የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነቢያት ጉባዔ ክፍል 2

የከበረው ነቢይ ሙሴ ወደ መናገሪያው አትሮኖንስ ተጠጋ ። ከአቤል ጀምሮ ያሉት ቅዱሳንን ለማወቅ ስማቸውን ያስተዋወቀኝ አልነበረም ። በዓለመ ነፍስ እውቀት ሙሉ ይሆናል ። ሙሴና ሚልክያስ ለመተዋወቅ በመካከል የሚያገናኝ ሰው አላስፈለጋቸውም ። ቅዱሳን በሰማይ አለማወቅን ድል ይነሣሉ ። ከሥጋ ግርዶሽ ፣ ኃጢአትን ካመጣው ጨለማ ነጻ ወጥተው በሰማይ ያደሩ ጻድቃን እውቀታቸው ሙሉ ይሆናል ። እንኳን በሰማይ ያሉትን የአምልኮ አጋሮቻቸውን ይቅርና በምድር ላይ እየተከናወነ ያለውን ያውቃሉ /ራእ. 6፡9-11/። “ትንሽ ሥጋ ከመርፌ ትወጋ” እንዲሉ የአካላቸው ክፋይ ቤተ ክርስቲያን በምድር አለችና ስለ እርስዋ ይጸልያሉ ። ቤተ ክርስቲያንን በሰማይና በምድር ያለች አንዲት አካል የሚያሰኛት ራስዋ አንድ ክርስቶስ መሆኑ ፣ እርስ በርስዋም የምትተሳሰብ መሆንዋ ነው ። እንኳን የቅዱሳን ይቅርና የኃጥአን ነፍስም እውቀትዋ በምድር ከነበረው የበለጠ ነው ። ነዌ የተባለው ባለጠጋ በሞተ ጊዜ ከሺህ ዓመት በፊት የነበረውን አብርሃምን ያለ ነጋሪ አውቆታል ። በምድር ላይ ስላሉ ወንድሞቹም ሁኔታ ተረድቷል ። ሉቃ. 16፡ 24-27። እኔም ለቅጽበት በዓለመ ነፍስ ራሴን ሳገኘው አለማወቅን አሸንፌው ነበር ። አለማወቅ ወዳጅን ያሳንሳል ። ስናውቅ በሰማይም በምድርም ብዙ ወዳጅ እንዳለን ያስረግጥልናል ።

ሙሴ ለመናገር ድምፁን ይሞርዳል ብዬ ስጠብቅ እግዚአብሔርን ሲያመሰግን የነበረ ጉሮሮ ነውና ጽዳት አላሻውም ። በዓለመ ነፍስ ከቍጥርና ከዘመን እንዲሁም ከታሪክ ውጭ የሆነችው ነፍስ በዘላለም አሁን ውስጥ ተጠቅልላለች ። ከሺህ ዓመት በፊት የነበረውን ለማስታወስ አትመሰጥም ፣ ወደፊት የሚሆነውን ለመረዳት አታሰላስልም ። ነፍስ በሰማይ በማያረጅ አዲስነት ትኖራለች ። ነቢዩ ሙሴ ተናገረ፡-

“አንድ ጊዜ ተፈትነው ባለፉት ዳግመኛ በማይፈተኑት በዓለመ መላእክት ፣ ዘመናችሁን በሙሉ ተፈትናችሁ በዕረፍት ዓለም ያላችሁት ፣ ጸሎትና ምስጋና ተጋድሎ ሳይሆን እስትንፋስ ነውና ፣ ከጸሎትና ከምስጋና ያላረፋችሁ ፣ ምስጋናውን አዝመራ ፣ ውዳሴን መኸር አድርጋችሁ የምትኖሩ ፣ በሰማይ ያደራችሁ ፣ በአብርሃም እቅፍ ፣ በዘላለም መውደድ የተጠቀለላችሁ ቅዱሳን ፣ በምድር ጠርቶን በሰማይ በተቀበለን በእግዚአብሔር ስም ሰላም እላችኋለሁ ! ከምድር እስከ ሰማይ የሚታመን ፣ በሥጋም በነፍስም ዋጋ የሚከፍል እግዚአብሔር ብቻ ነውና አሜን ብላችሁ አመስግኑ!”

ታላቅ ምስጋናና እልልታ ተሰማ ። ከሞተው አቤል እስካረገው ነቢዩ ኤልያስ ድረስ የሆታ ምስጋና አስተጋባ ። በሰማይ ለማመስገን ምክንያት አያስፈልግም ። እሴት መኖር የለበትም ። ፍጹምነት የማይጎድል ምስጋና ባለቤት ያደርጋል ። ሞላ ጎደለ የቍማር ኑሮ ጨዋታ ነውና ምስጋናና ምሬት ሲያፈራርቅ ይኖራል ። ነቢዩ ሙሴ መናገር ጀመረ፡-

“እኔ ከግብጽ ምድር እየመራኋቸው የወጡት ሚሊየን ሕዝቦች ዛሬ ከእኔ ጋር መውረስ አልቻሉም ። ለከነዓንም ለሰማይም ሳይሆኑ ባክነው ቀርተዋል ። አንድና ሁለት ልጅ የሞተበት አባት ሲያዝን ሁሉ አብሮት ያለቅሳል ፣ ሚሊየን ሕዝብ የሞተበት ሰባኪ ግን ብቻውን ልቅሶን ይገፋል ። የሰባኪው ደግነት ሳይሆን የሰውዬው ምርጫ ለድኅነት ያበቃል ። በምድር ላይ መንፈሳዊውን ጉዞ ያልጀመሩ ኢአማንያን ፣ የጀመሩ ወጣንያን ፣ የጨረሱ ፍጹማን አሉ ። ከነዓንን እያሰቡ ምድረ በዳ መቅረት ፣ ያልተገራ የገዛ ምኞት ራስን አሰቃይቶ መግደሉ ያሳዝናል ። በቤተሰብነት ኃጢአተኝነት የለም ። አቤል አዳም አባቱን ትቶ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቆመ ። መንታ ሁነው ቢወለዱ በብዙ ነገር ይመሳሰሉ ይሆናል ፣ ክርስቶስን መምሰል ግን ምርጫ ነውና አንዱ አምኖ አንደኛው ይቃወማል ፣ አቤልና ቃየን በምድራዊ አባት አንድ ሁነው በሰማያዊ አባት ተለያዩ ። እምነት የሚጫንብን ዕዳ ሳይሆን የምንመርጠውና ራሳችንን የምንሰጥለት ነው ። በምድር እምነታችንን እናከብራለን ፣ እምነታችንም በሰማይ ያከብረናል ። ሁሉም በቤቱ ያስተናግዳል ።”

ሙሴ ይህን ከተናገረ በኋላ በአሳብ የተጓዘ እስኪመስል ዝም አለ ። እኔም እልኸኛ ሕዝብ መሪውን በምድረ በዳ የማስቀረት አቅም አለው ብዬ ማሰብ ጀመርሁ ። በአገልጋዮች የተሰናከሉ ምእመናን ብዙ ናቸው ፣ ሙሴን ስናይ ደግሞ በሕዝቡ ምክንያት ተሰናክሎ በምድረ በዳ የቀረ ፣ የአርባ ዓመት አገልግሎቱን ፍጻሜ ያላየ ነው ። ይህ ሁሉ ለትምህርታችን ተጻፈልን ። አገልጋዮች ሕዝብን ስታስተምሩ ካህንም ፣ ዲያቆንም ፣ ሰባኪም ሰው መሆኑን አስተምሩ ።

ይቀጥላል

የነቢያት ጉባዔ/2

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ