የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነጠፈው ጅረት /3/

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ታህሣሥ 3 ቀን 2011 ዓ.ም.
ርስት አይሸጥምና ሀብትና ንብረቴን ባጣም ርስቴን ግን ላለማስነካት ቆርጫለሁ ። ርስት የእግዚአብሔር ስጦታ ነውና አይሸጥም ። ርስትን መሸጥ ከእግዚአብሔር ይለያል ። እግዚአብሔር ድል ነሥቶ የሰጠው እንጂ የእኛ የውጊያ ውጤት አይደለምና ርስት አይሸጥም ። መሢሑም ሲያስተምር “በከንቱ የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ” ብሏል ። ርስት ብዙ አባቶች የደም ዋጋ የከፈሉበት ነው ። ስለዚህ አይሸጥም ። ርስትን መሸጥ የአባቶችን ድንበር ማፍረስ ተገቢ አይደለም ። በታሪክ የተቀመጥ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተቀመጠ የአባቶችን ሥርዓት ማፍረስ አደጋው ከፍ ያለ ነው ። መሸጥ ቀላል ነው ፣ እንደገና ገንዘብ ማድረግ ግን ይከብዳል ። የሚሸጡት ያልቃል ፣ የሚሰጡት ግን ይበዛል ። መሸጥ አልፈልገውም ውሰዱልኝ ማለት ነው ፣ መስጠት ግን ፍቅር ነው ። በደጃፌ የሰው ኮቴ ከተሰማ ወራቶች እየተቆጠሩ ነው ። አመመኝ ብዬ ብልክም ልማዷ ነው እባላለሁ እንጂ ማንም አያዝንልኝም ። ሰው እንዴት ካላመመው አመመኝ ይላል ። ሰው ሥነ ልቡናው ሰግቶ ሊያመኝ ይችላል ብሎ ይፈራ ይሆናል ። በሥነ ልቡና ጨዋታ ግን አመመኝ እንዴት ይላል ? እያልሁ ከራሴ ጋር እሟገታለሁ ፤ የመሃይም ፍልስፍና እፈላሰፋለሁ ። በርግጥ ሰው ሰግቶ ሊታመም ፣ ታሞም ሊሰጋ ይችላል ። እኔን ሳይሆን ገንዘቤን የሚወዱ ባለመድኃቶች ንብረቱ ሲያልቅ የእነርሱም የእግር ኮቴ እያለቀ መጣ ። እስካሁን ያልከዳኝ ዘመድ በሽታዬ ነው።

ከሩቅ የሰዎች ድምፅ ስሰማ እንደ ምንም ብዬ ከመኝታዬ ላይ ተነሣሁና በመስኮት ማየት ጀመርሁ ። ብዙ ሰው ይተራመሳል ። የሁሉም አትኩሮት ወደ አንድ ሰው ላይ ይመስላል ። ከፊት የሚሄዱም ወደ ኋላ እያዩ ይሄዳሉ ግን አይደናቀፉም ። መምህሩ እያየላቸው በድፍረት ይራመዳሉ ፤ በዝተው ይገፋፋሉ ፣ ነገር ግን አይወድቁም ። መምህሩ የወየበ ልብስ ለብሷል ። የአይሁድ ረቢዎች ተቀምጠው በወንበር ደቀ መዛሙርትን ፣ ቁመው በምኩራብ ሕዝቡን ያስተምራሉ ። ይህ መምህር ግን መቀመጫ ወንበር ፣ ማስተማሪያ ዐውደ ምሕረት አጥቶ ከሰሚዎቹ ጋር አብሮ እየተጓዘ የሚያስተምር በመሆኑ ልዩ ነው ። በድንገት ያ ሰልፈኛ ለሁለት ተከፈለ ። አንድ ሰውም ወደ መምህሩ ለመድረስ በተነጠፈ ምንጣፍ ላይ እንደሚሄድ ሹም ብቻውን መጓዝ ጀመረ ። ሁለት ሹማምንት ሲገናኙ ሰዎች በአንክሮ ይመለከታሉ ፤ ሁለቱም ሹም ቢሆኑም ኢያኢሮስ ግን የአጥቢያ አስተዳዳሪ ፣ መምህሩ ግን የአጽናፈ ዓለም ገዥ ነው ። ሁለት ነገሮች ድብልቅልቅ አሉብኝ። “የምኩራቡን አለቃ ኢያኢሮስን በአደባባይ ያቆመው ምንድነው?  ችግር የማያንኳኳው ቤት የለም ማለት ነው ?” ብዬ ማሰብ ጀመርሁ ። ከመምህሩም ጋር አጭር ንግግር ከተነጋገሩ በኋላ ጉዞ ወደ ኢያኢሮስ ተጀመረ። ኢያኢሮስ የጉዞውን አቅጣጫ ያስቀየረ ይመስላል ። የሚደንቀው ደግሞ መምህሩ ወደ ኢያኢሮስ ቤት አቅጣጫ እየነጎደ ነበር ። መምህሩ የኢያኢሮስን ጭንቀት ስላየ በአቋራጭ ለመሄድ አሰበ ። አቋራጩም የእኔ እርሻ ነበር ። ባለቤቱ ሲተኛ አጥሩም ይተኛልና አጥሩ የፈረሰውን እርሻዬን መምህሩ ማቋረጥ ጀመረ ። እርሱ ችግሬን እያቋረጠው ፣ የመከራዬን ጅረት ለሁለት እየከፈለው መሆኑ ተሰማኝ ። የሰዎች ድምፅ እየበረከተ ሲመጣ “መሢሑ ነው” የሚል ድምፅ በጆሮዬ ጥልቅ አለ ። የእኔም ቀን ደረሰ ማለት ነው ብዬ ራሴን ጠየቅሁት ። የከተማዋ መናኝ ፣ በሰው መሐል ያለ ሰው ያለሁ እኔን አድራሻ አድርጎ እንደ መጣ እንዴት እጠራጠራለሁ  ? አልጋው ራሱ እግሮቼን ሲተፋቸው ተሰማኝ ። በበር ለመውጣት ማርፈድ ሁኖብኝ በመስኮት ዘልዬ ወረድሁ ። መሢሑን ለማግኘት ከራስ ጋርም መምከር አያስፈልግም ። እርሱ ከራስ በላይ ነውና ።
በለበስኩት ልብስ የሰነበትኩ ነኝ ። መምህሩን በአዲስ ጨርቅ ሳይሆን በአዲስ ልብ መቀበል እንደሚያስፈልግ ገባኝ ። እኔም እንደ ኢያኢሮስ እየሮጥሁ ስመጣ ሁሉም መንገድ ይለቅልኝ ጀመረ ። ልዩነቱ ኢያኢሮስ ከፊት ሲመጣ እኔ ግን ከኋላ መምጣቴ ነው ። ልዩነቱ ለኢያኢሮስ መንገድ የተለቀቀው በአክብሮት ሲሆን ለእኔ ግን በንቀት ነው ። ታረክሰናለች ብለው ሸሹኝ ። ከክርስቶስ ጋር የሚውሉ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ናቸው ። መንገድ ለንጉሥም ለእብድም ይለቀቃል ። ንጉሡ ማን እንደሆነ እብዱም ማን እንደሆነ ግን የኅሊናት ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ያውቃል ። መምህሩ ይህ ሁሉ ሲሆን መንገዱን እየሄደ ነው ። እርሱ ለሹምም ለድሀም ያዝናል ። አንዳንድ ሰው ሐቀኛ የሆነ እየመሰለው ሹም አልወድም ይላል ፣ ሌላውም ድሀ ይጠላል ። እርሱ ግን ሁሉን ይወዳል ፣ ሁሉን ይቀበላል ። መንገዱን ሲለቁልኝ ደስ አለኝ ። ጉዳዬ ከእነርሱ ጋር ሳይሆን ከአዳኙ ጋር ነው ። እርሱ ደግሞ የሸሸውን የሚከተል እንጂ የሚከተለውን የሚሸሽ አይደለም ። በአልጋ የደቀቀው አካሌ እየዛለብኝ ፣ ትንፋሼ ቁርጥ ቁርጥ እያለብኝ ነው ። መምህሩ ጋር ለመድረስ ሰባት ጊዜ ያህል ወድቄአለሁ ። ሰባት ጊዜ ተነሥቼ አሁንም ወደ እርሱ እፈጥናለሁ ። በመጨረሻው ውድቀቴ የመምህሩን የኋላ ቀሚስ ዘርፍ ነካሁኝ ። ሳልጨብጠው ዳሰስኩኝ መምህሩ አንድ እርምጃ ሄደና ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ ሲመለስ እኔ ከወደቅሁበት ጋ ቆመ ። ፍቅርና ጽናት በተሞሉ ቃሎች ተናገረ ። ራሴን ሳዳምጠው ቀቢፀ ተስፋ በተስፋ ፣ በሽታ በመዳን ተለውጦ ተሰማኝ ። መዳኔ ለእኔ ተሰማኝ እንጂ የሰዎች ማረጋገጫ አላስፈለገኝም ። የአሥራ ሁለት ዓመት የደም ምንጭ ነጠፈ ፣ ጅረቱ ቆመ ።ደስታ ከእንባ ጋር ፣ ሲቃ ከእልልታ ጋር ተቀላቀለብኝ ። ሰግጄ እንዳለሁ ያ አዳኝ አንድ ቃል ሲያወጣ መንቀጥቀጥ ጀምርሁ፡-
“ልብሴን የዳሰሰኝ ማን ነው ?”
በዚያ ሁሉ ግፊያ ውስጥ የሚጋፋውንና የሚዳስሰውን ያውቃል ። የሚጋፉ በሽታ እንዳለባቸው የማይሰማቸው በጉልበታቸው ኮርተው የመጡ ናቸው ። የሚዳስሱ ግን በሽታቸውን ያመኑና ፈውስን የሚናፍቁ ናቸው የሚጋፉ ለዝና የመጡ ናቸው ፣ የሚዳስሱ ግን መዳንን የሚሹ ናቸው የሚጋፉ ይደክማሉ ግን ምንም አያገኙም ። የሚዳስሱ ግን በትንሽ እምነት ብዙ ፈውስን ያገኛሉ ። የሚዳስሱ ቅዱስ ፍርሃት ያላቸው የንስሐ ልብ የያዙ ናቸው ። የሚጋፉ ግን በትክክለኛነት ስሜት ሌሎችን የሚንቁ ናቸው ። የሚጋፉ ከጌታ አጠገብ የማይጠፉ ነገር ግን ከጌታ የራቁ ናቸው ። የሚዳስሱ ግን ጌታን ለማግኘት የመጡ ናቸው ። የሚዳስሱ ከጌታ እየበሉ ወደ ሰው የሚውጡ ወይም ለዝና የሚኖሩ ናቸው ። የሚዳስሱ ግን ለእግዚአብሔር የሚኖሩ ናቸው ። የሚጋፉ ደፋር ናቸው ። የሚዳስሱ ግን ፍቅርና አክብሮት የተሞሉ ናቸው ።
ጌታ ልብሴን የዳሰሰኝ ማነው ማለቱ ሊያጋልጠኝ ብሎ አልነበረም ። በሽታዬን ዓለም አውቆ እንዳገለለኝ መዳኔንም ሁሉ ሰምቶ እንዲቀበለኝ ነው ። ከበሽታዬ ፈውሱ ትልቅ ነው ። ከበደሌም ምሕረቱ አያል ነው ። ማንም ሊያቆመው ያልቻለውን የደም ጅረት ጌታ በልብሱ ዘርፍ አቆመው ። ትልቅ ያልሁት ችግሬ ለካ ለቀሚሱ ዘርፍም አይመጥንም ። የኤርትራን ባሕር በበትር የከፈለ ፣ የሰው እጅ በምታህል ደመና ሰማርያን ያረሰረሰ አምላክ በቀሚሱ ዘርፍ የደም ምንጬን አነጠፈው ። ችግሬን ሳይ እግዚአብሔር ተሰወረብኝ ፣ እግዚአብሔርን ሳይ ችግሬ ተሰወረ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ