መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የተሰበረ ልብ

የትምህርቱ ርዕስ | የተሰበረ ልብ

መስተዋት ሲሰበር አንዱ ሰው ሁለት ሆኖ መታየት ይጀምራል። ልብ ሲሰበር ሥጋን ብቻ ሳይሆን ነፍስንም ማየት ይቻላል። የናርዶስ ሽቱ ብዙ ጠባያት ነበሩት። ውድ ነው፣ ይህን ሽቱ ለመግዛት ዓመት ሙሉ ጠንክሮ መሥራት ይገባል። የናርዶስ ሽቱ ለውድ ወዳጅ የሚሰጥ ነው። ሦስተኛውና የሚገርመው ይህ ሽቱ ከተከፈተ በኋላ ለሌላ ሰውና ለሌላ ጊዜ መሆን አይችልም። ልብ ሲሰበር እንደ ናርዶስ ሽቱ ነው። ሌላ ነገር ማሰብ እስከማይችል መንፈሳዊ ይሆናል። የዓለምን ከንቱነት ፣ የእግዚአብሔርን ብርቱነት ማሰብ ይጀምራል:: ከእግዚአብሔር ብርታት ተነሥቶ ዓለምን መናቅ በውስጡ ተስፋ አለው። ከፍልስፍና ተነሥቶ ዓለምን መናቅ ግን የእግዚአብሔርን ብርታት አያሳይም፣ በጨለማ ላይ አፍጥጦ መቅረት ነው።

ልብ በእግዚአብሔር ፍቅር ሲሰበር ዓለም ጠፊ ፣ ክብሩም ኃላፊ፣ ውበቱ ረጋፊ ፣ ጸጋ እግዚአብሔር ሰፊ መሆኑን ይረዳል። የናርዶስ ሽቱ ሲሰበር መዓዛው ሁሉን ያውዳል። የተሰበረ ልብም ጣዕም አለው። ሰው ራሱን የሚቀበልበት፣ የራሱን ልክ የሚረዳበት ነው፣ ከአዋኪው ዓለም የሚወጣበት፣ ሰላማዊነትን የሚላበስበት፣ ትሕትናን ጌጥ የሚያደርግበት ነው።

የተሰበረ ልብ ውበትን ያላብሳል። የሰውን ልጅ ከመልአካዊ መልክ ወደ አራዊታዊ መልክ የሚለውጠው ትዕቢት፣ ጭካኔ ፣ ፍቅረ ንዋይ ነው። የተሰበረ ልብ መንቀዥቀዥን፣ ስግብግብነትን፣ ስስትን ይጸየፋል። ብዙ  መጸለይ፣ ስለ እግዚአብሔር ማውራት፣ የዓለምን ሴራ መናቅ  ያገኛል። የተሰበረ ልብ የሌሎችን ሕመምና ስቃይ መካፈል ይችላል። የሚያስደስተውም ወደ ተጎዱት ዘንድ መሄድ ነው ። ከጉልበተኞች፣ በገንዘባቸው ከሚያስቡ ግብዞች ይርቃል፣ ዓለም የነቀፈቻቸውን ይፈልጋል። የተሰበረ ልብ እንደ እነ  እገሌ አገኛለሁ ሳይሆን እንደ ታመሙት ልታመም፣ እንደ ታሰሩት ልታሰር እችላለሁ ብሎ ቀን ለጎደለባቸው አገልጋይ ይሆናል።

የተሰበረ ልብ ከቅዱሳን ጋር ባለኅብረት የሚያደርገን ነው። ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት ነው። በዚህ ሸምበቆ ማንነት መኩራትን ፣ በዚህ የጠዋት ጤዛ በሆነ ዓለም መተማመንን ያቆማል። እግዚአብሔርና ቃሉ ዘላለማዊ መሆናቸውን ያምናል። የተሰበረ ልብ በተለያየ መንገድ ገንዘብ ይሆንልናል።

ዕለተ ዓርብን በዓመት አንድ ጊዜ ሳይሆን በየቀኑ መኖር ይገባል። የስቅለት ቀን መታሰቢያ ናት፣ ክርስቲያን ግን ከቀራንዮ ፍቅር ጋር ስቁል ሆኖ የሚኖር ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር ፣ የመስቀሉ ዋጋ ሲገባን የተሰበረ ልብ ይኖረናል። ክርስትናን ሆያ ሆዬ ያደረጉ ወገኖች ስለ ትንሣኤ እንጂ ስለ ሞቱ ማሰብ አይፈልጉም። ሞት በሌለበት ትንሣኤ የለም። መዳናቸውን ቀምተው መሮጥ የሚፈልጉ እንዴት እንደ ዳኑ ፣ ለምን እንደ ዳኑ መስማት አይፈልጉም። ብዙዎች ጥቅማቸውን ይከተላሉ። ጸጋው ግን የሚገኘው ባለ ጸጋውን በመያዝ ነው ። ክርስቶስን ሳይሆን ደስታቸውን የሚያመልኩ ይዘላሉ፣ ይጨፍራሉ እንጂ ተመሥጦ ፣ የእንባ ሕይወት የላቸውም። መዝሙርን የዘፈን ልዋጭ ያደረጉት ብዙዎች ናቸው። መስቀል አልባ ክርስትና የሚያወሩ አንታመምም ፣ አናጣም የሚሉ ወደ ልብ መሰበር መምጣት አይችሉም።

የእግዚአብሔር ውለታው ሲበዛብን፣ ምን ውዬለት ነው ይህን ሁሉ ያደረገልኝ ? ስንል፣ ጸሎታችን ሲመለስ ስእለታችን ሲደርስ የልብ መሰበር ፣ ቅዱስ ትሕትና ይገዛናል። በታላቅነቱ ፊት ስንቆም ራሳችን ያንስብናል። ግን የበታችነት ስሜት አይሰማንም፣ ሰማይ የከበበን ሆኖ ይሰማናል።

የንስሐ መንፈስ ሲቆጣጠረን እንጸጸታለን፣ ለኃጢአት ያዋልኩትን ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ ለእግዚአብሔር ልስጥ ስንል  የንስሐ ፍሬ እናፈራለን። ቅዱስ ፍርሃትም ይቆጣጠረናል።

የታመው፣ የታሰሩ፣ የተቸገሩ ሰዎችን ስንጎበኝ የተሰበረ ልብ እናገኛለን። ራሳችንን በቅጡ እናየዋለን፣ ሰው ደካማ መሆኑን ፣ ሲያዝ ጭብጥ እንደማይሞላ እንማራለን። ነግ ለእኔ ብለን እንጠነቀቃለን። ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን ማለትም ብራብ አብልታችሁኛል — ብታመም ጠይቃችሁኛል የሚሉትን በየዕለቱ መፈጸም የተሰበረ ልብን ያስገኛል።

ሰዎች በጉዳት ፣ በኀዘን ፣ ተስፋ በመቁረጥ ልባቸው ሊሰበር ይችላል። እየተማርን ያለነው የልብ መሰበር ግን የራስን፣ የዓለምን፣ የሰማይን እውነት በመረዳት የሚገኝ ነው። ጉዳታችን ከክርስቶስ የመስቀል ውሎ አይበልጥም። ተስፋ ትንሣኤን ስለምናምን ስለሞቱት እያዘንን አንኖርም። ቅዱስ ዳዊት ንስሐ በገባ ጊዜ ይህን የተሰበረ ልብ አገኘ ። ጾምም የተሰበረ ልብ መገኛ ነው።

የተሰበረ ልብ ሲኖረን በጣም ማማር እንጀምራለን። ሰዎች ከእኛ ጋር ሲያወሩ ይረጋጋሉ። ቤታችን ሰላማዊ ይሆናል፣ ባለንበት ስፍራ ሁሉ የእግዚአብሔር መገኘት አካባቢውን ያውደዋል። ሰዎች አይተው ያውቁናል፣ ፍቅራችን ለሁሉ ይሆናል። የጭንቀት ጉልበት ይሰበራል፣ የመጣውን ለመቀበል ጨካኝ እንሆናለን። ሞትን በደስታ እንጋፈጣለን።

የተሰበረ ልብ የሚያስፈልገን እግዚአብሔር ከትዕቢት ጋር ኅብረት ስለሌለው ነው። ጥበብ ፀጥታ ትፈልጋለች ፣ የተሰበረ ልብ ውስጣችንን ለማየት ያግዛል። ለብዙዎች አርአያ ለመሆን የመስቀልን መንገድ መምረጥ ይገባል። በልጅነት እውቀታችን እንኳ ከተቀማጠሉት ይልቅ የተጎዱት አገልጋዮች ይማርኩን ነበር። መስቀል ውበት ነው። የአገልግሎት መዳረሻው ሀብታም ማግባት፣ አሜሪካ መሄድ፣ ሀብት መያዝ አይደለም። ሰማዕታት ዕድሜአቸው አጭር ፣ ሥራቸው ረጅም ነው። ቂርቆስ፣ ጊዮርጊስ፣ እስጢፋኖስ…ዕድሜአቸው አጭር ነው። እውነት መናገር ዕድሜ ያሳጥራል። ዕድሜአችን የረዘመው ስለምንዋሽ ነው። የተሰበረ ልብ ለእውነት ይጨክናል።

እግዚአብሔር ከብርና ከወርቅ ስጦታችን በላይ የተሰበረ ልብ ደስ ያሰኘዋል፦ “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” ተብሏል (መዝ .50፥ 17)።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 8 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ