የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነቢያት ጉባዔ ክፍል 4

ሊቀ ነቢያት ሙሴ በልዑል ድምፅ ተናገረ፡-

“እኔ የተወለድሁበት አገር የባዕድ ምድር ነበረ ። ፈርዖን ወንድ ጠልቶ ፣ አራስ ልጅን ፈርቶ ፣ ከማኅፀን በር ላይ የሚያንቅበት ፣ ልጅ አትደግ የተባለበት ፣ ወላጅ ልጁ ለሞተበት የጥይት የሚከፍልበት ፣ ግፍ ልኩን አልፎ የሚፈስስበት ዘመን ነበረ ። ንብረትን የሚወርሱ ነገሥታት በሚረገሙበት ዓለም ልጅን ገድሎ አታልቅሱ የሚል ንጉሥ ከሁሉ የከፋ ነው ። ወንድ ልጅ ላይ ያነጣጠረ ግድያ ከጥንት እስካሁን ዘመን አለ ። ወንድን ለጦርነት የሚፈልጉ ነገሥታት ወንድ ልጅን ለማጥፋት ሲጥሩ ሲታይ ፈርዖንና ሄሮድስ ተጠቃሽ ናቸው ። ፈርዖን ወደ ፊት ግዛቴን ቢነጥቁ ብሎ ባዕድነት ተሰምቶት ገደለ ፣ ምንም ቢገድሉ ዘርን ማጥፋት አልቻሉምና እስራኤል ዛሬም አሉ ። እግዚአብሔር ሕዝቡን አትሞቱም አላለም ፣ አትጠፉም አላቸው እንጂ ። አማኝ ሲቆረጥ የሚያቆጠቍጥ ፣ አንድ ሁኖ ሙቶ አሥር ሁኖ የሚበቅል ነው ። የአማኝ ደም ዘር ሁኖ ሌሎችን ያፈራል ። በሰማዕታት ደም ላይ ያፈራሁ ፍሬ ነኝ ፣ ገዳዮች የሰው ሁሉ አንገት ምነው አንድ በሆነልኝ ብለው ቢመኙም ፣ በሞት ሸለቆ ውስጥ በሕይወት የሚያሻግረው ጌታ ያተረፈኝ ሕያው ምስክር ነኝ ። የገዛ ወገናቸውን የሚገድሉ ግን ከፈርዖን ይከፋሉ ። ሄሮድስ ኤዶማዊነቱ ስቦት በእስራኤል አራስ ቢጨክን የሚጠበቅ ነው ። ወገን ወገኑን ሲገድለው ግን የሚያሳዝን ነው ። የወንድማማች ጠብ አሸናፊ የለውም ። የገደልንም እኛ ፣ የሞትንም እኛ ተብሎ የሚለቀስበት ፣ ኀዘን ቅጥ የሚያጣበት ነው ።

ፈርዖን ማለት ጨካኝ ፣ ገዳይ ፣ ሙት አስገባሪ ነበር ። በዘመኑ የሞተ ሰው ለመቀበር ሦስት መቶ ብር ይከፍል ነበር ። ፈርዖን ያልሆነ የሃይማኖት አባት ይገኛል ወይ ? ብለን መጠየቅ አለብን ። ሙት የሚያስገብር አያሌ ነው ። ሰርቆ ካመጣው ሰው አሥራት የሚሰበስብ ሙት አስገባሪ አይደለም ወይ ? የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው የሚል ሙት አስገባሪ አይደለም ወይ ? ከሚሞተው ሰው ገንዘብ የሚበዘብዝ ሐኪም ፣ የተበደለ ላይ የሚፈርድ ዳኛ ፣ ራበኝ ብሎ ለአቤቱታ የወጣን ሕዝብ የሚገርፍ ፖሊስ ፣ ለመንገድ እያለ መቃብር ላይ የሚቀይስ ፣ የሞቱትን አላስሞት የሚል ባለሙያ ሙት አስገባሪ አይደለም ወይ ? ድሀ መኖር ብቻ ሳይሆን መሞትም እየከበደው ነው ። ለመቀበር ብዙ ሺህ ብር ይጠይቁታል ፣ ተለምኖ ይቀበራል ። ለምኖ ሲበላ የኖረው ድሀ ፣ ሲሞት ተለምኖ ይቀበራል ። ሙት አስገባሪ ፈርዖኖች በቤተ እግዚአብሔር አልሞሉም ወይ ? የገዛ ወገኑን የሚገርፍ ፣ ወንድን የሚያረግፍ ከሄሮድስ በላይ ጨካኝ ነው ። ወደፊት አድጎ ይቀናቀነናል ብሎ እርጉዝ የሚገድል ፣ አራስ የሚያንቅ ዳግማዊ ፈርዖን ነው ። ፈርዖን አገራችሁ እዚህ አይደለም ብሎ እስራኤልን ሲገፋ የእርሱ ፍጻሜ ቀይ ባሕር መሆኑን አላወቀም ነበር ። ላይኖርበት ዓለም የሚኖሩ ሕፃናትን ፈጀ ። የፈርዖንም የሄሮድስም ወንድ የማነቅ ተግባር ወንድ ልጅ ይወለዳል ፣ ዓለሙንም ያድናል የሚለውን የመሢሕን መምጣት በአጭር ለመቅጨት ሰይጣን የወጣበት ዘመቻ ውጤት ነው ። ከሚሊየን ወንዶች መካከል መሢሑን ባገኝና ብገድለው ብሎ ጸላዔ ድኅነት የሆነው ዲያብሎስ የሸመቀው ትግል ነው ።

“ጊዜ ሲደርስ ፣ አምባ ይፈርስ” እንዲሉ ፈርዖንና ሠራዊቱ በኤርትራ ባሕር ተቀበሩ ። በየብስ ላይ መኖር ያልቻሉ እስራኤል ፣ በባሕር ውስጥ ማለፍ ቻሉ ። በየብስ ይገድል የነበረው ፈርዖን ፣ በባሕሩ ሠጠመ ። የኤርትራ ባሕር አንዱን በሕይወት ሲያሻር ሌላውን ይገድላል ። ሞትና ትንሣኤ በኤርትራ ባሕር ይታያል ። ሐዋርያው ጳውሎስ ሆይ ቀይ ባሕርን የጥምቀት ምሳሌ አድርገህ እንዳቀረብህ አውቄአለሁ ። ፈርዖንና ሠራዊቱ በባሕሩ እንደ ሞቱ በጥምቀትም ዲያብሎስንና ኃጢአትን ክደን በሞት ሕግ እንለያቸዋለን ። ሰው ሲሞት ለራሱም ፣ ለሰዎችም ፣ ለዓለምም ይሞታል ። ሞት ዓለም መለወጥ እንጂ የማሻሻያ ሕግ አይደለም ። የሞተ ሰው በወርቅና ብር አይደነግጥም ። ከክርስቶስ ጋር ለዓለም የሞተም ዝና አያነቃውም ። በግብጽ ሞተው የነበሩ እስራኤል በቀይ ባሕር በሕይወት አለፉ ። ጥምቀትም ለእግዚአብሔር ለመኖር መነሣት ነው ። እስካሁን ፈርዖን ስጋታቸው ነው ። አሁን ግን ምኞታቸው ብቻ ስጋት ይሆንባቸዋል ። ጥምቀትም ክርስቶስን መልበስ ነውና ፣ እርሱን የለበሰ የራስ ቍር ፣ የደረት ጥሩር ፣ የእግር ገምባሌ ከለበሰ ይልቅ የጠላት ጦር የማያገኘው ነው ። ብሉይን በአዲስ ያብራራችሁ ፣ አዲስን በብሉይ ያስተዋላችሁ ሐዋርያትና ሊቃውንት ምስጋና ይገባችኋል ።”

የሰማይ ሠራዊት ሁሉ በመደመም ዝም አሉ ። በምድር የሚከናወነውን ነገር ባሰቡ ጊዜ ሰው ከታሪክም ፣ ከጉዳትም እንደማይማር በመገንዘብ አዘኑ ። ፈርዖን የኑሮውን ቀንበር አክብዶ ፣ ሕፃናትን ማነቁ ፣ መከራን እንደ ካባና ቀጸላ በሰው ላይ ሲደርቡ ውለታ የዋሉ የሚመስላቸውን ልበ ጠንካሮች አሰቡና፡- “አቤቱ ሕዝብን አድን ከመከራ ፣ አቤቱ ሕዝብህን ባርክ በእንጀራ” ብለው ልመና አቀረቡ ።

እኔም የሚሆነው በሰማይ እንደሚታወቅ ተረዳሁና ስጋቴ ቀነሰ ፤ የጸሎት ረዳቶችም እንዳሉን አሰብኩና ብቸኝነቴን ገሠጽኩት ።

ይቀጥላል

የነቢያት ጉባዔ/4

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ