የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የታወቀ አምላክ

“የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤” ሮሜ. 1፡20 ።

የእግዚአብሔር አሳብ ይህን ፍጥረት አቀደ ፣ መለኮታዊ ቃሉ አበጀው ፣ ቅዱስ መንፈሱ አቆመው ። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ክፍልና ምዕራፍ እንዲሁም ቍጥር የሚናገረው ይህ ዓለም አስገኚ እንዳለው ነው ። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ነው ። ዘፍ. 1፡1። ሰማይ ሲል የማይታየውን ዓለመ መላእክትን ፣ ምድር ሲል የሚታየውን ዓለመ ሰብእ ማለቱ ነው ። በጸሎተ ሃይማኖትም፡- “ሁሉን በያዘ ሰማይና ምድርን የሚታይና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን” በማለት እናውጃለን ። ይህ ጸሎትም ፣ ምስክርነትም ነው ። የሚታየውን የፈጠረ ንዑስ አምላክ ፣ የማይታየውን የፈጠረ ልዑል አምላክ አለ ብለው የሚያምኑ አሉና የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ አምናለሁ እንላለን ።

ፍጥረት ስለ እግዚአብሔር የሚያሳውቅ ነውና ከመምህራን በፊት የነበረ መምህር ነው ። ፍጥረት ስለ ቅዱሱ ፈጣሪ ይናገራልና ቅዱስ ጽሕፈት ነው ። ሁሉም ሰው የሚያነበው ፊደል ፣ የቋንቋ ገደብ የሌለበት ጽሕፈት ፣ የተማረና ያልተማረ የሚያነበው መጽሐፍ ፍጥረት ነው ። መጽሐፍ ይታጠፋል ፣ ፍጥረት ግን ሁልጊዜ ተዘርግቶ ያለ መጽሐፍ ነው ። መጽሐፍ ዓይንን ያደክማል ፣ ለማየት የማይታክት መጽሐፍ ግን ፍጥረት ነው ። በፍጥረት መጽሐፍነት የምናነበው “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” የሚለውን ጽሕፈት ነው ። በፍጥረት ላይ ችሎታው ፣ ምልአቱ ፣ ርቀቱ ፣ ረድኤቱ ፣ ጥበቡ ፣ ውበቱ የተገለጠ ቢሆንም ይህ ሁሉ የፍቅር ጠባዩን የሚገልጥ ነው ። የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን ያልተተወ ፣ መለኮታዊ ጥበቃ ያለው ፍጥረት መሆኑን እናያለን ። የሚጠፋው ዓለም ገና ተመርምሮ ካልታወቀ የማይጠፋው ዓለም እንዴት ሊመረመር ይችላል ብለን እንጠይቃለን ። ስለተፈጠረው ፍጥረት ገና ግምት እንጂ እርግጥና ድምድም አሳብ አላገኘንም ፣ ስለ ፈጣሪው ጌታ ባናውቅና ባንገነዘብ የሚደንቅ አይደለም ።

ሰዎች መምህር አጥተው አላመኑም ፣ ሀልወተ እግዚአብሔርን አልተረዱም እንዳንል ከመጽሐፍ በፊት መጽሐፍ ፣ ከመምህራን በፊት መምህር ሁኖ ፍጥረት ቁሟል ። ፍጥረት በአንድ ድምፅ እግዚአብሔር አለ ብሎ ይናገራል ። በፍጥረት ላይም የእግዚአብሔር ባሕርይ ጎልቶ ይታያል ። የሚታየውና የማይታየው ኅብረት ስምምነቱ የእግዚአብሔርን አንድነት ይገልጣል ። ውበትና መናበቡ የእግዚአብሔርን ፍቅርና መሪነት ያጎላል ። ኃያልነቱና ግዝፈቱ የእግዚአብሔርን የማይመከት ክንድ ይተርካል ። ሰዎች ስለ ፍጥረት ብቻ ቢያጠኑ ፈላስፋ ሊቃውንት ይባላሉ ። በተፈጠረው ፍጥረት ፈጣሪውን ሲያስቡ ግን አማኝ ይባላሉ ። የዚህ ዓለም አዋቂዎች የተፈጠረው ፍጥረት ላይ ሲቀሩ ቅዱሳን አባቶች ግን ፈጣሪውን ያመልካሉ ። ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረውን ፍጥረት ብቻ ሳይሆን የፈጠረውን እግዚአብሔር ተመልከቱ ትላለች ። ፍጥረታት ያለማቋረጥ ስለ እግዚአብሔር ይመሰክራሉ ። ከሰዎች ጋር ስለ ፍጥረት ብናወራ ሐሜት ይቀላቀላል ። ፍጥረት ግን ስለ ሌላ ሳይቀላቅል ስለ እግዚአብሔር ብቻ ይናገራል ። “የተፈጥሮ ጸጋ ፣ ተፈጥሮ ለግሶን” እያሉ ሰዎች ይናገራሉ ፣ ፈጣሪ ጌታ እንጂ በራሱ የሚለግስ ተፈጥሮ የለም ።

በግዙፍ መነጽሮች የረቀቁ ነገሮችን እናያለን ። በፍጥረትም እግዚአብሔርን እናስተውላለን ። መሃይም የሚያነበው ፊደል ተፈጥሮ ነው ። ተፈጥሮ ስለ እግዚአብሔር ይናገራልና ቅዱስ ጽሑፍ ነው ። ስለ እግዚአብሔር የሚናገሩ ሁሉ ቅዱሳን ናቸው ። መጽሐፍ ስናነብ የደራሲውን ልብ እናያለን ። በፍጥረት መጽሐፍነትም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የፍቅር አሳብ እንረዳለን ። ቋንቋ በጆሮ የሚሰማ ነው ፣ የፍጥረት ቋንቋነት ግን በዓይን የሚስተዋል ነው ። ለተፈጠረው ፍጥረት መገኘትን ብቻ ሳይሆን ቀጣይነትን ፣ ቀጣይነትን ብቻ ሳይሆን ግብን የሰጠ አንድ አምላክ አለ ። በሥጋችን ነፍሳችንን የተሸከምን ፣ በነፍሳችን ሥጋችንን የተረዳን የሰው ልጆች ፣ ረቂቅነትን ከግዙፍነት አሳማምተን ይዘናል ። ሕይወትና ሞትን አስማምተን በየዕለቱ እንራመዳለንና አስደናቂ ፍጡራን ነን ፣ ደግሞም ጌታ ያገዘን ብርቱዎች ነን ። እግዚአብሔር ለማወቅ ለሚሹ ግልጥ ነው ። እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በፍጥረቱ ይታወቃል ። እግዚአብሔርን በፍጥረቱ አውቆ አለማምለክ ያስቀጣል ። ክብር ምስጋና ለፈጣሪነቱ ይሁን ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተጻፈ ግንቦት 11 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ