የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነቢያት ጉባዔ/9

ነቢዩ ኤልሳዕ አንድ ጊዜ ታላቁን ነቢይ ሙሴን ፣ ሌላ ጊዜም መምህሩን ነቢዩ ኤልያስን እያየ ንግግሩን ቀጠለ፡-

“ኢያሪኮ ደማቅ ከተማ ነበረች ። በኢያሪኮ ሰማይ ፀሐይ አይጠልቅም ነበር ። እግዚአብሔር ፀሐይን ሲያጠልቅ ሰዎች መቅረዝ አብርተው ይቀመጡ ነበር ። ውድ የሆኑ የሙት ባሕር ቅባቶች ሴቶች ያችን ከተማ እንዳይለቁ አድርገዋል ። ንጹሕ መታጠቢያ ቤትና ቅባት ብዙዎችን የከተማይቱ እስረኛ አድርገዋል ። ኢያሪኮን ለመጎብኘት የሄዱ በዚያው ነዋሪ ሁነው ይቀራሉ ። በኢያሪኮ ሕይወት የሚለካው በልብስ እንጂ በልብ አልነበረም ። በቂ ጥበቃ ያለባት ከተማ ፣ ሰዎች ማንንም ላለመንካት የሚጠነቀቁባት ምድር ናት ። ፍርሃትና የልብ ሁከት ግን ሰውን ብረር ብረር ያሰኘው ነበር ። በኢያሪኮ መቃብሮች የተጌጡና በአበባ የተንቆጠቆጡ ነበሩ ። እዚያ መኖር ብቻ ሳይሆን መሞትን ያስመኛሉ ። የመቃብር ስፍራዎች ቢያምሩም ሕይወት የለባቸውም ። በኢያሪኮም ውበት አለ ፣ ሕይወት ግን የለም ። መቃብሮች ተጠጋግተው ቢቀመጡም ፣ አንዱ ባንዱ ላይ ቢነባበርም አያወሩም ። በሰለጠነችው ከተማም ጎረቤት ሰላም አይባባልም ። ሰው ለሰው ተፈራርቶ ላለመነካካት ተጠንቅቆ ይኖራል ። የገንዘብ አምልኮም ስስትን እየዘራ “ምን እሰጣለሁ?” ሳይሆን “ምን እቀበላለሁ?” የሚል ሒሳባዊ ዓለም ፈጥሮ ነበር ። ከተሞች ሲሰለጥኑ ብልጠት እንደ ጽድቅ ይታያል ።”

“የጥይት ድምፅ ባይሰማም የሰለጠነ ከተማ ነዋሪ ውስጡ የተረጋጋ አይደለም ። በኢያሪኮ ባርነት ይወገዛል ። የእጅ ስንሰለት ያጠለቁ ባሮች አይታዩም ። ሕይወት ግን በዚያ ከተማ ግብ የሌላት እሽክርክሪት ነበረች ። ሳምንት ሙሉ የባከኑ ሰንበት ላይ በሙት ባሕር ዳርቻ ተዘርረው ፀሐይ ይሞቃሉ ። የልብ ቃጠሎን በበረሃው ቃጠሎ ሚዛናዊ ለማድረግ ይጥራሉ ። ከተማይቱ ውስጥ ያለው ባርነት አእምሮአዊ ነው ። መንፈሳዊ ቅኝ ግዛት በርክቶ ነበር ። የከተማይቱ ስም የጨረቃ ከተማ የሚል ትርጉም አለው ። በዚያች አገር የሚወራው ስለ ጨረቃ ነው ። የሰማይ ጎረቤት ስለመሆን ነው ። ሌሎች ዓለማትን ስለማግኘት ነው ። የረገጡትን ምድር አክፍተውት ሌላ ምድር ይናፍቁ ነበር ።”

“ነጻ መሆንና ነጻነት ልዩነት አለው ። የዚያች ስልጡን ከተማ ነዋሪዎች ነጻ ነኝ ይላሉ ። ነጻነት ግን አልነበራቸውም ። እንደ ልባቸው መሪያቸውን መሳደብ ይችላሉ ፣ መንካት ግን አይችሉም ። የማስተንፈሻ ጫካዎች ተዘጋጅቶላቸው እንደ ልባቸው ይቃወማሉ ። በተዘዋዋሪ ግን የመንግሥታቸው ተንቀሳቃሽ ማሽን ናቸው ። ማንም የእኔን ፍላጎት እንዲወስን አልፈልግም የሚል ድምፅ ከተማይቱን አጣቧታል ። ቃለ እግዚአብሔር መስበክ የሰውን ነጻ ፈቃድ መጫን እንደሆነ ይታሰብ ነበር ። በዚህ ምክንያት ከተማይቱ ስብከትን ለማገድ ታቅዳለች ። ሴቶች ዕርቃናቸውን ይሄዳሉ ። ሙቀቱን ምክንያት አድርገው ይራቆታሉ ። የሚነሰንሱት ሽቱም መልካም መዓዛ በመውደድ ሳይሆን ሌላውን ለመሳብና ልዩ አትኵሮት ለማግኘት ነው ። በሰለጠነ ከተማ ተፈጥሮን የማይቀበል ትውልድ ይፈላል ። ወንድ ሁኖ ሴት መሆንን ፣ ሴት ሁኖም ወንድ መምሰልን ይሻሉ።”

“ኢያሪኮ ጎዳናዋ ሰፊ ነው ። ያለ ድንበር ከልካይ ብዙ ንግዶች ይመጣባታል ። መብራት አይታጣባትም ። ቅባት በቀላሉ ይገኝባታል ። የመዝናኛ ስፍራዎች በብዛት ያሉባት ውብ ከተማ ናት ። ነገር ግን ውኃዋ መራራ ፣ ምድሪቱን የምትጨነግፍ ነበረች ። የሰለጠኑ ከተሞች ዘመናዊ ትምህርት አላቸው ። የኖረውን እሴት ግን ይጥላሉ ። ዘመናዊነት ዓለም ዛሬ ጀመረች የሚል ትላንትን የሚንቅ ነው ። በሰለጠኑ ከተሞች መኖር የማይፈልጉ ወላጆች ፣ ለልጆቻቸው ግን ይመኛሉ ። ልጆች ግን ሕይወት መራራ እንደምትሆንባቸው ፣ ከምግባርም እንደሚጨነግፉ አያስተውሉም ። ምድር ከመልካም ነገር ፣ ከጥሩ ትውልድ በምትጨነግፍበት ከተማ መኖር ተጨማሪ ፈተና ቢኖረውም እንደ ሎጥ መቀደስ ይቻላል ። አዳም በገነት ረከሰ ፣ ሎጥ በሰዶም ተቀደሰ ። አንድ ራሱን ቢያድንም ሚስቱንና ልጆቹን ግን ከስሯል ። በሰለጠኑ ከተሞች ትዳር ትግል አለው ። ቢሆንም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን በእሳትም በውኃም አክብሮ መያዝ ይገባል ። ልጆች እናውቃለን ብለው ይጠፋሉ ። ልጅ ይሮጣል ፣ ሽማግሌ ግን መንገድ ያውቃል ። በትዕግሥትና በጸሎት ልጆችን ማትረፍ ይገባል ። የተጸለየበት ልጅ ወጥቶ አይቀርምና ።”

“እግዚአብሔርን ለማምለክ ምቹ ከተማ ሳይሆን ምቹ ልብ ያስፈልጋል ።”

ነቢዩ ኤልሳዕ በምድር ላይ በሰፊ ትምህርቱ ሳይሆን በብዙ ተአምራቱ የሚታወቅ ነው ። አሁን ግን ሰፊ ትምህርት መስጠቱ ገረመኝ ። ይህን ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሰማይ ለእኛ መልእክቱን ዛሬም እንደ ቀጠለ አስተዋልሁ ። ምድርን ለማየት ሰማያውያን ዓይናቸው በቂ ነው ። እኛ ሰማይን የምናየው ግን በእምነት ነው ። በእምነት ነገሥታትንና መከራን ብቻ ሳይሆን ምቾትንም ድል እንድንነሣ ተመኘሁ ። ዛሬም ለእኔ ቃል ያላለቀበትን እግዚአብሔርን አመሰገንሁ ።

ይቀጥላል

የነቢያት ጉባዔ/9

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ