የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነጠፈው ጅረት /2/

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ ኅዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም
ዛሬ የሮማና የግሪክ ጠበብቶች የሚሠሩትን ሐውልት የማስጀምርበት ቀን ነው። በዚህ የማስጀመሪያ ቀን ወዳጆቼ ፣ መከራ ያሸሻቸውና ፈውሴ የመለሳቸው ሁሉ የሚገኙበት ድንቅ ቀን ነው ። እግዚአብሔር ፈውስን ከሰጠ ባለፈው ነገር መታመም ፣ እግዚአብሔር ካዳነ ሰውን መቀየም ከንቱ ነው ። ሁሉንም የሚያገናኘው እርሱ ክርስቶስ ነው ። በልደቱ ሕዝብና አሕዛብን ፣ መላእክትና ሰውን ፣ አዳምና እግዚአብሔርን ያገናኘ ሁልጊዜም አንድ ሲያደርገን የሚኖር እርሱ ነው ። ነዶው ፍሬ ቢኖረውም እርስ በርሱ ለመያያዝ ግን እጅ የለውም ። እያንዳንዱ ሰውም በተፈጥሮና በጸጋ የተቀበለው መልካም ነገር ቢኖረውም ያለ ክርስቶስ መንፈስ አንድ መሆን ግን አይቻልም ። እርሱ አንድ ሲያደርግም በአንድ ቤት መኖር ፣ በአንድ መቀመጫ መቀመጥ ፣ ተመሳሳይ አሳብ ማውራት ሳይሆን ከዚህ በበለጠ ለእኔ ሳይሆን ለወንድሜ የሚል ፣ ከመብት ፍቅርን የሚያስቀድም አንድነት ነው ። አዎ መብት ተከብሮ ፍቅር ላይከበር ይችላል ፤ ፍቅር ግን መብትን አክብሮ የበለጠ ያደርጋል ። በዚህ ቀን የሐውልቱን ሥራ ለማስጀመር ፣ የመሠረት ድንጋይ ለማኖር ሌቱ አልነጋ ብሎኝ ፣ ጨለማና ብርሃን ፍልሚያ ሳይገጥሙ ፣ ወፎች ዝማሬ ሳይጀምሩ ማልጄ ደረስኩኝ ።

ወዳጆቼም ማልደው ከማለዳው በ12 ሰዓት ደረሱ ። አንዳንዶቹ ከደቡብ ከይሁዳ ሌሎቹም ከገሊላ አውራጃ የመጡ ናቸው ። ብዙ ዓመት በበሽታዬ ጠይቀውኛል ። ስፈወስ ታዲያ አንድ ቀን ከእኔ ጋር ማመስገን ይገባቸዋል ።ጠይቁኝ ብዬ አላኩባቸውም ፤ አመስግኑልኝ ብዬ ግን ጠርቻቸዋለሁ ። ምስጋና የተባበረ ቃል ይፈልጋል ። እኔን የሰማ ሁሉን እንደሚሰማ አምናለሁ። ሰዎች ከሚያውቁኝ በላይ የማያውቁት ኑሮ አለኝ ። እንግዶቼ በዚያ ታላቅ እርሻዬ ላይ ተሰበሰቡ ። አንዳንዶቹ እያለቀሱ ያዩኛል ። አንዳንዶቹ በመገረም ያጠኑኛል ። እኔም ራሴን እንዲሁ ስለማየው አልደነቀኝም ። መላው ዓለም የተሰበሰበ መሰለኝ ። ግሪካውያንና ሮማውያንም አሉ ። ይጨክናሉና ሮማውያን ርኅራኄውን ፣ ዘመናይ ናቸውና ግሪካውያን ጥበቡን እንዲያዩልኝ ፈለግሁ ። ምልክት ፈላጊዎቹ አይሁድም ለእኔ ያደረገውን እንዲያዩ ተመኘሁ ።
ንግግሬ ከደስታ ብዛት እየሰከረ መጣ ። አንዴ በአራማይክ አንዴ በሱርስት አንዴ በግሪክ አንዴ በላቲን መናገር ጀመርሁ ። ዝናው በዓለም ሁሉ ብቻ ሳይሆን ዝናው በዘመን ሁሉ እንዲናኝ ተመኘሁ ። ሁሉም እንግዶቼ ከእኔ አንድ ትረካ ፣ አንድ ቅዱስ ታሪክ ሊሰሙ በዝግጅት ላይ ናቸው ። እኔም ያሳለፍኩትን ዘመን ለመተረክ ጉሮሮዬን አሟሸሁ ።
የተወለድሁት በይሁዳ ያደግሁት በገሊላ ነው ። ገሊላ ሁሉንም የምታስታርቅ አውራጃ ናት ። ኢየሩሳሌም የአምልኮ ማዕከል ናት ። ዕድሜዬ ገና ለጋ ሳለ ተዳርሁ ። ለትምህርት ያላሰቡኝ ወላጆች ለትዳር ግን አሰቡኝና ገና በ15 ዓመቴ ኑሮ ያዝሁ ። ትዳርን ርእስ ይሰጡታል ቢባሉም እነዚያ ልጆች አልመጡም ። ለእኛ ማኅበረሰብ አለመውለድ ትልቅ የሴት ልጅ ጥፋት ደግሞም ርግማን ተደርጎ ይቆጠራል ። የወለዱት ያልወለዱትን ለመናገር ጨካኝ ናቸው ። እንደምታውቁት ባሌ ብዙም ዕድሜ አላገኘም በሞት ሲለየኝ ሕይወትን በመከራ ትምህርት ቤት መማር ጀመርሁ ። ቤቴ ሲፈርስ የተውሁትን የእናት የአባቴን ቤት መማጸን ፈለግሁ ። ለካ የወላጅ ቤት ቤት የሚሆነው እስከ ትዳር ነው ። ንግግራቸው ያስከፋኝ ፣ ንግግሬ ያስከፋቸው ጀመረ ። ሁሉም ሆደ ባሻ ሁኖ መኖር አይቻልምና እንደገና ለብቻዬ ወጣሁ ። ቀድሞ ከወላጆቼ ቤት የወጣሁት ተድሬ ለአንድ ወንድ ተሰጥቼ ነበር ። አሁን ግን ሳልዳር ከራሴ ጋር ለመኖር ሁለተኛ ጊዜ ወጣሁ ። በስሜታቸው ሁነው የሚናገሩኝ ይበልጥ አቆሰሉኝ ። ብዙ ስለምጠብቅ የቤተሰቦቼ ማጽናናቱም ስድብ መሰለኝ ። የምንሰማበት ስሜት ደጉን ንግግር ክፉ ያደርገዋልና ስሜታችንን ማረም ከሁሉ የተሻለ መንገድ ይሰጠናል ።
ወደ ወላጆቼ ቤት ስገባ በጥብርያዶስ ዳርቻ የነበረውን ቤቴንም እርሻዬንም አከራይቼ ነው ። አሁንም ተከራዮቼን ውጡ ማለት አልፈለግሁም ። በደግነት ሳይሆን ብቻዬን እንዳልሆን ብዬ ነው ። ነገሮች ግን ድንገት እየተለወጡ መጡ ። በደም ማዕበል ተመታሁ ። ጊዜያዊና ልማደ አንእስት ይሆናል ብዬ ማሰብ ጀመርሁ ። ልማደ አንእስት ከቀናት ከሰው ይለየኝ ነበረ ። ሊቆም ስላልቻለ ለዘመናት ከሰው እየተለየሁ መጣሁ ። ተከራዮቼም ችግሬን መገንዘብ ሲጀምሩ እንዳይረክሱ ብለው ቤቴን ለቀው ወጡ ። እኔም ልማድ ሳይሆን በሽታ እንደ ገጠመኝ አወቅሁ ። የማያቋርጥ ደም ይፈሰኝ ጀመረ ። ስቃይ ፣ ሐፍረት ፣ መገለል እየገጠመኝ መጣ ። ከሰውነቷ ፈሳሽ የሚወጣት ሴት ተገልላ መኖር እንዳለባት ሕጉ ያዝዛል ። ስለዚህ በአዋጅ የተለየሁ ሰው ሆንሁ ። ሰው ገንዘቡን ለጤናው ይከፍላል ። ገንዘብ ግን የሄደውን ጤና መመለስ አይችልም ። ጤና የማይገዛ ሀብት ፣ ሳለ የሚናቅ ከሄደ ግን ለመመለስ የሚያስቸግር ነው ፤ ለዘመናት የካበተው የሀብት ቁልል መድኃኒት ፍለጋ ስዞር ተናደ ። ሁሉም በበሽታዬ ላይ አዋቂ ለመሆን ይመኛል ። ከበሽታው በላይ መድኃኒቱ እየጎዳኝ መጣ ። የሰው መድኃኒት አንዱን ክፍል ጸጥ ለማሰኘት ሌላውን ክፍል የሚገድል መሆኑን አስተዋልሁ ። የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው የእርሱ መድኃኒት ብቻ ነው ። በሽታዬ ብዙ ሰዎችን አሳወቀኝ ። ባለመድኃኒቶቹ የተለያየ ማንነት ነበራቸው ። የማያውቁ በግምትና በድፍረት የሚያክሙ አንደኞቹ ናቸው ። ሁለተኛዎቹ ሰውነቴን የሚመዝኑት በሃምሳ በስድሳ ኪሎ አፈር ነውና በጣም ግዴለሾች ነበሩ ። የያዙት መድኃኒት መሥራት አለመሥራቱን የሚሞክሩብኝ በሦስተኛ ምድብ የሚቀመጡ ባለመድኃኒቶች ነበሩ ። ቅንነቱ ያላቸው ነገር ግን መድኃኒቱ የሌላቸው ሐኪሞችም በአራተኛ ደረጃ ገጥመውኛል ። እውቀት ያላቸው መድኃኒቱንም ለማግኘት የሚሞክሩ በአምስተኛ ደረጃ ቢገጥሙኝም እውቀታቸው ግን ሥነ ምግባር የሌለው ሌላውን የሚያዋርድ ነበር ። በስድስተኛ ደረጃ የገጠሙኝ ስለገንዘብ እንጂ ስለ ሰው ዋጋ የማይሰጡ ሐኪሞች ናቸው ። በሰባተኛ ደረጃ የገጠሙኝ የራሳቸውን በልተው ለሌላ አዲስ ተመጋቢ ሐኪም የሚጽፉልኝ ናቸው ። ብቻ ሕመሜ ብዙ የታመሙ ሐኪሞችን አሳየኝ ።
በዚህ ሕመሜ እስከ ግሪክ ድረስ ሄድኩኝ ። ነገር ግን ፈውስ አላገኘሁም ። አሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሰኝ ኖርኩኝ ። ሰው እንዲመጣም እኔም ሰው ጋ እንድሄድ ሳልመኝ ፣ ከራሴ ሸሽቼ አሥራ ሁለት ዓመት በቀን ጽልመት ውስጥ ኖርኩኝ ። ከአሥራ ሁለት ዓመት በኋላ ምሰሶው እንደ ተሰበረ ቤት አቅሜ ፍጹም ተሰበረ ። በአልጋ ወደቅሁ ። የቀረ የሀብት እንጥፍጣፊ ካለ ብሎ ሐኪሙ መምጣት ጀመረ ። እኔም ለሙከራ መክፈል ሰልችቶኝ ብቻ ሳይሆን ገንዘቤን ጨርሼ ነበርና ደከመኝ ። ገንዘብ ሲያልቅ እምነት ብቻ መከታ መሆን ይጀምራል ። ገንዘብ ግን አምላክን ያስረሳል ።
ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ