ምዕራፍ ዐሥራ አራት – የእንጀራ ዋስትና
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ዐቢይ /ትልቅ/ ጾም ሲባል ያስተማረውም «የአቡነ ዘበሰማያት» ጸሎት ትልቅ ጸሎት ይባላል፡፡ አባታችን ሆይ ብዙ የተጻፈለት ብዙ ተርጓሚዎች ያፍታቱት ቢሆንም የምሥጢሩ ጥልቀት፣ የፍቅሩ ትንታኔ ዛሬም የማይጠገብ ነው፡፡ አባታችን ሆይ ደጋግመን ከምንጸልየው ይልቅ እንደ ጸሎት ትምህርት ቤት ብንማርበት የተሻለ ነው፡፡ ጸሎቱ ብዙ ነገሮችን አካቷል፡፡ ምሥጋና፣ ጸሎት፣ ንስሓ፣ ምልጃን አጠቃሎ ይዟል፡፡ የጥንት አባቶች የልመናውን ይዘት እንዲህ ያቀርቡት ነበር፡፡ ለምሳሌ፡– «የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን» የሚለውን «በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን መንግሥት ያንተ ናትና ለዘላለሙ አሜን፤» ይላሉ፡፡
ከፊት ምስጋናውን እንደ አዝማች ማድረጋቸው ልመናን የምትቀበለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማወደስ ሲሆን መዝጊያው መንግሥት ያንተ ናትና መሆኑ ደግሞ የዕለት እንጀራ የሚሰጠን በመንግሥቱ ሥልጣን መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ የአባታችን ሆይ ጸሎት ነፍስን ብቻ ሳይሆን ሥጋንም ይመለከታል፡፡ እግዚአብሔር የነፍስና የሥጋ ፈጣሪ ነውና የነፍስና የሥጋ መሻታችንን የሚፈጽምልን እርሱ ነው፡፡ ለዚህ ነው በታላቁ ጸሎት «የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን» (ማቴ.6፣11) ብለን እንድንጸልይ የታዘዝነው፡፡
የቋጠሩት ስንቅ ያልቃል፣ የስሙ ስንቅ ግን አያልቅም፡፡ በጎተራ ያከማቹት በዘገኑለት ቍጥር ይቀንሳል፡፡ ከሰማይ ግምጃ ቤት የሚሰፍሩ ግን አያልቅባቸውም፡፡ ገንዘብ ያከማቹ ይደኸያሉ፣ እግዚአብሔር አለኝ የሚሉ ግን በረከታቸው ከዘመን ዘመን ይሻገራል፡፡ እግዚአብሔር እርሻ እየታየ ይመግባል፣ እርሻ ሳይታይም ያኖራል፡፡ ደመና አዙሮ ያዘንባል፣ በጠራራ ፀሐይም ማዝነብ ይችላል፡፡ 3 ዓመት ከ6 ወር የደረቀችውን የሰማርያን ምድር ያረካት እጅ በምታህል ደመና ነው፡፡ ለእኛ ትልቅ የሆነው ጉዳይ ለእርሱ አቅም ትንሽ ነው፡፡ እርሱ ለመንገዱ ፍለጋ የለውም፡፡ በታሪክ የተጠና፣ በሊቃውንት የተረጋገጠ የእግር ፈለግ የለውም፡፡ በየብስ ሲጠብቁት በባሕር መጥቶ ይረዳል፡፡ ሁላችንም ለተፈጥሮ ሕግ ተገዝተናል፡፡ እርሱ ግን ከተፈጥሮ ሕግ በላይ ይሠራል፡፡ የእግዚአብሔርን የበረከት እጆች ከተለማመድን የስሌት ኑሮ መልመድ ያቅተናል፡፡ አዎ «የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን» መባሉ እውነት ነው፡፡
የዓለማችን የሚሆነው ሕዝብ ደሃ ነው፡፡ የዓለማችን ሀብትም ያለው በሚያህሉ ሰዎች እጅ ነው፡፡ ከአንድ ቀን በላይ የማያውል በረከት ያላቸው ሕዝቦች እልፍ ናቸው፡፡ አንድ ቀን እቤታቸው ከዋሉ የሚራቡና የሚሞቱ ቍጥር የላቸውም፡፡ እነዚህ ሁሉ ድሆች በምንድነው የሚኖሩት? ስንል በተአምራት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረትን ስለ ቃል ኪዳኑ ያኖራል፡፡ ከገቢያችን በላይ በሆነ ወጪ እግዚአብሔር ሲያኖረን አይተናል፡፡ እግዚአብሔርን በቃሉ ስንፈልገው፣ በእምነት ስንጠብቀው እናገኘዋለን፡፡ እርሱ እንዳወቅነው ሳይሆን እንዳመነው ነው፡፡ «የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን»
እንጀራን ሁሉም ሰው ይፈልጋል፡፡ የእንጀራውን አድራሻ ግን የሚያውቅ ጥቂት ነው፡፡ እንጀራ ተዘርቶ፣ ታጭዶ፣ ባለ ሙያ ሴት አሰናድታ የምታቀርበው የሚመስለው ሰው ብዙ ነው፡፡ እንጀራ ግን ከሰማይ ነው፡፡ በየዕለቱ እንጀራን የሚሰጠን እግዚአብሔር ነው፡፡ የፍላጎቶቻችን ሁሉ ሙሉ መልስ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ እግዚአብሔር የፍላጎታችን ንጉሥ ነው፡፡ እርሱ ለነፍሳችን እንደሚያስብ ለሥጋችንም ያስባል፡፡ ይልቁንም የምንፈልገው ከእግዚአብሔር አቅም በላይ ስላልሆነ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የእጁን ሳይሆን ልጁን ሰጥቶናል፡፡ የእጁን የዘገኑ ይጎድልባቸዋል፣ ጸጋውን የወሰዱ ያልቅባቸዋል፡፡ ባለጸጋውን የያዙ ግን ምንም አይጎድልባቸውም፡፡ እግዚአብሔር ጸጋውን ፍለጋ በደርሶ መልስ እንድንኖር ፈቃዱ አይደለም፡፡ ራሱን ሊሰጠንና ወደ በረከትነቱ ምንጭ ሊያስጠጋን ይፈልጋል፡፡ ያዕቆብ ሲሰደድ የበረከቱ አድራሻ ወደ ሆነው ጌታ ጸለየ፡– «እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ እግዚአብሔር አምላክ ይሆንልኛል፤… ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ» (ዘፍ.28፣20–22)፡፡
«የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን» ስንል ግዙፉን እንጀራ ብቻ ሳይሆን የዕለት ቃልህንም ስጠን ማለታችን ነው፡፡ እግዚአብሔር የዕለት መና አለው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ወይም ቃሉን በመስማት የዕለት እንጀራችንን እንቀበላለን፡፡ በእንጀራ ብቻ መኖር የተሟላ አይሆንምና የዕለት ቃልህን ስጠን ማለት ያስፈልጋል፡፡
የዕለት እንጀራችንን ስጠን ከማለት የዓመት ቀለባችንን ስጠን ማለት አይቀልም ወይ? ነገሥታት እንኳ በጀት የሚባጅቱት በዓመት ነው፣ በንጉሥነት የሚኖረው እግዚአብሔር ለምን በየዕለቱ ለምኑ አለ ብንል እርሱ ፈቃዱ ሕይወትን ዕለት በዕለት እንድንኖራት በመሆኑ ነው፡፡ ከዛሬ አልፈን ስለ ነገ እንድናስብ ፈቃዱ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ስለ መኖራችን እናስብ፡፡ ከዚያ በኋላ ስለ መኖሪያው እናስብ፡፡ መጀመሪያ ለመኖራችን ዋጋ እንስጥ፡፡ ከዚያ በኋላ ፍላጎታችንን እግዚአብሔር ይሞላልናል፡፡
የምንኖረው ኑሮ በትላንትናና በነገ መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ነው፡፡ የትላንት ትዝታ የነገ ፍርሃት ዛሬን እንዳንኖር አድርጎናል፡፡ ሕጻናት ደስተኛ ከሚሆኑበት ነገር አንዱ ሕይወትን በሰዓቱ ስለሚኖሯት ነው፡፡ ትክክለኛ የሕይወት መልክ ያለንበትን ቀን መኖር ነው፡፡ ነገ በደኅንነት ሠራተኞች ጥልቅ ምርመራ፣ በፖለቲካ ተንታኞች ግምት፣ በአስተዋይነትም አትታወቅም፡፡ ነገ የእግዚአብሔር ምሥጢር ናት፡፡ እግዚአብሔር ስለ ነገ ያልገለጠልን የምንለውጠው ነገር ስለ ሌለ ነወ፡፡ የጨበጥናትን ዛሬን መኖር እያቃተን ስለ ነገ መጨነቅ ድካም ነው፡፡ የብዙዎቻችን ፍርሃት ራበኝ
ሳይሆን ሊርበኝ ነው የሚል ነው፡፡ ነገ ምን እንደምንሆን አናውቅም፡፡ ዛሬን እንድንኖር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡
ሳይሆን ሊርበኝ ነው የሚል ነው፡፡ ነገ ምን እንደምንሆን አናውቅም፡፡ ዛሬን እንድንኖር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡
«የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን» ብለን መጸለያችን የእንጀራችን አድራሻ አንተ ነህ፣ የእንጀራችን ባለቤቱ አንተ ነህ ማለታችን ነው፡፡ እንጀራ የሚሰጡን ተስፋ የሰጡን ወይም ስልኮቻቸውን የመዘገብናቸው ትልልቅ ሰዎች አይደሉም፡፡ እነዚህ ጌታን እንዳናይ እንቅፋቶች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ካልሰጠ እንኳን ሰው መልአክ አይሰጥም፡፡ ሰዎች ብዙ አድርገውልን ይሆናል፡፡ ስለ እኛ እንቅልፍ የነሣቸው ግን እግዚአብሔር ነው፡፡ ውለታ አንረሳም፣ ሰጪ ግን እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው ሰጠን ብለን አንናገርም፡፡ መስጠት የሰው ባሕርይ አይደለምና፡፡
ከእግዚአብሔር መንግሥት ለእያንዳንዳችን የዕለት በጀት አለን፡፡ አንዱ የአንዱን በጀት አይበላም፡፡ የአንዱ በጀት ለአንዱ አይሆንም፡፡ የየራሳችንን ድርሻ እንቀበላለን፡፡ ይህ ቢገባን ኖሮ እግዚአብሔር ሰጥቶ የሚነሣን፣ እግዚአብሔር ነሥቶን የሚሰጠን እንደ ሌለ እንረዳ ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ቅንዓትና ምቀኝነት በራቀልን ነበር፡፡ «ስጠን» እግዚአብሔርን እንቀበለዋለን እንጂ አንነጥቀውም፡፡ «ስጠን» እርሱ የስጦታ አምላክ ነውና አበድረኝ አንለውም፡፡
«ዛሬ ስጠን» የእኛ የምንላት ቀን ዛሬ ናት፡፡ የእኛ በምንላት ቀን እግዚአብሔር ያስብልናል፡፡ የተፈጥሮ ተግባራችንን እንፈጽምባታለን፡፡ እንሮጥባታለን፡፡ የእኛ ቀን ዛሬ ናት፡፡ ነገ የእኛ አይደለችም፡፡
«ስጠን» የስጦታ ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡ ያዕቆብ «በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ» (ያዕ.1፣17) ይላል፡፡ «እንጀራ ስጠኝ» ሁሉም ሰው እንዲህ አይባልም፡፡ ምንም ቢርብ እንጀራ ስጡኝ ለማለት ክብር ይይዘናል፡፡ እንጀራ ስጪኝ ስንል የማናፍረው እናታችንን ነው፡፡ እግዚአብሔርም እናት ነውና እንጀራ ስጠኝ እንለዋለን፡፡ እንጀራ የበሰለ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ያለቀለት በረከት አለው፡፡ ብዙ ዘመን አጉርሶናል፡፡ የእጁም ጠረን ይሸተናል፡፡
ዳግማዊ ሚኒልክ ሁልጊዜ ሲያልፉባት በብዙ በረከት የምትቀበላቸውን አገር «ምን ልበልሽ ማጀቴ ብዬሻለሁ» ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በሸዋ ውስጥ ማጀቴ የምትባል ከተማ አለች፡፡ እግዚአብሔር ማጀታችን ነው፡፡ ማጀት ምግብ የሚሠናዳበት ማእድ ቤት ነው፡፡ ማጀት በድብቅ ነው፣ በአደባባይ የቁንጅና ውድድር የሚወዳደሩት ግን በእርሱ ነው፡፡ ማጀት ሲያዩት አያምርም፡፡ የብዙ ሽቅርቅሮች ምሰሶ ግን እርሱ ነው፡፡ በድብቅ የለመኑትን በአደባባይ የሚመልስ እግዚአብሔር ማጀታችን ነው፡፡ በማጀት አንድ ነገር አይታጣም፡፡ ከእግዚአብሔርም አይታጣም፡፡ የጸሎታችን መልሱ ገና ቢሆን እንኳ ሌላ በረከት አስታቅፎ ይሸኘናል፡፡
የእንጀራውን አድራሻ የማያውቅ በልቶ ካጅ፣ የሰውነት ክብር የተለየው፣ ምስጋና የማያውቅ ነው፡፡ አይሁዶች «ተቀብሎ የማያመሰግን ከቀማኛ ይቆጠራል» ይላሉ፡፡ ሃያ ሠላሳ ዓመት እድሜ ለእገሌ እርሱ እዚህ ቦታ ባይተክለኝ ኖሮ እያሉ የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ ሰዎች ምክንያት ሆነው በዚያ ቦታ ላይ እንድንቀመጥ አስተዋጽኦ አድርገው ይሆናል፡፡ እነርሱ ግን ሎሌ ናቸው፣ ያስቀመጠን እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው ይነቅለኛል ብለን የምንፈራው ሰው ያስቀመጠን ስለሚመስለን ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ብናምን ግን የእርሱን ስጦታ ነገሥታት እንኳ በጉልበታቸው እንደማይነጥቁን ይገባናል፡፡
«የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን» ልመናው የኅብረት ነው፡፡ የዕለት እንጀራዬን አይልም፡፡ እኛ ስንበላ ጎረቤታችንም መብላት አለበት፡፡ እኛ እንጀራ ስናገኝ ጎረቤታችንም ማግኘት አለበት፡፡ እኛ እየበላን ጎረቤታችን ካልበላ ደስታችን ሙሉ አይሆንም፡፡ ከበላነው በኋላ አይጣፍጠንም፡፡ በሽታ ሆኖ ያሰቃየናል፡፡ ከላይ የሚያየው እግዚአብሔር እኛ ቤት ያለውን ጥጋብ፣ ጎረቤታችን ቤት ያለውን ረሀብ በእኩል ዓይን ሲያይ ያዝንብናል፡፡ እግዚአብሔር በኑሮአችን ሲያዝንብን ደግሞ ደስታና ኃይል እናጣለን፡፡ ለሰዎች እንጀራን መለመን ብቻ ሳይሆን ማካፈልም ያስፈልጋል፡፡ እንጀራ ስንጋግር አንዱን አጥፈን ለጎረቤታችን መስጠን አለብን፡፡
በዚህች ከተማ ላይ ብዙ ድሆች በባለጠጎች ግርማዊ አጥር ተሸፍነው ያቃስታሉ፡፡ አንድ ቀን ከቤት ካልወጡ የሚሞቱ፣ እስከ ማታ የማይቆዩ ብዙ ጎስቋሎች አሉ፡፡ የክረምቱን ዝናብ የሚከላከሉበት የሌላቸው ልጆቻቸውን የብረት ምጣድ አልብሰው የሚያሳድሩ ብዙ ወላጆች አሉ፡፡ በዚህች በአዲስ አበባ ውስጥ ገላቸውን ሽንት ቤት በሚለቀቅባቸው ወንዞች የሚታጠቡ ብዙ ጎልማሶች ይታያሉ፡፡ የዚያን ያህል ደግሞ ውሾች በሻንፖ ይታጠባሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ እያሉ እንዴት ደስ ይለናል? እንዴት በልተን እንጠግባለን? እንዴት ለብሰን እንደምቃለን? እነዚህ ድሆች በእግዚአብሔር ፊት ይከሱናል፡፡ የድሆች ድርሻ ነገሥታት ጋ ብቻ ሳይሆን እኛም ጋ አለ፡፡
ጎረቤቶቻችን ካልበሉ ክፉ ያስቡብናል፡፡ በጎዳና ላይ የፈሰሱ ልጆች ያሳስባሉ፡፡ እኛ ልጆቻችንን በልዩ ማባበያ ወደ ትምህርት ቤት ስንሸኝ፣ ስንንከባከብ ያዩናል፡፡ ከልጆቻችን ጋር እየተያዩ ያድጋሉ፡፡ ነገ እነዚህ ትውልዶች እንደ ይስሐቅና እስማኤል ባላጋራዎች መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ በእውነት መማር የሚገባቸው ሕጻናት እንጀራ ለማግኘት ከመኪና መኪና ሲሯሯጡ ማየት ያሳዝናል፡፡ እነዚህን ድሆች አስብ እያሉ መጸለይ ብቻ አይበቃም፡፡ የድርሻችንን መወጣት ያስፈልገናል፡፡ ጸሎት ከተግባር ጋር ነውና፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ሕዝብ መግቦ አሥራ ሁለት መሶብ እንደ ተረፈ እናነባለን (ማቴ.14፡13-21)፡፡ በትንሽ ነገር ብዙ ረሀብተኞችን ሸኘ፡፡ ይህ የበረከት እጅ በታሪክ የቀረ ሳይሆን ዛሬም የሚሠራና ብዙዎችን የሚያኖር ነው፡፡ ወላጆቻችን ይህን እጅ በትንሽ ገቢያቸው ብዙ ቤተሰብ ሲያስተዳድሩበት አይተዋል፡፡ እንደ እኛ በስሌት ሳይሆን በእምነት መኖርን ያውቁታል፡፡ የእግዚአብሔር እጅ ዛሬም አለ፡፡ እኛ በስፍራችን የለንም እንጂ፡፡
አንድ አገልጋይ ደሞዙ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ የሚከፍለው የቤት ኪራይ ግን ከደሞዙ ሠላሣ ብር የሚጨምር ነው። በዚህ ኑሮው ተስማምቶት ሲኖር የልጅነት ጓደኛው የነበረችውን እህት በቶሎ እንዲያገባ አሊያ እንዲተወት የልጅቱ አባት ጠርተው ነገሩት። እንደውም ቀን ቆርጠው በዚህ ቀን ካላገባህ ለሌላ እድራታለሁ ብለው በሃብታቸው ተማምነው ተናገሩት። እርሱም አንድ አባት ጋ መጥቶ አማካራቸው። ታዲያ «አግባት» አሉት። አገልጋዩም ጮሆ «ደሞዜ እኮ ትንሽ ነው» አላቸው። እርሳቸውም «ሁለት ዓሳና አምስት እንጀራ አበርክቶ አምስት ሺህ ሰው በመገበ ጌታ ታምናለህ?» አሉት። እርሱም «አምናለሁ» አላቸው። «ካመንህ ይዘሃት ግባ» አሉት። አግጋዩም «የምግባንስ ይዣለሁ የት አኖራታለሁ ቤት የለኝም» አላቸው። እርሳቸውም «ሳጠራ ከልልና አስገባት፣ የምታምነው እግዚአብሔር ምን እንደሚሠራ ያኔ ታያለህ።» አሉት። በቅርብ እንደማውቀው ባገባ በሁለት ወሩ የማይጠብቃቸው ሰዎች ቤት ገዝተው ሰጡት። ካገባ ጀምሮም የጎደለበትን አላየሁም።
የሕጻናት እምነት ያስፈልገናል። ሕጻናት በወላጆቻቸው ያላቸው እምነት ከፍተኛ ነው። ምን እበላለሁ? ምን እጠጣለሁ? ምን እለብሳለሁ? ብለው አይጨነቁም። ባለመጨነቃቸውም ምንም አልጎደለባቸውም። እኛም እንደ ሕጻናት ያለ እምነት ሊኖረን ይገባል። ሕጻናት የተሰጣቸውን ተስፋ ያምናሉ። እኛም እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ የሰጠንን ተስፋ ማመን አለብን። እግዚአብሔር ይሆናል ያለንን ይሆናል ብለን ማመን ያስፈልገናል። ሕጻናት ወላጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ስለእግዚአብሔር ሲነገራቸውም ያምናሉ። እግዚአብሔርን ይቀርቡታል፤ ያምኑታል፤ይወዱታል። ለዚህ ነው። «አውነት እውነት እላችኋለሁ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕጻናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም» የተባለው። (ማቴ ፲፰፣ ፫)።
ታዲያ መሥራት አያስፈልግም ማለት ነው? ሥራ እርግማን ነው? ሥራ ሰው ከተፈጠረበት ዓላማ አንዱ ነው። በርግጥ ከበደል በኋላ «በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ» (ዘፍ ፫፣ ፲፱) የሚል እርግማን ቢሰጥም ቀድሞ ሥራ አልነበረም ማለት አይደለም። ከበደል በኋላ ግን የሥራ ጫናው ጨመረ፤ እርካታው ቀነሰ። ከዚያ በፊት ግን ሥራ በረከት ሆኖ ተሰጥቷል፤ (ዘፍ ፪፣ ፲፭)። ስለዚህ ሥራ ያስፈልጋል። ሥራ በረከት ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤል ልጆች ዐርባ ዓመት መና አወረደላቸው ብለን ተምረን የለም ወይ? ብንል አዎ መዝራት በማይቻልበት በረሃ ላይ መናን አውርዷል። ወደ ከነዓን ከገቡ በኋላ ግን መና ማውረድ አቁሟል። መዝራትና ማጨድ በሚቻልበት ምድር መናን ማውረድ ስንፍናን በሰማይ ሸንጎ ማጽደቅ ነው። ደግሞም የሰማይ ወፎች አይዘሩም ፣ አያጭዱም፣ ጎተራም የላቸውም ተብሎ የለም ወይ? ብንል አዎ አይዘሩም አያጭዱም ምግባቸውን ለማግኘት ግን ይሯሯጣሉ።
ሥራችን አገልግሎታችን ነው። አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ቆሞ ማገልገል ብቻ አይደለም። ባሉበት ቦታ ሥራችንን በታማኝነትና በትጋት መፈጸምም አገልግሎት ነው። ወረቀት ላይ በታማኝነት መፈረም፣ እንግዳን በር ላይ መቀበል ለእግዚአብሔር ክብር የሚውል አገልግሎት ነው? አዎ ለእግዚአብሔር ክብር የሚውል አገልግሎት ነው። በእኛ መልካምነት ሰዎች እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑና ችግራቸው ሲቃለል አገልግሎት ነው። የአገልግሎት ጥሪና ካለንና በሙሉ ጊዜያችን እግዚአብሔርን ለማገልገል የሚሰማን ድምጽ ካለ ቆርጠን መውጣት ነው። እግዚአብሔር ያኖራል። እንኳን ለቤቱ ለቤታችንም በጀት አለው።
በርግጥ የምንኖረው ስለሮጥን አይደለም። እንጀራ የምንቆርሰው አለቃችን ደስ ስላለውም አይደለም። እየጠሉን፣ እየተፈራረሙብንም እግዚአብሔር ያኖረናል። የእንጀራችን ጌታ እርሱ ነውና፤ ሰው ወዶ የሚሰጠን፣ ጠልቶ የሚያሳጣን ምንም ነገር የለም። የእኛ ዕጣችን ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው። አለቆቻችንን መውደድ፣ ማክበር፣ ምክር መጠየቅ ይገባናል። ከዚያ ባሻገር ግን እንደ ትንፋሻችን ጌታ አናያቸውም። እንኳን አለቃችን መሥሪያ ቤቱም ፈርሶ ያኖረናል። ሠርተን ከኖርነው በስጦታው የኖርነው ይበልጣል። ተግተን መሥራት፣ ተግተን መማር፣ ባለንበት ቦታ ብቁ ሆኖ መገኘት ያስፈልገናል። ከዚያ ባሻገር ግን እየበላን የሚርበን ሰዎች መሆን የለብንም የእንጀራችን ዋስትና እግዚአብሔር ነው።
የጽሞና ጊዜ
እግዚአብሔር ስለፈጠራቸው ብቻ የሚያኖራቸው ብዙ የማያምኑት ሕዝቦችን ስናይ ለምናምነውማ እንዴት ቸር ነው፤ ኑሮን በስሌት ስታስበው ከባድ ነው። በእምነት ሁሉን ለእግዚአብሔር ስትተውለት ግን ደስታህ የማያቋርጥ ይሆናል። ላልፈጠርከው ራስህ ያን ያህል አትጨነቅ። ሠራተኞችህ ያንተን ደመወዝ ተማምነው እንቅልፍ ሲተኙ፣ ዕቁብ ሲገቡ አንተ ለምን ትናወጣለህ? ስለዚህ፡-
· የምትኖረው መንግሥት የእግዚአብሔር ስለሆነ መሆኑን አስብ
· ለትልቁ ጥያቄህ እግዚአብሔር እጅ በምታህል ደመና መልስ እንደሚሰጥ አስብ።
· የእንጀራህ አድራሻ ከሰማይ እንደሆነ እመን።
· ሕይወትን ዕለት በዕለት መኖር ተለማመድ።
· በቤትህ ጥጋብ ሲሆን የጎረቤትህን ረሃብ አስብ።
· ክርስቲያን በሁሉም ነገር ብቁ ሲሆን መልካም ነውና ተግተህ ሥራ፣ ተግተህ ተማር። ያንተ አእምሮ ስለሰማይ ያውቃልና የምድሩን ማወቅ አያቅትህም።
ጸሎት
አቤቱ ጉልበቴ ሆይ አመሰግንሃለሁ። ወገን በወገን፣ ሰው በሰው ሲጠቃቀም እኔ ግን አንተን ከመጥራት በቀር የማውቀው የለኝምና ትበቃኛለህ እያልኩ አመሰግንሃለሁ። ሁሉ ሲለወጥ መለወጥ በማይደርስበት ከፍታ የምትኖር ጌታዬ ሆይ አመሰግንሃለሁ። ከእኔ ምን የሚያስወድድ ነገር አግኝተህ ነው ክረምት ከበጋ የምታባብለኝ? እኔ የጠላሁትን ይህን አዳፋ ሰውነቴን ሳይከብድህ መውደድህ ይገርመኛል። እንደ ጴጥሮስ ኃጢአተኛ ነኝና ከእኔ ራቅ አልልህም። አንተ ከራቅህኝ የሚቀርበኝ የለምና። እኔስ ኃጢአተኛ ነኝና ከእኔ አትራቅ እልሃለሁ። በረከቴ አንተ ነህ። የኖርኩት በአንተ እንጂ በሥራዬ አይደለም። አሁንም በተስፋህ አኑረኝ። ሰይጣን በኑሮ ፍርሃት ሲንጠኝ አንተ በእምነት ዓለት ላይ አቁመኝ። ሲርበኝ ሁሉም ሰው የራበው ይመስለኛል፤ ስጠግብም ሁሉም ሰው የጠገበ ይመስለኛል። እባክህ ይህ ራስ ወዳድነቴ ነውና የፍቅር ሰው አድርገኝ። የእኔና የሕዝብህ የእንጀራችን አድራሻ አንተ ነህና አመሰግንሃለሁ። በማያልቀው ቸርነትህ ለዘላለሙ አሜን።