የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የትውልድ ንስሐ

“አቤቱ ፥ መረመርኸኝ ፥ አወቅኸኝም ።” መዝ. 138፡1
በሽታ ሁሉ የሚርድልህ ፣ እባብና ጊንጥ በፊትህ የሚወድቅልህ ፣ የዓለሙ ሐኪም ፣ የዓለሙ ጤና እግዚአብሔር ሆይ አመሰግንሃለሁ ። በቃልህ መረመርኸኝ ፣ በማስተዋልህ አወቅኸኝ ። ሐኪም የተራቆተውን ታካሚ በር ዘግቶ ያየዋል ፣ አንተም ከልብስ ዘልቀህ አወቅኸኝ ። ሐኪም ቀዶ ጥገና አድርጎ ባለቤቱ ያላየውን የአካል ክፍሉም ያየዋል ፤ አንተም ልብና ኩላሊቴን መርምረሃል ። አዎ መረመርኸኝ ትኩሳቴ እንደ በዛ ፣ ደም ሳፈስስ ደሜ እንደ በዛ ፣ ስቆጣ ያንተን ፍርድ እንደረሳሁ አወቅኸኝ ። በርግጥ መረመርኸኝ አእምሮ እንደ ከዳኝ ፣ እኖራለሁ ብዬ ሰው እንደ ገደልሁ አወቅኸኝ ። በእውነት መረመርኸኝ ክርስቲያን ሁኜ ኑሬ ፣ ጎሠኛ ሁኜ ስሞት አወቅኸኝ ። በነፈሰበት እንደምነፍስ ፣ ያላጣራሁትን እንደ ማስተላልፍ ፣ ሕንፃ ሥላሴ ሰውን ለማፍረስ እንደምቸኩል መረመርኸኝ አወቅኸኝም ። ጽጌረዳን ስቆርጥ እንደምሳሳ ፣ ሰውን ስቆርጥ እንደምጨክን መረመርኸኝ አወቅኸኝም ። ያሳደግሁትን እንስሳ ለማረድ እንደምሳሳ ያሳደጉኝን ግን ለመግደል እንደምነሣ መረመርኸኝ አወቅኸኝም ። ልቤ ከድቶኝ ፣ አቅሌን ስቼ ፣ በቁመናዬ ልክ ወድቄ ፣ ሲኦልን ገነት አድርጌ መጥቻለሁና በቤትህ አሳርፈህ አክመኝ ። መረመርኸኝ አወቅኸኝም እባክህን መድኃኒት እዘዝልኝ ። እኔ የተበላሸሁ ነኝና ወደ ራሴ ሳይሆን ወዳንተ መልሰኝ ። ለዘላለሙ አሜን ።
ጥቅምት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ