የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነቢያት ጉባዔ ክፍል 5

ታላቁ ነቢይ ሙሴ ንግግሩን ቀጠለ፡-

“ታጋይ መሆን ፣ ለወገን ጥቅም መቆም ፣ ስለ ነጻነት ነጻነትን ማጣት ፣ ስለ እስረኞች መታሰር በሕይወት ላይ ክብር ነው ። በታጋይ ስም የምንታገለው ለራሳችን ዝና ነው ወይ ? ብለን ልባችንን መጠየቅ ያስፈልጋል ። የጤና እክላቸውን ላለመስማት ታጋይ የሚሆኑ አያሌ ናቸው ። በውጫዊ ዓይናቸው ስለ ድሆች መገፋት እያለቀሱ በውስጣዊ ዓይናቸው ግን ስለ ኑሮና ስለ ትዳራቸው የሚያለቅሱ ዛሬ በዝተዋል ። ጭር ሲል ጭንቀት የሚጀምራቸው ፣ ውጫዊ ጦርነትን በመክፈት ምስኪኖችን የሚያስጨርሱ ቤት ይቍጠራቸው ። ለማይራሩለት ድሀ የአሳብ ዳቦ እየቆረሱ ፣ እኔ ብገዛችሁ ማር አዘንብላችሁ ነበር እያሉ በምኞት የሚቸሩ ብዙዎች ናቸው ። የጀብደኝነት ስሜት የተጠናወታቸው ፣ ዝናቸውን በረሀብተኛ ሬሳ ላይ የሚገነቡ ፣ መነዳት ጠባዩ የሆነውን ወገን በምላስ የሚነዱ ፣ “በአልጋ ሞተ ከመባል ገድሎ ሞተ መባል ለታሪክም ጥሩ ነው” እያሉ ለአንድ ማንነታቸው ሺህዎችን የሚገብሩ ፣ ግላዊ ጠባቸውን ብሔራዊ የሚያደርጉ ፣ የሰውን ስስ ብልት እየነካኩ ፣ የዘር ዕድር እያቋቋሙ ትውልድን የሚቀብሩ በዚህም ለብዙዎች መሞት ምክንያት የሚሆኑ ፣ ዋናው ተዋናይ አይሞትምና ሰው ሁሉ ሲሞት እነርሱ ግን መውጫውን አዘጋጅተው የሚተርፉ ብዙ ናቸው ። ምድር እነዚህን እንደምትሸከም ብታውቅ ኖሮ አትፍጠረኝ ብላ አምላኳን ትለምን ነበር ።

እኔ ለእስራኤል ሕዝብ እቆረቆር ነበር ። የቤተ መንግሥት ኑሮዬ ፣ የወገኖቼን ጭንቅ አላስረሳኝም ነበር። የግል ድህነቴን ለመበቀል የታገልኩ አልነበርኩም ። ንግሥናን አስቀምጬ ፣ አልጋ ወራሽነትን ንቄ ፣ ከቤተ መንግሥት ይልቅ ምድረ በዳን መርጬ ነበር ። ስለ ድሆች በእውነት የሚቆረቆር የተባረከ ነው !

መታገል መልካም ነው ። መከራ የመረረውን ሕዝብ ቢታገሉለት ነጻ ልውጣ ይላል ። መከራን እንደ ሰርግ የሚኖር ሕዝብ ግን ቢታገሉለት መልሶ ይታገላል ። የገዛ ሌባውን የደበቀ የትኛውም ፖሊስ አያወጣለትም ። ራሱን ለመከራ የጻፈ ሕዝብ ፣ በሬ ካራጁ እንዲውል ገዳዮቹን እያቀፈ ፣ የኖሩለትን ይገድላል ። ለማንና ለምን ነው የምቆረቆረው ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ። ራሳችን ሕዝብ መስሎ የሚሰማን ጊዜ ጥቂት አይደለም ። የዓለም ሕዝብ ስንት ነው ቢባል ውስጣችን አንድ ነው ። እርሱም እኔ ነኝ ማለቱ የማይቀር ነው ። እያልን የማንኖረው እውነት አለ ፣ ሳንል የምንኖረው ራስ ወዳድነት አለ ። ተራ ምርምርና ፣ የሥነ ልቡና ብልጠት ሳይሆን ራስን ለማየት ጥልቅ የሆነው ቃለ እግዚአብሔር ያስፈልገናል ። እኔ የማስፈልገው ለማን ነው ? ብሎ መጠየቅ መታደል ነው ። በቦታችን ሠራተኛ ፣ ያለ ቦታችን ተመልካች ነን ። በቦታችን ታዳጊ ፣ ያለ ቦታችን አጥፊ ነን ። እኔ ልቤ ለእስራኤል ይቀና ነበር ። ቅንዓቴ ግን ሥጋዊ ስለ ነበር ነፍሰ ገዳይ አደረገኝ ። በሥጋዊ ቅንዓትና ያለ ጊዜው በመውጣት ለአርባ ዓመት ስደት ተዳረግሁኝ ። ወገኖቼም ደስ አልተሰኙብኝም ። ላቀልላቸው ያሰብኩት ቀንበር የበለጠ ጸናባቸው ። መንፈሳዊነት የጎደለው ቅንዓት ራስንም ሌላውንም አያድንም ። ሚስቴ ኢትዮጵያዊት እንደመሆንዋ እንዲህ ብላ ትተርት ነበር ። “የእንጨት ምንቸት ራሱ አይድን ፣ ሌላውን አያድን” ትል ነበር ። ከእንጨት የተሠራ ድስት ራሱም በእሳት ይበላል ። የሚጠብቀውንም ወገን አብስሎ አያበላም ። የወንድነት ቅንዓት የእንጨት ምንቸት ነው ።

እግዚአብሔር ስለ ወገን ሸክም ሲሰጣችሁ እኔ የተላክሁት ለማን ነው ? ማለት አለባችሁ ። እዚህ ፊት ለፊቴ የማያችሁ የጌታዬ የክርስቶስ ሐዋርያት አላችሁ ። ቶማስ ለሕንድ ፣ እንድርያስ ለግሪክ ፣ ጳውሎስ ለሮም ተልካችኋል ። ሀገረ ስብከታችሁን በመለየታችሁ ወንጌልን ለዓለም አደረሳችሁ ። ደግሞም በምድር ላሉት ተተኪዎቻችን ደግሜ የምናገረው የምትሰብኩት ፣ የምትሮጡት ለማን ነው? በርግጥ ለወገናችሁ ነው ? ወይስ ለግል ኑሮአችሁ ነው ? የራሳችሁ ሎሌዎች ከመሆን ፣ በሰማያዊ ዓላማ ምድራዊ ኑሮአችሁን ከማሞቅ አምላከ እስራኤል ይጠብቃችሁ ። እኔ ለቀናት ከፈርዖን ጋር ታገልሁ ። ለአርባ ዓመት ግን ነጻ ከወጣው እስራኤል ጋር ታግያለሁ ። በማያምኑ ከመፈተን በሚያምኑ መፈተን ፣ በውሻ ከመነከስ በበግ መነከስ ሕመሙ ከፍ ያለ ነው ። እግዚአብሔር ግን በካህንም በምእመንም አይለካም ። ያመናችሁትን ካወቃችሁ በየጣቢያው “ወራጅ አለ” እያላችሁ አትጮኹም ። አሁንም በእግዚአብሔር የምታምኑ አገልጋዮች በርቱ ፣ ልባችሁም ይጽና ። በብዙ ሕዝብ የምታምኑ ሰባኪዎች ታዝናላችሁ ፣ ልባችሁም ይቆስላል ። ምርጫው የእናንተ ነው ፤ እግዚአብሔር የተገኘበት ትንሽ ጉባዔ የለምና በሙላትም በጉድለትም ደስ ይበላችሁ !

የአንበሳ ቆዳ አልብሰው ሲያሞግሱአችሁ ደስ እንዳላችሁ ፣ የውሻ ቆዳ አልብሰው ሲያኮስሱአችሁም ደስ ይበላችሁ ። ሆሳዕና ሲሉአችሁ በልኩ ከተደሰታችሁ ፣ ይሰቀል ሲሉአችሁም ትታገሣላችሁ ። አይዟችሁ ዓርብ እሁድ ፣ ስቅለትም ትንሣኤ አለው ። በበረከት ተባረኩ !

የነቢያት ጉባዔ/5

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሚያዝያ 11 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ