የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነቢያት ጉባዔ ክፍል 7

ነቢዩ ሙሴ፡- “የሰማዩ ሰማይ እግዚአብሔር ነው ፣ ሀገረ ሕይወት ፣ መንግሥተ ሰማያትም እርሱ ነው ።” በሚል ምስጋና ተሞላና ስለ አገልጋዮች መናገሩን ቀጠለ ። ዮሐንስ መጥምቅም በታላቅ ትሕትና ይሰማው ነበርና ወደ እርሱ አትኵሮ መናገሩ ጀመረ፡-

“እግዚአብሔር ያለፉት ለቆሙት እንዲናገሩ አድርጎ ሕይወትን አዋቅሯል ። እርሱ ትላንት ያላመለጠው ፣ ዛሬ ያልካደው ፣ ነገም ከእጁ የማይወጣ ሕይወተ ባሕርይ አምላክ ነው ። ቅዱሳን በኑሮአቸው በቃል ፣ በሞታቸው በዝምታ ሲናገሩ ይኖራሉ ። እኔ እግዚአብሔርን የተከተልሁት ስለ ከነዓን አልነበረም ። ከነዓንን የፈጠረውን ይዤ ስለ ተፈጠረ ነገር እንዴት አገለግላለሁ ? የተመኘሁት ቢቀርም እግዚአብሔርን ግን አላጣሁም ። ሰው አጣሁ ነጣሁ ማለት ያለበት እግዚአብሔርን ሲከስር ብቻ ነው ። እግዚአብሔር ኪሣራ የሌለው ትርፍ ፣ የማያረጅ ዘመድ ነው ። በተራራው ላይ ሆኜ ከነዓንን ተሳለምኋት ። በዚያም መላእክት አፈር አልብሰውኝ አንቀላፋሁ ። ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እንዲኖርና እንዲያገለግል የተጠራው ከሞትሁበት ተራራ ፊት ለፊት ባለ ሸለቆ ውስጥ ነው ። ማን ይቀብረኛል ? ብቻዬን ነኝ እንዳይል አፈር አልባሽም ፣ ታሪክ ቀያሽም ፣ ሞትን የሚበቀል ልጅም እግዚአብሔር መሆኑን ሊያስተምረው ነው ። ወላጆቹ ከሄሮድስ ሰይፍ ሊጋርዱት በምድረ በዳ ይዘውት ሸሹ ። እነርሱ ሞቱ ፣ ዮሐንስ ግን አደገ ። አራስ ልጅም በእግዚአብሔር እንደሚያድግ ዮሐንስ መጥምቅ ምስክር ነው ፣ እግዚአብሔር እንደሚቀብርም እኔ ምስክር ነኝ ። እናንተ አገልጋዮች ከፍርሃት ዳኑ ። ምድራዊ መንግሥት እንኳ በጀት አለው ። እግዚአብሔርም ለመንግሥቱ በጀት አለው ። ያለ ከረጢትና ያለ ኮሮጆ ልኮ የማያጎድል አምላክ ነው ።

ኤልያስ ነቢይም ድንገት ብድግ አለና፡- “እግዚአብሔር የሕያዋንና የሙታን ጌታ መሆኑን ሊያስተምር አንተ እንድትሞት ፣ እኔ ወደ ብሔረ ሕያዋን እንድነጠቅ አደረገ ። በደብረ ታቦርም ሞቱን ለማስተማር አንተን ፣ ትንሣኤውን ለማስተማር እኔን አመጣ ። የዘመናት ርቀት ቢኖርም አለመተዋወቅ አልገጠመንም ። የአንድ አባት ልጆች የትም አገርና ዘመን ቢኖሩ ይተዋወቃሉ ። መተዋወቅ መተሳሰብ እንጂ መተያየት አይደለምና ።” የኤልያስን ቃል ሙሴ ነጠቀ ፣ የነቢያት ጉባዔ ነውና ምክሩ ፈለቀ፡-

“የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሆይ ! የጣለው በረዶ ጣራችሁን እንዳይነድለው ፣ የመጣው ጎርፍ መሠረታችሁን እንዳይፈነቅለው ቃሉን ሰምቶ ማድረግ ይሁንላችሁ ። የቃሉ የጆሮ ደምበኞች ቃሉን ይሰማሉ ፣ ለጊዜው ተመስጠው ስሜታቸው ሲበርድ ይረሱታል ። ቃሉን ሰምተው የሚያደርጉ ክርስቶስን ጌታ ፣ ሰማይን ዋጋ ያደረጉ ናቸው ። “በአህያ ቆዳ የተሠራ ቤት ጅብ የጮኸ ዕለት ይፈርሳል” እንዲሉ ቃሉን በሕይወታቸው የማያውቁት በፈተናና በመከራ መንገድ ይቀራሉ ። “የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል” እንዲሉ እሳትን በውኃ እንጂ እሳትን በእሳት ለማጥፋት አትሞክሩ ። “ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራልና” እልኸኛ ሕዝብን እንደ እኔ የምታገለግሉ ከሆነ ኑሮአችሁ ልቅሶ ያለበት ነው ። እኔን አንድ ቀን ያላመሰገነኝ ፣ በምድረ በዳ ሲቀማጠልብኝ የነበረ ሕዝብ ስሞት ሠላሳ ቀን አለቀሰልኝ ። ስትኖሩ ርኵስ ፣ ስትሞቱ ቅዱስ ናችሁና አትደነቁ ። እንደው የኢትዮጵያ ምሳሌ ግሩም ነውና፡- “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል ይላሉ ። እናንተም መዛላችሁን ማንም ሳያውቅላችሁ እንዳትሞቱ ሁልጊዜ ተጠንቀቁ ። ደግሞም “አሽሟጣጭ ዝናብ ወንዝ ዳር ያካፋል” እንዲሉ ቃሉን ጠገብን ካሉ ሰዎች ርቃችሁ የተራበውን አገልግሉ ። የራበው እያለ የሚያቅረውን ለምን ትታገላላችሁ ? “የድሀ ጉልበት በጎመን ዘር ያልቃል” እንዲሉ ጉልበታችሁን በከንቱ አትጨርሱ ! በማገልገላችሁም ውለታ አይሰማችሁ ። ማገልገል መገልገል ነውና !

ይቀጥላል

የነቢያት ጉባዔ/7

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ