመደበቅ ወራት ይህን አላለም ። የእግዚአብሔርን ክብር ፣ ታላቁን ክንድ ካየ ፣ አእላፋት የሚሆኑ ሕዝቦች ካመኑ ፣ ንጉሡም ለእግዚአብሔር እጁን ከሰጠ በኋላ ኤልያስ በትንሽ ነገር ያውም በዛቻ ልቡ ፈራ ። ስደት ጀመረ ፣ ሞትን ለመነ ። ትርጉም ማጣት ከስኬት ማግሥት የሚጀምር ነው ። ነጻነትና ስኬት ማስተዳደር ይፈልጋሉ ። መድኃኒቱ ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስን መመገብ ፣ በጸጥታ የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት ነው ። ነቢዩ ኤልያስ ነፋስ ፣ የምድር መናወጥ ፣ እሳት ገጥሞት ነበር ። በዚህ ውስጥ እግዚአብሔር አልነበረም ። በትንሽ ዝምታ ውስጥ ግን እግዚአብሔር ነበረ ። ለሕይወት ትርጉም ማጣት በገጠመ ጊዜ የዜና ጣቢያዎችን ፣ አዋኪ ሰዎችን ፣ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን መቀነስ ይገባል ። ቃሉን መተገን ጎርፉ እንዳይወስደን ይረዳናል ።
“ተስፋ የሕይወት ማቆያ ናት ።” ተስፋ የሕይወት መደለያ አይደለችም ። ተስፋ አምላክ አላት ። ተስፋ ነገን ማያ መነጽር ናት ። ስለዚህ ተስፋ አድርጉ ። ትላንትም ዛሬም ነገም ጨለማ ሆኖ ሊታያችሁ ይቻላል ። ዘመኔ ተቃጠለ የሚል ስሜት ፣ ነገን ለመድረስ ፍላጎት ማጣት ይገጥማል ። እኛ በእኛ ላይ የሚታየን ነገር ባይኖር እንኳ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያየው ነገር አለ ። እኔም እንደ እናንተ የማይገቡኝ ነገሮች አሉ ። ሁሉን እንዳውቅ ሆኜ አልተፈጠርኩምና አንተ ታውቃለህ ብዬ ማረፍ አለብኝ ። እናንተ ስለዘገያችሁ ላልወልድ ነው ወይ ? ብለው ወላጆቻችሁ ሰግተው ነበር ። እናንተ እንድትወለዱ ብዙ ስእለት ቀርቦባችኋል ። ስትወለዱ እልልታ ተሰምቷል ። በእናንተ ምክንያት ድግስ ተደግሷል ። እንቅልፋችሁን የማያምኑ የሚወዱአችሁን አግኝታችኋል ። ሰው ጥሏችሁ በሌላ ሰው እግዚአብሔር አንሥቷችኋል ። በነጻ አልኖራችሁም ፣ ብዙ ዋጋ ተከፍሎላችኋል ። በሰውነት የመላው ዓለም አባል ፣ በዜግነት የአንዲት አገር መዝገብ የሚያውቃችሁ ፣ በዝምድና ከእገሌ ቤተሰብ የተወለዳችሁ ፣ በልጅነት የእገሌ ልጅ ናችሁ ። ባለ ብዙ ቅርንጫፎች ፣ ሥራችሁ ሲመዘዝ ዳዊት አብርሃም ላይ የሚደርስ ፣ ከአዳም ጋር ተፈጥራችሁ በዚህ ዘመን የተገለጣችሁ ዕንቈ ናችሁ ። ጌታ እያለ እናንተን ማንም አይነካችሁም ። የሚዋጋላችሁን ጠላት አይችለውም ። ፊታችሁ ይብራ ፣ አሸናፊው ጌታ ከፊት ወጥቶላችኋል ።
ብርድ ብርድ አይሰማችሁ ፣ ክርስቶስ የተራቆተው እናንተ እንዲሞቃችሁ ነው ።
ቀሚሱ ዕጣ ሲጣልበት ፣
ተገፎ ዓለም አጌጠበት ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም.