የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ
ማክሰኞ ጥቅምት 25/ 2007 ዓ/ም
ማክሰኞ ጥቅምት 25/ 2007 ዓ/ም
መቅድም
የምትበላው መኖር ስላለብህ፣ የምትለብሰው አበደ እንዳይሉህ፣ የምታፈቅረው ስለሚያሳዝኑህ፣ የምትረዳው ሕሊና ፀጥ እንዲልልህ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ማሽላ እያረሩ መሳቅ ውስጥህን ጎድቶት ይሆናል፡፡ ምስጥ እንደ በላው እንጨት ላይህ ገዝፎ ትንሽ ሲነኩህ የምትወድቅ ሆነህ ይሆናል፡፡ ስለገባው ገቢ እንጂ ስለወጣው የማያወቁ ምቀኛ ጎረቤቶች ያበሳጩህ፣ ሁሉም ነገር አልጥም ብሎህ በግድ የምትኖር ሰው ሆነህ ይሆናል፡፡ እንዲህ የምሆነው የመረጥኩትና የሰለጠንኩበት ትምህርቴ አሊያም በቀደመ አስተሳሰቤ ያገባኋት ሚስቴ ትክክለኛ ምርጫዬ ስላልሆኑ ነው እያልክ ትታመስ ይሆናል፡፡ ዛሬ ስታገኝ የድህነት ሚስትህና ጓደኞችህ ያን ክፉ ቀን መስለውህ ይሆናል፡፡ በምትኩ ደግሞ በሽንገላ ፍቅር አብደህ ይሆናል፡፡ ሲገባ ሰፊ ሲወጣ ጠባብ በሆነው፣ ማላመጥ እንጂ መዋጥ በሌለበት ፖለቲካ ውስጥ ገብተህ በሩ ጠፍቶህ እየተቍለጨለጭክ ይሆናል፡፡
አርፍበታለሁ ብለህ የገነባኸው ቤትህ ነገር የተጣደበት ምድጃ ሆኖብህ አሊያም የምትወደው ልጅህ በሕመም የሚንገላታበት ሆኖ ወደ ቤትህ የሚወስደውን ጎዳና ስትጀምር እግርህ እያጠረብህ ተቸግረህ ይሆናል፡፡ የሞቀው ትዳርህን ስታስብ ከመሐል አንዳችን ብንቀነስ ልጆቹ ምን ይሆናሉ? የሚል ፍርሃት እየወዘወዘህ ሊሆን ይችላል፡፡ ብር ካለ በሰማይ መንገድ አለ በሚል ፈሊጥ ተይዘህ ገንዘብ የሁሉም ነገር መልስ መስሎህ ፍቅርን እየገፋህ ገንዘብ ታከማች ይሆናል፡፡ የአገሬ ሰው የሚያከብረው ሲወፍሩ ነው ብለህ ጭንቀትህን በምግብ እየተወጣኸው ይሆናል፡፡ ገንዘብ ሲመጣ ሰላሜ በየትኛው በር እንደ ወጣ አላውቅም እያልክ ይሆናል፡፡
ብዙ ሕዝብ እየወደደህ ይህ ሁሉ ተከታይ ቢከዳኝስ እያልክ ተጨንቀህ ይሆን? ወይስ አመስግና በምትራገመው ዓለም ተራው ደርሶህ ያመሰገነህ ሁሉ ሰድቦ እስኪጨርስ ወረፋው ረዝሞብህ ይሆን? ከክብርህና ከሥልጣንህ የተነሣ እንኳን ጠላቶችህን ወዳጆችህን ማመን ተስኖህ ጥላህን እየፈራህ የምትኖር ሆነሃል?
በማያስተማምን ፖለቲካ ቤት ሠርቶ ከባድ ማሽን ተክሎ መኖር እያስጨነቀህ ያላረፈ ልብ ይዘህ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም መብራት ጠፍቶ፣ ጉንዳን ገብቶ፣ እርሱ ታሞ፣ ሚስቱ ምጥ እንደ መጣባት ሰው ሆነሃል? ለነገ የሚሆን በጎተራህ ስለ ሌለ ዕረፍት አጥተህ ይሆን? ብቻህን ለምታወራው፣ ጭር ባሉ መንገዶች ለምታለቅስ፣ በሰው ልቅሶ ለራስህ ኑሮ ለምታላዝን፣ በወዳጅና በትዳር መካከል ብቸኝነት ለፈጀህ፣ ቋንቋህ ሰሚ ላጣው፣ ከዚህ ሁሉ በላይ በነገ ፍርሃት ለተያዝከው ወገን የኑሮ መድ ንህ ማን ነው?
በሰለጠነው ምድር ኢንሹራንስ ያልተገባለት ማንኛውም ተንቀሳቃሽ ንብረት መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ የጤናና የሕይወት ዋስትና ያልገቡ ሰዎችን መቅጠርም ባለ ሀብቶች ይፈራሉ፡፡ በከፍተኛ በጀት የሚንቀሳቀሱ የዋስትና ተቋማትም መኪና ለወደመበት ያንኑ የሚያህል መኪና፣ ቤት ለተቃጠለበት ተካካይ ቤት ይሰጣሉ፡፡ ምንም እንኳ የሕይወት ኢንሹራንስ ቢያስገቡም ሕይወት ላጣ ሕይወትን ሰጥተው አያውቁም፡፡ በለማ ከተማ ፍርሃት ለሚንጠው፣ የውስጥ ጥያቄ ለወጠረው፣ ጣራ ሲቆጥር ለሚያድረው እንቅልፍ ብርቁ፣ ትዳሩ አክሲዮን ለሆነበት፣ ሀብቱ እርካታ ለነሣው፣ በጦርነት ቀጠና ለሚኖረው፣ የፍቅር ረሀብ ላጠወለገው፣ ወዳጅ ሁሉ የተልባ ስፍር ለሆነበት፣ ነገ ጨለማ ሆኖ ለሚታየው ዋስትና የሚሰጥ የኢንሹራንስ ተቋም የለም፡፡ እንዲህ ያለውን ዋስትና ሰጪ ቢያገኙ የኢንሹራንስ ተቋሙ ባለቤትም ይፈልጉት ነበር፡፡ ታዲያ የኑሮ መድኅን ማን ነው?
ይህን ሁሉ ሕመማችሁን የነካካሁት እየቆነጠጡ ማስለቀስ እንደሚወዱ ሰዎች ሆኜ አይደለም፡፡ ስለ ኑሮ ሳነሣም ጆሮን ለመማረክ ብዬም አይደለም፡፡ ለእናንተ እንደምናገር ባስብ ኖሮ ብዕሬን አስቀምጥ ነበር፡፡ ከድካሜና ከሩጫዬ በኋላ እፎይ የምልበት ቃል ለራሴ እያዘጋጀሁ እንደ ሆነ ግን አውቃለሁ፡፡ ይህን የምጽፈው ቃለ መጠይቅ አድርጌ ሳይሆን ራሴን አይቼ ነው፡፡
እኔም ለእኔ ያለሁት እኔ ብቻ እየመሰለኝ የባዘንኩበትን ዘመን አውቃለሁ፡፡ ሰዎች በሕይወቴ ወሳኝ የሆኑ እየመሰለኝ ሲወዱኝ የምኖር፣ ሲጠሉኝ የምጠፋ ይመስለኝ ነበር፡፡ የትልልቅ ሰዎችን ስልክ መያዝ እንደ ቡዳና መጋኛ መድኃኒት የኪሴ መሣሪያ ይመስለኝ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ሳይሆን የሰውን ፊት እያየሁ ያገለገልኩበት ዘመን ብዙ ነው፡፡ ጊዜዬን እንጂ ሕይወቴንና ክብሬን አስቀምጬ ማገልገል ባለ መቻሌ ሩጫዬ ሁሉ የብቻ ሩጫ እንደ ነበር ተገንዝቤአለሁ፡፡ ስህተትን በስህተት ለማጥራት በመሞከር አእምሮዬን ለብዙ ዘመን እንዳቆሰልኩ እግዚአብሔር በሰጠኝ የፀጥታ ጊዜዎች አውቄአለሁ፡፡
ምድር ለተሸከመችኝ እነርሱ ከብዷቸው ብዙ ያሉኝ ወገኖች አሉ፡፡ ለመወደድም ለመጠላትም ጊዜ አለውና ሁለቱንም አይቼ ሕይወት እንዲህ ነው? ያልኩበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ መርዝ የተቀላቀለበት ሰላም ብዙ ጊዜ ተቀብዬአለሁ፡፡ «እየወጉ ይማርህ» የሚሉ የከበቡኝ ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ ስለ ከዱኝ ባልንጀሮቼ ሰዎች ሲጠይቁኝ ውስጤ እያረረ ደህና ናቸው ስል መልሰው «አቤት የእናንተ ፍቅር» ሲሉኝ ደግሞ ራሴን ጠይቄአለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ወጀብ ውስጥ ግን የተረዳኹት እግዚአብሔር ቁም ሳይል ሕይወትን የሚያቆማት እንደ ሌለ ነው፡፡ በርግጥም የኑሮ መድኅን እግዚአብሔር ነው፡፡
—– ይቀጥላል።