የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የትዕግሥት ትጥቆች

 

“በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤”

                                            

                                 ኤፌ. 4 ፡ 2 ።

 

ቍጣ የእኛ የኢትዮጵያውያን መገለጫ ሊመስል ትንሽ የቀረው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ። የማያስቆጣው ያስቆጣናል ፣ መልሶቻችን ከፍቅር ይልቅ ለቍጣ ያደላሉ ። መልካምነቶቻችንን ቍጣችን እየቀበራቸው ነው ። ደጎች ብንሆንም ቍጣችን ግን ሰዎች እንዲፈሩን ያደርጋቸዋል ። እሳት ለብሰን ፣ እሳት ጎርሰን እንንቀሳቀሳለን ። በቍጣ እንሰብካለን ፣ በቍጣ እናስተምራለን ፣ በቍጣ እናክማለን ። እሳት ለብሰናልና የሚነካንን እናቃጥለዋለን ፣ እሳት ጎርሰናልና ኃይለ ቃል በመናገር የሚሰሙንን እናሸማቅቃለን ። አባት በአባትነቱና በባልነቱ ቍጠኛ ነው ፣ እናት ቍጠኛ ናት ። ልጆችም ይንተከተካሉ ። የታክሲ ረዳቶች ፣ የአውቶብስ ትኬት ቆራጮች ገና ለገና ብለው ያስቀመጡትን ቍጣ በመምዘዝ ምንም እንዳንናገር ያደርጉናል ። በእርስ በርስ ግንኙነት ሰውዬው ተናግሮ ሳይጨርስ እንደ ብራቅ ስንጮህበት ኩም ብሎ ይቀመጣል ። ተጠባብቀን የምንኖር ለመንደድ የተዘጋጀን ሆነናል ። እሳት እንወረውራለን ፣ እሳት ይመለስልናል ።

 

አዲስ አበባ መጥተው ምግቡና ሰዉን መልመድ ያቃታቸው አንድ መነኩሴ፡- “ምግቡ እሳት ፣ ሰዉ እሳት” ብለው ሲናገሩ ሰምቻለሁ ። የሁሉም ሰው መገለጫ ነው ባንልም ቍጠኝነት ግን እየበዛ ነው ። ጆሮአችንን ዘግተን ስለምንሰማ ፣ የምናስበውን እንጂ የሚነገረንን ስለማንሰማ እንቆጣለን ። ግምቶቻችን ነቢይ እንዳደረጉን ይታወቃል ፣ ግምቶቻችንን በማመን እንዲህ የሆነው አንዲህ ስለሆነ ነው በማለት ቍጠኛ ሆነናል ። ለስላሳና ትዕግሥተኛ መሆን ያስንቃል በሚል አመለካከት ቍጣን የክብር መጠበቂያ እያደረግን ነው ። ስስ መሆን  ፣ የኑሮ ጫናዎች መበራከት ቍጠኛ አድርጎናል ። ስሜቴን የሚረዳልኝ ሰው የለም ብለን ማሰብም የብቸኝነት ስሜት ውስጥ ይከተንና ቍጠኛ ያደርገናል ። አብዛኛው የቍጣችን መንስኤ ያልተጨበጠ ነገር ነው ። በውይይት የምንፈታውን በስድብ ፣ በመነጋገር የሚያልቀውን በጦርነት ለመደምደም እንጣደፋለን ። ለእኔ ካልሆነ ለማንም አይሁን የሚል አጥፍቶ መጥፋት እየለማብን ነው ። አሳባችን ባለማንበብና ባለመጸለይ ጉልበት ስለሌለው በሥጋ ጉልበት መለካካት እንፈልጋለን ። ምክንያቱ ባነሰ ቍጥር ጠቡ ከፍ ማለቱ የታወቀ ነው ።

 

ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ትዕግሥት እየተናገረን ነው ። ትዕግሥት አምቆ መያዝ ከሆነ የፈነዳ ቀን ሁሉን ነገር ያበላሻል ። ትዕግሥት ራስን እየጨረሱ ሌላውን ማስደሰት ከሆነ እንደ ሻማ ነዶ ማለቅን ያስከትላል ። ስሞት ይገባቸዋል በማለት ራስ ላይ በሽታን መጥራት ትዕግሥት ሳይሆን ሞኝነት ነው ። የለበጣ ሳቅ እየሳቁ ፣ ለቀለድ ሌላ ቀልድ እየሰጡ በሕይወትና በዕድሜ ማፌዝ ይህም ትዕግሥት አይደለም ። ሐዋርያው መታገሥ ያለብን እንዴት እንደሆነ ይነግረናል ።

 

በትሕትና ታገሡ ፣

 

በየዋህነት ታገሡ ፣

 

በትዕግሥት ታገሡ ፣

 

በፍቅር ታገሡ ይለናል ።

 

በትሕትና መታገሥ ማለት ይህን ሁሉ ጫና ተሸክሞ ቢቆጣ ትክክል ነው ፣ ብዙ ነገሮች አልሆኑላትምና ማዘንዋ አያስወቅሳትም ብሎ መታገሥ ነው ። በትሕትና መታገሥ በዚያ ሰው ጫማ ውስጥ እግርን አስገብቶ ፣ እኔ ብሆን ይህን አልችለውም ነበር በማለት ያንን ሰው ማብረድ ነው ። ቍጣን ከሚያስከትሉ ነገሮች አንዱ የትዕቢት አስተሳሰብና ንግግር ነው ። ትሕትና ግን ጠብን ታበርዳለች ። ከመሳሳትና ሌላውን ከማሳሳትም ታተርፋለች ። ትሑታን ራሳቸውን በቅጡ የሚያውቁ ናቸው ። ጸሎታቸው ባይመለስ አያማርሩም ። እኔ እግዚአብሔርን መቼ ሰማሁትና የእኔን ልመና ስማኝ እለዋለሁ ብለው ተደምመው ይቀመጣሉ ። ትሑታን የሌላውን ስህተት አይከታተሉምና ለቍጣ አይዳረጉም ። ጥቅሜ ከእግዚአብሔር ነው ብለው ስለሚያስቡም ለጠብና ለጦር አይነሣሡም ። ሰዎችን በማጋጨት የሚኖሩ ፣ በጥቅማቸው ፊት የቆመ የመሰላቸውን ማስወገድ ትክክለኛ አካሄድ ነው ብለው የሚያስቡ አይደሉም ። በትሕትና መታገሥ ከመጎዳት ይጠብቃል ።

 

የዋህነት የኑሮ ልምድና እውቀት ከፍ እያለ ሲመጣ ሌላውን በይቅርታ ማየት ፣ እያወቁ የራስን ጥቅም መልቀቅ ፣ ክፉ ቃላት ቢሰሙም አለማኘክ ነው ። በየዋህነት መታገሥ ይህን ያደረገው መኖር በእግዚአብሔር መሆኑን ዘንግቶ በከንቱ ስሌት ለመኖር በማቀዱ ነው ብሎ ለዚያ ሰው ማዘን ነው ። የዋህነት ለዚያ ሰው መልካምነት ዋጋ እየሰጡ ክፋቱን አሳንሶ ማየት ነው ። በየዋህነት ስንታገሥ ልባችን ለስላሳ ፣ አፋችን ልዝብ ይሆናል ።

 

ትዕግሥትን መታገሥ ያስፈልጋል ። ትዕግሥት ለዚያ ሰው የምንከፍለው ዋጋ ብቻ ሳይሆን ለራሳችን ዘላቂ ክብር የምንከፍለው መሥዋዕትነትም ነው ። ቁጭ አድርጎ መሄድ ፣ ሁሉን ትቶ በር መዝጋት ፣ የራሱ ጉዳይ ማለት ይቻላል ። ለአሁንም ድል መስሎ ይታያል ። ቆይቶ ግን ይቆረቁራል ። ትዕግሥት ተራራውን ሳይሆን ከጀርባው ያለውን ድል ማየት ነው ። ትዕግሥት የማየት ውጤት ነው ። ሁሉም ያልፋል ብሎ ተስፋ የማድረግ ውጤት ነው ። ያየነው ጋ ለመድረስ ጤና አስፈላጊ ነውና ትዕግሥተኛ ሰው ራሱን ይጠብቃል ። መታገሥ ሥራ መፍታት ሳይሆን ሁልጊዜ መፍትሔ ማፈላለግ ነው ።

 

በፍቅር መታገሥ ኃይል ይሰጠናል ። ያለ ፍቅር መታገሥ ራስን በልቶ መጨረስ ነው ። በፍቅር መታገሥ ግን በኃይል ላይ ኃይልን መጨመር ነው ። እግዚአብሔር እንዲሁ እንደ ወደደን እንዲሁ መውደድ ስንችል ፍቅራችን ድንበር የለሽ ይሆናል ። ያ ፍቅርም በሰዎች መለወጥ ያምናልና ታጋሽ ያደርገናል ። ማዘንና መታገሥ ልዩነት አለው ። እያረሩ መሳቅና መታገሥ ልዩነት አለው ።

 

እኔም በእርሱ ቦታ ብሆን የበለጠ እስት ነበር ብሎ በትሕትና መታገሥ፤

 

ትምህርትና ልምድ ቢኖረው ይህን በፍጹም አያደርግም ነበር ብሎ በየዋህነት መታገሥ፣

 

መታገሥን እንደ ውለታ በመቍጠር ሳይሆን መታገሥ ለጤናዬና ለዘለቄታ ክብሬ አስፈላጊ ነው ብሎ መታገሥ፣

 

እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ፍጥረት ከቻለ እኔ ደግሞ አንዱን ሰው በመቻል መስቀሉን ላግዘው ብሎ መመቻቸት እርሱ እውነተኛ ትዕግሥት ነው ።

 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ