የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነጠፈ ስቃይ

     ቤተ ጳውሎስ፤ ዓርብ ሚያዝያ 19 2004 ዓ.ም.
በየዕለቱ ልባችን ከሚደማበት ነገር አንዱ በሰዎች መካከል ልዩነት ሲደረግ ማየት ነው፡፡ አንዱን ማክበር መልካም ቢሆንም ሌላውን መናቅ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ደግሞ ከገረዴ ጋር እኩል በአንድ ወንበር ልቀመጥ እንዴ? ደግሞ ከማንም የድሀ ልጅ ጋር ልዋል እንዴ? የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን የአእምሮ ድሆች ናቸው፡፡ ከገንዘብ ድህነት የአስተሳሰብ ድህነት ይከፋል፡፡ ካጠቡት ሁሉም ንጹሕ፣ ካስተማሩት ሁሉም አዋቂ፣ ከደገፉት ሁሉም ጎበዝ ነው፡፡ እውነተኛ ክብር ከእውነተኛ ፍቅር ይገኛል፡፡ እውነተኛ ፍቅር ደግሞ በደሳሳ ጎጆ ከድሆች ጋር በመዋል ይረካል፡፡ አላወቅነውም እንጂ ድሆች ክብሮቻችን፣ ደስታዎቻችን፣ እውነተኛ ወዳጆቻችን ናቸው፡፡ ባለጠጎች ያላቸውን፣ ድሆች ራሳቸውን ይሰጡናል፡፡ ጌታችን እንኳ ሰማይ ምድርን በመስጠት ባለጠግነቱን ገለጠ፣ ራሱን በመስቀል ላይ ቢሰጥ የማይተረጎም ፍቅሩን ገለጠልን፡፡ በምድር ላይ እውነተኛ ወዳጆች ድሆች ናቸው፡፡ ሌላው ግን የእኩያ ኑሮ፣ የብድር ሕይወት ነው፡፡ 
ይልቁንም በእግዚአብሔር ቤት ድሆችና ባለጠጎች ሲለዩ ማለት ያሳፍራል፡፡ ከሥጋ አልፎ የነፍስ ደረጃ ያወጣን ይመስላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ታዋቂ ሰው ሲድን ለወራት እልል እንላለን፡፡ የአንድ ምስኪን መዳን ግን አይታየንም፡፡ ደግመንም ማሰብ አንፈልግም፡፡ ነፍስ ግን አይበላለጥም። በርግጥ በሙያቸውና ለወገናቸው ባደረጉት አስተዋጽኦ ሊከበሩ የሚገባቸው ሰዎች አሉ፣ ምንም ባለሥልጣንና ባለጠጎች ቢሆኑ ለራሳቸው ኖረው ያለፉ ግን እውነተኛ ክብርን አያገኙም፡፡ እኛ ክቡር ብንልም እግዚአብሔር ማኅተሙን ካላሳረፈበት ሕጋዊ ማዕረግ አይደለም። ክብር ከእግዚአብሔር ነው፡፡

በዓለም ትልቁ ክቡር ፍጥረት ሰው ነው፡፡ ከማዕረግ ክብር የሰውነት ክብር ይበልጣል፡፡ ሌሎች ካከበሩትም መልካምነቱ ያከበረው ይበልጣል፡፡ የማይሻር ሹመት፣ የማይወልቅ ዘውድ መልካምነት ነው፡፡ ትልቁ ክቡር ፍጥረት የምድሪቱ ባለ አደራ የሰው ልጅ ነው፡፡ ሰው በሰውነቱ ብቻ ክቡር ነው፡፡ አንድ ሎሌ ከንጉሡ የሚለየው በኃላፊነት ድርሻ እንጂ በሰውነት አይደለም፡፡ ሰው ክቡር መሆኑን ስናምን ሕጻኑንም ሆነ ሽማግሌውን፣ ድሀውንም ሆነ ባለጠጋውን እናከብረዋለን፡፡ ሰው ክቡር ነው የሚባልበት መሠረቱ ሰው በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረ፣ በክርስቶስ የደም ዋጋ የተገዛ መሆኑ ነው፡፡ ሰውነት በሌለበት ታላቅነትም ሆነ ማዕረግ እንዲሁም ጀግና መባል የለም፡፡ ሰውን ማክበር በተዘዋዋሪ ራስን ማክበር ነው፡፡ በሌሎች የመወደድ ምሥጢሩ ሌሎችን ቀድሞ መውደድ ነው፡፡ በሌሎች የመከበር ብልሃቱ ሌሎችን በእውነት ማክበር ነው፡፡ 
ጌታችን ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለሰው ልጆች እንጂ ለእነ እገሌ አይደለም፡፡ ከሰማይ የሳበው የሰው ፍቅር እንጂ ከነገሥታት ጋር ሊወያይ አይደለም፡፡ ያን ቢመርጥ ኖሮ በበረት ከመወለድ በመቅደስ ይወለድ ነበር፡፡ ካህናተ አይሁድ ሳሉ እረኞችን በልደቱ ደስታ አይጋብዝም ነበር፡፡ ከመቅደስ በረት፣ ከሊቃውንት እረኞች በልጠዋል፡፡ የእግዚአብሔር ሚዛኑ ከሰው ይለያል፡፡ ጌታችን ሲጮኹ ይቆም የነበረው ለአለቆችም ለጭፍሮችም ነበር፡፡  
በማርቆስ 5÷21 ላይ ኢያኢሮስ የተባለ የምኲራብ አለቃ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና ድረስልኝ ብሎት ይዞት ሲሄድ አንዲት ከ12 ዓመት ጀምሮ ደም ይፈስሳት የነበረች ሴት በመንገድ ላይ አቆመችው፡፡ ለኢያኢሮስ እንደቆመ ለእርሷም ቆመላት፡፡ ትንንሾች የሚመስሉን ትልቅ አምላክ አላቸው፡፡ እኛስ ሚዛናችን፣ ሰዎችን የምንቀበልበት መስፈርታችን ምን ይሆን? 
ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ አንድ ሰው መጥቶ “አባታችን የፊታውራሪ እገሌ የልጅ ልጅ ናት እኮ ይተዋወቋት” ቢላቸው፡- “ጎጠኛ! የክርስቶስ ከሆነች ይበቃኛል” አሉት ይባላል፡፡ እኛስ የክርስቶስ ከሆኑ ይበቃናል?
ጌታችን ወደ ኢያኢሮስ ቤት እየተጓዘ ሳለ አንዲት መከረኛ ገጠመችው፡፡ እርሱ የሚያገለግልበት የተለየ ሰዓትና ቦታ አልነበረውም፡፡ በመንገድም በሜዳም በቀንም በሌሊትም ያገለግል ነበር፡፡ አገልግሎቱ ሥራ ሳይሆን ሕይወቱ ነበርና። ቃሉ እንዲህ ይላል፡-
“ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፡ ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሣቀየች ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ (ማር. 5÷25-26)፡፡ 
እንደ ብሉይ ኪዳን ሕግ ከሰውነት ፈሳሽ የሚወጣበት ሰው እንደ ርኩስ ይቆጠር ነበር፡፡ ስለዚህ ይህች ሴት ከዐሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ በሚፈሳት ደም እንደ ርኩስ ተቆጥራ በሃይማኖት አዋጅ ተለይታ ትኖር ነበር፡፡ ሰዎችም ከእርሷ በመራቃቸው ለእግዚአብሔር እንደ ታዘዙ ይቆጥሩ ነበር፡፡ ሕጋዊ ከዳተኞች ነበሩ እንደ ማለት ነው። “ሃይማኖት የለየንን መቃብር አንድ አያደርገንም” የሚል መመሪያና መጽሐፍ ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ወጥቶ ነበር፡፡ ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ያለን ጠብ እስከ መቃብር እንዲቀጥል ታውጆ ነበር፡፡ ሕጋዊ ጥላቻ ግን ሊኖር አይችልም፡፡ አስተሳሰቡን አለመቀበልና ሰውዬውን አለመቀበል ሰፊ ልዩነት አለው፡፡ 
በአዲስ ኪዳን ሰው ርኩስ የሚባለው በበሽታ ሳይሆን በመጥፎ ሥነ ምግባር ነው፡፡ የተፈጥሮ እንከን ሳይሆን የጠባይ እንከን ኃጢአት ነው፡፡ ከሰውነት ፈሳሽ የሚወጣ ከሆነ በግድ መጥፎ ጠረን መኖሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ይህች ሴት በሃይማኖት አዋጅ ባትለይም ራሷን በግድ ትለይ ነበር፡፡ ማንም ሰው ለደቂቃ አብሯት አይቀመጥም ነበር፡፡ የአይሁድ እምነት ተከታይ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖት የሌለውም የሸሻት ሴት ነበረች፡፡ ከአማኝ አልፎ የማያምነውም የሚጠየፈን የመናቅና የመረሳት ዘመን አለ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ነገርን ሲለውጥ ዝም ሳትሉ ተናገሩ፣ ሳታሰልሱ ወደ እኛ ኑ እንባላለን፡፡ የሕይወትን ተራ በትዕግሥት መጠበቅ፣ ክብሩን እንደቻሉ ውርደቱንም መቻል በእውነት ይገባል፡፡ ይህች ሴት የቤቷንና የአካባቢዋን ቆሻሻ ማጽዳት ትችላለች፡፡ ከውስጧ የሚወጣውን ግን መቆጣጠር በፍጹም አትችልም፡፡ ለሌሎች መለወጥ ምክንያት የሆኑ ራሳቸው ግን የቆሸሹ ሰዎችን ታስታውሰናለች፡፡ አካባቢያቸውን እያፀዱ፡ ሜዳዊ ቅድስና /የሥርዓት ጠንቃቃነት እየታየባቸው ከውስጣቸው ግን ብዙ ክፋት የሚወጣባቸውን ሰዎች ታሳየናለች፡፡ በሰዎች ላይ የበላይ ሆነው በፍላጎታቸው ላይ ግን የበላይ መሆን ያቃታቸውን ሰዎች እንድናዘክር ታደርገናለች፡፡ 
ይህች ሴት በሽታ የሚያመጣውን ተጽእኖ ሁሉ ተሸክማለች፡፡ ኅሊናዋ ተጎድቷል፣ መገለል ደርሶባታል፣ ገንዘቧ ተራግፏል፣ ማኅበራዊ ግንኙነቷ ተበላሽቷል፣ የሐኪም መለማመጃ ሆናለች፡፡ ሐኪም በልቶ በልቶ ዋጋ የለሽም ብሎ ሸኝቷታል፡፡ ሰው የጉልበት አቅሙን ቢያጣ እንኳ የገንዘብ አቅም ካለው ውሰዱኝ ይላል፡፡ የገንዘብ አቅሙ ከተሟጠጠ ግን ጉልበት እያለውም ይቀመጣል። ይህች ሴት ማጣቱ ቁጭ ብላ የሚመጣውን ጥፋት በጀግንነት እንድትጠባበቅ አድርጓታል፡፡
ደም መፍሰስ እንደ ቀላል የምናየው ነገር አይደለም፡፡ እኛ ለአንድ ሙሉ ቀን እንኳ ቢነስረን ምን እንደሚሰማን እናውቃለን፡፡ ከአክታችን ጋር ደም ቀላቅሎ ሲወጣ ልባችን ምቱን ይጨምራል፡፡ ይህች ሴት ግን ለአሥራ ሁለት ዓመት የደም ምንጯ ተነድሎ ላይቆም ይወርድ ነበር፡፡ ቆማ መሄዷ በሕይወት መኖሯ አስደናቂ ነው፡፡ ሞት በጥሪ እንጂ በበሽታ አለመሆኑን ይህች ሴት ትናገራለች፡፡ 
የሚሰጣት መድኃኒት ሁሉ በሽታዋን አላገኝ እያለው ያላመመውን አካሏን መድኃኒቱ ያጠቃው ጀመር፡፡ መድኃኒት መድኃኒት አልሆንልሽ ያላት በተቃራኒው የመድኃኒቱን ክፉ ጦስ የተሸከመች ሴት ነበረች፡፡ ሐኪሞችም እንደማይችሉት እያወቁት ገንዘቧን እስክትጨርስ በከንቱ ተስፋ እያታለሉ ይዘርፏት ነበር፡፡ ክፉ ሐኪሞች በዓለም የመጀመሪያዎቹ ወንጀለኞች መሆናቸውን ማን ባወቀ። የጨከነ ሐኪም ከጨከነ ሽፍታ ይከፋል፡፡ በአገራችን ወይ መድኃኒት ወይ መልካም ቃል የሌላቸውን ብዙ የተበላሹ ሐኪሞች እያየን ነው፡፡ ያልታከሙ ሐኪሞች ወረርሽኝ ናቸው። ሕክምና ሰብአዊ ርኅራኄ፣ የቃል ኪዳን ተግባር መሆኑ ቀርቶ በሬሣ ላይ የሚኖሩበት ሆኗል፡፡ ብዙ ወገኖቻችን በሐኪሞች ተስፋ አስቆራጭ ድምፅ እያጣጣሩ ከበሽታው በላይ ሐኪም ያሳመማቸው እንደሆኑ እያየን ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን በሐኪም ልክ እንዴት ለካነው?  ሐኪም የማይችለውን እግዚአብሔር ይችላል፡፡ እግዚአብሔርን የምናምነው ሰው እስከሚችለው መፍትሔ ድረስ ከሆነ ምኑን እግዚአብሔር ሆነ?  ሰው የማይችለውን የሚችል ጌታ ስለሆነ ብቻ እግዚአብሔር ነው፡፡ 
ከጭንቀታቸው የተነሣ ወደ ቤተክርስቲያን የመጡ ነገር ግን ለገንዘብ ባደሩ አምጡ እንጂ እንኩን በማያውቁ አገልጋዮች ያዘኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሐኪሙ አሳማሚ ከሆነ ከባድ ነው፡፡ አባት ያሉት ልጁን ለዝሙት ከተመኘ፣ ወንድም ያሉት አገልጋይ ወንድም ጋሻ መሆኑ ቀርቶ ዘርፎ ከጠፋ ከባድ ነው፡፡ ሕዝባችን እውነተኛ አገልጋዮችን በስማ በለው ሲገፋ ኖሯል፡፡ የሐሰተኞች ድምፅ ማጉያ ሆኖ ሊቃውንቱን ስም እየሰጠ ሲያጠፋ ስለኖረ ዛሬ ያሉት ብዙ አገልጋዮች ቅጣቶቹ ይመስላሉ፡፡ ብርሃንን ከጠላን ጨለማ ይሰለጥናልና ይኸው የጨለማ ሠራዊት፣ እግዚአብሔርን የማይፈሩ፣ ሰውን የማያፍሩ አገልጋዮችን አፍርተናል፡፡ 
ያች ሴት በሐኪም ተስፋ የቆረጠች ሴት ነበረች፡፡ ድካሙ አልቀረላትም፡፡ ፈውሱ ግን ደረስኩ እያለ ይሸሻል፡፡ የእኛ ሲያልቅ የእግዚአብሔር ይጀምራል፡፡ ያች ሴት ተስፋ ቆርጣ፣ የትም ላልሄድ ብላ ተቀምጣ፣ ዘጠኝ ሞት ቢመጣ አንዱን ግባ በሉት ብላ ፎከራ ሳለ ጌታ ኢየሱስ በመንደሯ እንደሚያልፍ ሰማች፡፡ እርሱ ቃሉ፣ መዳሰሱ፣ መድኃኒቱ ሳይሆን ልብሱን ብዳስሰው እድናለሁ ብላ አመነች፡፡ በብዙ ሐኪሞችና መንፈሳዊ አገልጋዮች አዝና ሳለ የደስታ ምንጭ የሆነው ሐኪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንደሯ አለፈ፡፡ እርሱ የበሽታ ብቻ ሳይሆን የሞትም መድኃኒት ነው፡፡ ትልቁ ሐኪም እርሱ ነው፡፡ እጁ የሚያነሣ፣ ቃሉ የሚፈውስ ልዩ ባለመድኃኒት ነው፡፡ 
ቃሉ እንዲህ ይላል፡- “የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች፡- ልብሱን ብቻ የዳሰሰሁ እንደሆነ እድናለሁ ብላለችና፡፡ ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቅ ከሥቃይዋም እንደ ዳነች በሰውነትዋ አወቀች”(ማር. 5÷27-29)፡፡ 
ይህች ሴት መምጣቷን ቢያውቁ ኢየሱስን የከበቡት ሰዎች ሁሉ እንዳትነካቸው ይሸሹና ካለፈም በድንጋይ ወግረው ይገድሏት ነበር፡፡ የእነርሱ ቅድስና ሰዋዊ ቅድሰና በመሆኑ ይረክሳል፡፡ አምላካዊ ቅድስና ያለው ጌታችን ኢየሱስ ግን የረከሱትን ይቀድሳል፡፡ የሚለውጥ እንጂ የማይረክስ ቅድስና ያለው አምላካችን እንዴት ድንቅ ነው!ከኢየሱስ ጋር የሚራመዱ ነገር ግን የማይከተሉት፣ የሚያጅቡት ነገር ግን የማያምኑት፣ የሚያጋፉት ነገር ግን የማይድኑበት ዛሬም አሉ፡፡ በመንፈሳዊ ቦታ የተቀመጡ ነገር ግን መንፈሳዊ ያልሆኑ ሰዎች ለብዙዎች የልብ ድካም ሆነዋል፡፡ ሰዎች ወደ ክርስቶስ መጥተው እንዳያርፉ እንቅፋት የሆኑ ወይ ነክተውት አይድኑ ወይ መንገድ ለቅቀው ሌሎችን አያድኑ ምሳሌ የሌላቸው ሰዎች ዛሬም አሉ፡፡ እነ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሲገሰግሱ ጨለማው፣ ገዳዮች፣ የሮማ ወታደሮች አላስፈራቸውም፡፡ የልባቸው ስጋት ድንጋዩን ማን ያንከባልልልናል? የሚል ነበር /ማር. 16፡3/፡፡ ዛሬም በእውነት ከዘመኑ ጨለማነትና ከመንግሥታትም ሃይማኖት የለሽነት የተነሣ የደረሰብን ጉዳት የለም፡፡ ጌታን እንዳናገኝ የተገጠሙ ድንጋዮች ግን የልባችን ስጋት ናቸው፡፡ ክርስቶስ ግን ድንጋይ ሳይዘው ከመቃብሩ በላይ እንዳበራ ይኖራል፡፡ 
ይህች ሴት ለእኔ ችግር መፍትሔው ትልቅ አይደለም፡፡ ከክርስቶስ ትልቅነት የተነሣ ችግሬ እንኳን ለእርሱ ለለበሰው ልብስም ቀላል ነው ብላ አመነች፡፡ አዎ በበትር ባሕር የከፈለ አምላክ እንደሆነ አውቃለች፡፡ ኢየሱስን ባላሰበችበት ዘመን ችግሯ ትልቅ ነበር፡፡ የክርስቶስን ክብር ስታስብ ግን ችግሯ አነሰባት፡፡ ለእኛ የከበደ ለጌታ ግን ቀላል ነውና ክርስቲያኖች ተጽናኑ!
የእርሷ ርኩሰት ጌታ ኢየሱስን አላረከሰውም፣ የእርሱ ቅድስና ግን ፈወሳት፡፡ ኃጢአተኞች ሸሽተዋት ነበር ቅዱሱ ግን ተቀበላት፡፡ ሁሉ ገፍተዋት ነበር፡፡ ጌታ ግን ልጄ አላት፡፡ በደዌያትና በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ጌታ ያሸነፋትን አሸነፈላት፡፡ እንደዳነች ሰዎች አልነገሯትም፣ ለራሷ ተሰማት። እውነተኛ መዳን በመጀመሪያ ለባለቤቱ ይሰማዋል፡፡
የነጠፈ ስቃይ
ዛሬስ አልቆም ብሎ የሚወርደው የሥቃይ ጅረት ምን ይሆን? ብዙ ሞክረን መፍትሔ ያጣንለት፣ ይህ ነገርስ ካልገደለኝ አልገላገለውም ያልንለት ታጋያችን ምን ይሆን? መድኃኒት ስንፈልግለት ለተጨማሪ በሽታ የዳረገን ወለድ ያለው መከራችን ስሙ ማን ይሆን? የራሱ ችግርነት ሳያንስ ለሌላ ችግር አሳልፎ የሰጠን፣ ለጠንቋይ ለቃልቻ፣ ለሐሳዊ መምህራን አሳልፎ የሰጠን ችግራችን ምን ይሆን? 
ከሙከራ በላይ፣ ከገንዘብ በላይ፣ ከሐኪም በላይ የሆነ ችግር ክርስቶስን በማመን ይወገዳል፡፡ ክርስቶስ በመንደራችን እያለፈ ነው፡፡ በታሪካችን የሚመዝኑን ሰዎች እርሱን ብንከተለው ይነቅፉናል። ደግሞ በዚህ መጣችሁ ይሉናል፡፡ እርሱ ግን በታሪካችን አይመዝነንም፡፡ እርሱ ከማረን የሚከሰን የለምና እንከተለው፡፡ የእርሱን ቃል ስንሰማ ወደ ቤታችን ተጠግቷል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሩን ከፍተን ግባልኝ እንበለው፡፡ ቤቱን እስክናስተካክል ያልፋል፡፡ ዝም ብለን እንክፈትለት፡ አስተካክሎ በቤታችን ይነግሣል፡፡ ቤቱ ጨለማ ከሆነ እርሱ ብርሃን ነው፡፡ ቤቱ ጣዕም አልባ ከሆነ እርሱ የሕይወት ቅመም ነው፡፡  መከራዬ ኩሬ ቢሆን ያልቃል፣ ምንጭ ነውና ተቀድቶ አያልቅም አትበሉ። ክርስቶስን ስንነካው የሥቃይ ምንጭ ይነጥፋል። ክብር ምስጋና ለጌታችን ይሁን። አሜን፡፡     
    
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ