እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ 2016 ዓ.ም. ወደ ዘመነ ማቴዎስ 2017 ዓ.ም. በሰላምና በጤና አሸጋገራችሁ!
“ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ፥ ከንጹሕም እንስሳ ሁሉ ከንጹሐን ወፎችም ሁሉ ወሰደ፥ በመሠውያውም ላይ መሥዋዕትን አቀረበ።” (ዘፍ. 8 ፡ 20 ) ።
ዛሬ ላይ ያለው መላው የዓለም ሕዝብ ተደምስሶ ፣ እንስሳቱ ከዝርያ በቀር ሁሉም አልቀው ፣ እጽዋቱ ተጎሳቁለው የእኛ ቤተሰብ ብቻውን ቢተርፍ ፣ የቤተሰቡም ብዛት ስምንት ብቻ ቢሆን ምን ይሰማናል ? ኖኅ የገጠመው ስሜት እንዲህ ያለ ነበር ። የቅርብ ዘመዶቹ ፣ ጎረቤቶቹ ፣ የአገር ልጆች ፣ የዓለም ሕዝቦች የሉም ። ያለው ፣ የተረፈው ቤተሰብ የእርሱ ብቻ ነው ። ያለው የተረፈው የአገር ዜጋ የእርሱ ቤተሰብ ብቻ ነው ። ያለው የተረፈው የዓለም ሕዝብ የእርሱ ቤተሰብ ብቻ ነው ። ይህም ቤተሰብ የተረፈው በብልሃት ሳይሆን በእምነት ነው ። በብልጠት ሳይሆን በመታዘዝ ነው ። በማልመጥ ሳይሆን በደስታ ለእግዚአብሔር በመገዛት ነው ። በከተማው ላይ ይሰማ የነበረው የየቀኑ ጭፈራ ዛሬ የለም ። ጨፋሪዎቹም ፣ የጭፈራ ቦታዎቹም የሉም ። የትልልቅ ሰው ቤቶች ፣ ለመግባት ፈቃድ የሚጠየቅባቸው የተቀጠሩ ሰፈሮች ዛሬ የሉም ። እነዚያ የጌቶች ዘበኞች ራሳቸውንም አዛዦቻቸውንም ማትረፍ አልቻሉም ። እልቂቱ ከቃል በላይ ነው ። እልቂቱ የምጽአት ያህል ነው ። መትረፉም ከዚህ በላይ ያስደንቃል ። ኖኅ ሰባኪም ነበርና አስቀድሞ የንስሐ ስብከት አሰማ ፤ ሁሉም የሰውን መደሰት የማይወድ ምቀኛ አድርገው ሳሉት ። የተቃወሙት ግን ዛሬ የሉም ። ያሸነፉ የመሰላቸው ለዘላለም ተሸንፈዋል ። አርደው የሚበሉ ፣ ገድለው የሚዘርፉ እንኳን መኖሪያቸው የቀብር ስፍራቸው አልታወቀም ።
ከብዙ ስደትና ስጋት ውስጥ ተርፈው የሚመጡ ወገኖቻችን ገና ከአውሮፕላን ሲወርዱ በጉልበታቸው ወድቀው መሬቱን ይስማሉ ። ኖኅ ከመርከብ ሲወርድ ምን ተሰምቶት ይሆን ? እግዚአብሔርን ካላሰበ በቀር መጽናናት አይችልም ። ከወራት በፊት የነበረው ያ ሁሉ ጫጫታ ዘላለማዊ ጸጥታ ወርሮታል ። የሚያጋፉ መንገዶች ዛሬ ጭር ብለዋል ። መላው ዓለም በስምንት ቤተሰብ እጅ ወድቋል ። የሚገርመው ከዚህ መዓት ተርፎ ኖኅ በስካር ወደቀ ። የሚገርመው ጥቂት ሳሉ ካም አባቱን ለማዋረድ ተነሣሣ ። አይቶ እንዳላየ መኖር ከባድ ነው ። ያለፈው መከራ ፣ የደረሰው እልቂት ከመናገር በላይ ነው ። ከዚህ የተረፈ ይመንናል ፣ በጽድቅ ይኖራል እንጂ ይበድላል ተብሎ አይታሰብም ። ሰው ግን ከባድ ነው!
ኖኅ የእግዚአብሔርን ማዳን አየ ። ዳግማዊ አዳም ሁኖ በእርሱ ቤተሰብ የዓለም ሕዝብ እንደገና ጉዞ ሊጀምር ነው ። በእነዚያ ቀናት በመርከብ ውስጥ ሁኖ ከመርከቡ ውጭ ያለ ወገን ሲያልቅ እያየ ነው ። መርከቡን ለመያዝ ሲሞክሩ እየራቃቸው ያለቁት ሕዝቦች በዓይኑ ላይ አሉ ። በመርከቡ ውስጥ ዛሬ የምንፈራቸው አራዊት ሁሉ ነበሩ ። እያንዳንዱ ቀን የሺህ ዓመት ያህል ረጅም ነበረ ። ኖኅ ግን ልቡን በእግዚአብሔር አበረታ ። በዚያች መርከብ ካፒቴን ፣ አባወራ ፣ ካህን ፣ ንጉሥ ነበረ ። መርከብ ሁሉ መድረሻ ቦታ አለው ፣ የኖኅ መርከብ ግን ተጓዥ ሳትሆን ለማዳን ብቻ የምትንሳፈፍ ናት ። በመርከቡ ውስጥ ሕይወት አለ ፣ ከመርከቡ ውጭ ግን ሞት ነበረ። ሰማይ ጠቀስ ፎቅ የሠሩም አልተረፉም ። ዛሬ ላይ የሚረዳው የኖኅ እምነት ብቻ ነው ። ይህች መርከብ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት ። “ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ድኅነት የለም ።” “ቤተ ክርስቲያን እናት ያልሆነችው እግዚአብሔር አባቱ አይደለም” የሚባለው ጽኑ ምሥጢር ነው ። ኖኅ ከመርከቡ ሲወርድ ሬሳ ለመቍጠር ፣ ቤት መሥሪያ መሬት ለማስተካከል አልቸኮለም ። የወደመው የእርሱም የዘመናት ሀብት ነው ። ሕይወቱን አትርፏልና ለንብረት አልተጨነቀም ። ኖኅ ግን ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት ለማቅረብ መሠዊያ ሠራ ። ለንጹሑ እግዚአብሔር ንጹሕ መሥዋዕት ለማቅረብ ተጋ ።
ከብዙ ሞት አምልጠን ፣ ከማይታየው ስውር መጥመድ ተጋርደን ፣ ከሚንበለበለው ፍላጻ ተሰውረን ዛሬን ያየን ነን ። ይህች ቀን ኖኅ የሚታሰብባት ፣ ከመርከብ የወረደባት ቀን ናት ። ያለፈው ጊዜ አይደገም የሚባል ብዙ ሰቆቃ የታየበት ፣ ወገን እንደ ቅጠል የረገፈበት ፣ ራብ ቤተኛ ሁኖ አልወጣም ያለበት ፣ ወንድም በወንድሙ የጨከነበት ነው ። ብዙዎች አልፈው እኛ ተርፈናል ። ብዙዎች አልቀው እኛ ቆመናል ። ለእግዚአብሔር ንጹሕ መሥዋዕትን ልናቀርብ ይገባል ።
መርገጫ በታጣበት ፣ እናት የልጇን ጩኸት በማትሰማበት ፣ አንዱ አንዱን እንዳይረዳው ሁሉ በተቸገረበት ዘመን የምታሻግር የኖኅ አምላክ ስለዚህ ቀን ፣ ስለዚህ አዲስ ዘመን እናመሰግንሃለን ። ከብዙ ጥፋት ያመለጥን ነንና እናከብርህ ዘንድ እርዳን ! እነዚያ ለምን ሞቱ ? ሳይሆን እኛ ለምን ኖርን ? ብለን እንድንጠይቅ እርዳን ! ለሞቱት ዕረፍት ፣ ለእኛም ኅብረት ስጠን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም.