ልክ እንደ ተወጠረ ቍስል ፣ እንዳልተበጣ እብጠት ፣ የቆሸሸው ነገር እንዳልፈሰሰ ውጥረት ፣ መራመድ እንደሚከለክል ንፍፊት የታመቀ ስሜትም እንዲሁ ነው ። እየተራመዱ ድንገት ጉዞ እንደሚያስቆም ፣ ሰላም እየተወራ በመሐል አስጩኾ እንደሚያስደነግጥ እባጭ የታመቀ ስሜትም እንዲሁ የሕይወትን ጉዞ ይገታል ። የጀመሩትን ነገር ላለመጨረስ ምክንያት ይሆናል ። ራስን በትክክለኛነት ስሜት እየሞላ ሰው ሁሉ ጥፋተኛ ነው ያሰኛል ። በልብ ኀዘንን ፣ በዓይን እንባን ይሞላል ። ለማልቀስ ሰዋራ ቦታን ይፈልጋል ። የታመቀ ስሜት ይወጥራል ። ለመቆም ለመቀመጥ ፣ ለመኖር ለመሞትም መንታ አሳብ ላይ ያውላል ። የታመቀ ስሜት ሕመም አለው ። ፍቅርም ሆነ ጥላቻም ሲታመቅ ሁለቱም እኩል ሕመም አለው ። ጉዳትም ሆነ እልልታ ሲታፈን ሁለቱም ጭንቀት ያመጣል ። ጸሎትና ምስጋና ለልቅሶና ለእልልታ ዘመን የተዘጋጁ ማስተንፈሻዎች ናቸው ። ኀዘንም ደስታም ሁለቱም አጋር ፣ ተባባሪ-ወዳጅ ይሻሉ ። የታመቀ ስሜት እብጠቱ ለሰው ባይታይም ለባለቤቱ ግን የተራራ ያህል ይሰማዋል ። ውስጡን የመረዘው ፣ ሊወገድ ሲገባው አብሮት ያለው ክፉ ስሜት የነፍስ ሲቃ ውስጥ ይከተዋል ። ማንም በሌለበት ከራሱ ጋር እንዲያወራ ያደርገዋል ።
በክፉ አስተዳደግ ፣ በባሕል ተጽእኖ ፣ ድንበሩን አልፎ ሰውን በሚያጠቃ ማኅበረሰብ መካከል ማሳለፍ ፣ በአጉል የሕይወት ምርጫ ፣ ማንም ሰው ያለሁበትን ሁኔታ ሊፈርድ እንጂ ሊያውቅልኝ አይችልም የሚል አስተሳሰብ የታመቀ ስሜት ይመጣል ። የታመቀ ስሜት ከልጅነት እስከ ወጣትነት ፣ ከወጣትነት እስከ ሽምግልና እንደ-ታፈነ ሊኖር ይችላል ። ዕድሜውን የሚያሳጥረው የዓለምን እውነታ መረዳት ነው ። የታመቀ ስሜት የምንወደውን ነገር እያሰብን ፣ ከማንወደው ጋር እንድንኖር የሚያደርግ ነው ። ለምሳሌ፡- በታመቀው ስሜት ፍቅራቸው ከእገሌ ጋር ነው ። አሁን ግን በትዳር የሚኖሩት ያንን ሰው እያሰቡ ከሌላ ሰው ጋር ነው ። አንዳንዴ ከልባችን ሳንሆን መንገዱን በትክክል እንሻገራለን ። ባልነቃ አእምሮ ተግባራችንን እናከናውናለን ። በዚያ በታመቀ ስሜት ጡዘት ውስጥ ሁነው ሌላ ኑሮ የሚመሠርቱ ፣ በአሳብ ከሌላ ጋር በተግባር ደግሞ ከሌላ ጋር የሚኖሩ አሉ ።
የታመቀ ስሜት እያመሳሰለ መኖር ይወዳል ። የሚወደውን ሰው በሞትና በሌላም ነገር ስላጣ ያንን ወዳጅ የሚመስል ሰው ሲያገኝ ያንን ሰው በነጻ ይወደዋል ። የሄደው ሰው የጎዳው ቢሆን እንኳ ለዚያ ሰው የነበረውን የቀደመ ፍቅር እያሰበ ሌላ ሞክሼውን ሲያገኝ ይወደዋል ። ልጄን ይመስላል ተብለው በነጻ የሚወደዱ ሰዎች እንዳሉ ማለት ነው ።
ካለ መናገርና የሚመስልን ሰው ካለ ማግኘት የተነሣ የታመቀ ስሜት ዕድሜው እየረዘመ ይመጣል ። ለመንፈሳዊ አባት ወይም ለሥነ ልቡና አማካሪ በተገቢው መንገድ መተንፈስ ከውስጥ የነበረው አዋኪ ነገር የሚወጣበት መንገድ ነው ። ያንን ለማድረግ ያልተመቸው ደግሞ በጸሎትና በእንባ በእግዚአብሔር ፊት መናዘዝና ማልቀስ ትልቅ መፍትሔ ነው ። ከሁሉ በላይ በዚያ ስሜት ውስጥ የሚያልፍን ሰው ማግኘት ልብን ይፈውሳል ። ስሜቴን የሚረዳልኝ ሰው አገኘሁ ማለት ነፍስን ከሞት መንገድ ይመልሳል ። ጌታችን ከኃጢአት በቀር የእኛን የሕይወት ትግል በፈቃዱ የተቀበለው ፣ የሰው ልብ “እንደ እኔ የተፈተነ ነው” በማለት የስሜት አጋሩን በማግኘት ፈውስ ስለሚያገኝም ነው ። እርሱ ስሜታችንንም ሊያድን ወደ ምድር መጥቷል ። የከበረው ሐዋርያ፡- “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም” ብሏል ። ዕብ. 4፡15።
ችግራችንን እንዲያርቅ እንለምነዋለን እንጂ ችግራችን እንዲገባው አናስረዳውም ። እርሱ ሁሉንም ያውቀዋል ። የታመቀ ስሜት ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች የሚፈርድባቸውን ፣ የሚያጣጥላቸውን ሰው በፍጹም አይፈልጉም ። እጸልይልሃለሁ የሚላቸውን ሳይሆን የሚያዳምጣቸውንና በእግር ጫማቸው ውስጥ እግሩን ከትቶ የሚረዳቸው ሰው ይፈልጋሉ ። የታመቀ ስሜት ያላቸው ሰዎች ከትዳር አጋራቸው ፣ ከቅርብ ዘመዳቸው ፣ ከወላጆቻቸው ይልቅ ያሉበትን ሁኔታ ያወቀላቸውን መንገደኛ በጣም ሊወዱና እንደ ንስሐ አባታቸው ሊያዩት ይችላሉ ። የታመቀ ስሜት የተለያዩ መነሻዎች አሉት ።
ይቀጥላል