“እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል ።” (መዝ. 145 ፡ 7) ።
ሳዑዲ ዐረቢያን ላለፉት ዘጠና ዓመታት ከአያት እስከ ልጅ ልጅ እያስተዳደሯት ነው ። የአሁኑ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ለየት ያለ ሰብእናና ውሳኔ ሲያደርጉ ይታያሉ ። በ32 ዓመታቸው አባታቸውን የተኩት ወጣት መሪ ንጉሣውያን ቤተሰቦችንና ባለጠጎችን የአገሬን ጥቅም አሳጥተዋል በማለት ንብረት ወርሰዋል ፣ ለእስር ዳርገዋል ። እነዚህ እስረኞች የታሰሩት ደረጃውን በጠበቀ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ነው ። ነገር ግን እስረኞች ናቸው ። አንድ ድሀ ተነሥቶ የታደሉ ናቸው ፣ ኑሮአቸው ከእኔ ኑሮ ይሻላል አይለም ። እስር ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ቢታሰሩም ያው እስር ነው ። ጃንሆይና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የታሰሩት በቤተ መንግሥት ነበር ። እስር ግን እስርነቱን ቦታው አይቀይረውም ። በኖርዌይ የሚገኘው ሀልደን እስር ቤት በሆቴል ቅርፅ ፣ በጫካ ውስጥ የተገነባ ሳውናና እስቲም በየቀኑ የሚወሰድበት ፣ ሰዎችን ከመበቀል በፍቅር ማስተማር በሚል ፍልስፍና የተሠራ ቅንጡ እስር ቤት ነው ። በዚያ ያለ እስረኛ ግን ነጻነት ያለው የጎዳና ድሀ ሆኖ መኖርን የሚመርጥ ነው ። እስር ያለው በዋናነት ሕሊና ውስጥ ነው ። ነጻነት ከጥሩ ቤትና ከጥሩ ምግብ በላይ ነው ። የነጻነት ዋጋ የሚገባን ስናጣው ብቻ ነው ። በእስረኞች ጫማ ውስጥ ለአንድ ደቂቃ እግራችንን ማስገባት ብንችል በየሰንበቱ እስረኞችን እንጠይቅ ነበር ።
ግብጽ ለእስራኤላውያን ትልቅ እስር ቤት ነበረች ። 430 ዓመታት በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ የታሰረባት ነበረች ። እግዚአብሔር የእስራቱን ሰንሰለት ቆረጠና በተአምራት ነጻ አወጣቸው ። እስከ ዛሬ ድረስ ፋሲካን በማክበር የነጻነትን አምላክ ያመሰግናሉ ። የሰው ልጅ ከነጻነት ጋር የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው ። ነጻነቱን የሚነኩ ነገሮችን መቋቋም አይችልም ። ሰው በሥጋና በነፍስ እስር ውስጥ ሊያልፍ ይችላል ። የሚፈታው ግን እግዚአብሔር ነው ። እስር አንድ ዓይነት ብቻ አይደለም ። እስረኞችም የተለያዩ ናቸው ።
አዳም የምኞት እስረኛ ነበረ ። ያለውን ነገር መቍጠር እንኳ አይችልም ፣ ነገር ግን ሌላ ያምረው ነበር ። የሚፈልገውን ነገር ለምን እንደ ፈለገው ምንም ግንዛቤ የለውም ። ግን በምኞት ምክንያት ከሰይጣን ተሻረከ ፣ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ወጣ ። ያንን ነገር የፈለኩት ለምንድነው ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል ። ስለ ራበኝ ነው ወይስ ስላልረካሁ ነው ( ሚሊየነር መሆን የፈለኩት ፣ ለሰይጣንም የሰገድኩት ግራ በሚያጋባ ችግር ውስጥ አልፌ ነው ፣ ራሴን ፈርሜ ለአጋንንት አምልኮ የሰጠሁት መላ አጥቼ ነው ( ብሎ ራስን መጠየቅ ይገባል ። በዓለም ላይ በሥራም በስርቆትም መሰብሰብ ይቻላል ። የሰበሰቡትን መብላት ግን እግዚአብሔር ሲፈቅድ ብቻ ነው ። ብዙ ሰው የማይጠቀምበትን ቁሳቁስ ሲሸምት ይውላል ። የሚሰማውን ጭንቀት ዕቃ በመግዛት ማስታገሥ ይፈልጋል ። የሚያስጨንቀው የጎዳቸው ሰዎች ከሆኑ እነርሱን ይቅርታ መጠየቅና መፈታት ያስፈልገዋል ።
ሲያልም የሚያድር ፣ በሕልሙ ምራቅ እየዋጠ ሲነቃ ምንም የሌለው ሰው አያሌ ነው ። የሚስላቸው ሰዎች ፣ የደረደረው መስፈርት በምድር ላይ የሌሉ ናቸው ። ሰዎች ሁሉ ለእርሱ የሚያጨበጭቡ ፣ ሲራቆት የሚሸፍኑት ፣ ሲወድቅ የሚነጠፉለት ፣ የከበቡት እኔ ልቅደምና ልሙትልህ የሚሉት እየመሰለው በምኞት ይሰክራል ፤ ላልተጨበጠው ፍቅር ንብረቱን ያባክናል ። በሚረጨው የገንዘብ ብዛት ወዳጅ የሚያበዛ ይመስለዋል ። በገንዘቡ ሊገዛን ይፈልጋል ብለው ይበልጥ እንደሚጠሉት አያውቅም ። አዎ እንደ አዳም በምኞት የታሰሩ ብዙዎች ናቸው ። ለሰይጣን አሠራር ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ሚሊየነሮች ፣ የዓለም ዝነኛ ሰዎች ሲኦልን በምድር ላይ ጋብዘዋት ይኖራሉ ። ጥሩ ቤት እንጂ ጥሩ ኑሮ ፣ ጥሩ መኪና እንጂ ጥሩ መዳረሻ ፣ ጥሩ አልጋ እንጂ ጥሩ እንቅልፍ ፣ ብዙ ሰው እንጂ አንድ ወዳጅ ፣ ውድ መድኃኒት እንጂ ፈጣን ፈውስ የላቸውም ። ምኞት ገደብ ከሌለው እንቅልፍን ይነሣል ፣ ያለውን ነገር ይጋርዳል ። እጅ ንብረት ጨብጦ ልብ ግን መጨበጥ ካልቻለ በእጦት ስሜት ያሰቃያል ።
ጨዋ ሰዎች ፣ መልካቸው ቀና የሆነ ፣ ደጋግመን ብንበድላቸው ይቅርታ የሚያደርጉልን ፣ በቂ ኑሮ ያላቸው ፣ ለፍቅር ዋጋ የሚሰጡ ፣ የቤተሰብ ክብር ያላቸው ፣ ተሰሚነትን ያተረፉ እነዚያ ሙሉ ሰዎች በምድር ላይ የሉም ። እመጣለሁ ብለው ልባችንን በምኞት የሚሞሉት ፣ የስልክ ቅዱሳን ፣ በተግባር ግን ጨካኝ የሆኑ ሰዎች ብዙ ናቸው ። ላልተጨበጠ ነገር የተጨበጠ ኑሮአችንን እንበጠብጣለን ። ከእኛ የሌለውን ፍጹምነት ከሰው እንጠብቃለን ። ፍጹም ወሬ ይኖራል ፣ ፍጹም ሰው ግን የለም ። ላዩን አይተን ያደነቅነው ውስጡ የፈራረሰ ፣ የቁም ነገር በረሃ ሊሆን ይችላል ። አዎ እግዚአብሔር በተሰጠን ነገር እንዳናመሰግን ከሚያደርገን ከከንቱ ምኞት ይፈታል ። አዳም የቆጡን አወርድ ብሎ የብብቱን ጥሏል ። ያልተጨበጠውን ሲፈልግ የተጨበጠውን አጥቷል ። “አገባ ያለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ” ይባላል ። በጣም ተጎድተሻል ፣ ጥሩ ኑሮ ይገባሻል ብሎ ትዳርን የሚያስፈታው ሸንጋይ ያልሠራበትን ንብረት ለመካፈል ነው ። አዳም በምኞት እንኳን ሊጨምር ያለውን ሁሉ አጣ ። መልካም መመኘት ክፉ አይደለም ፣ ከልክ ሲያልፍ ፣ የመሥራት ጉልበትን ሲይዝ ግን ክፉ ነው ። “ምኞትና ያልተገራ ፈረስ ሁለቱም አንድ ናቸው ፣ ጋላቢውን ካልጣሉ አይቆሙም” ይባላል ።
አቤቱ አግዘን ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም.