የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ
ቅዳሜ ጥቅምት 29 / 2007 ዓ/ም
ቅዳሜ ጥቅምት 29 / 2007 ዓ/ም
መግቢያ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚስቡ ቃሎች ብቻ ሳይሆን የሚስብ ፍቅርም ነበረው፡፡ በረሃው ዓለም ላቃጠለው ቃሎቹ ጥም ቆራጭ ያው ፣ ፍቅሩም ማረፊያ ጥላ ነበር፡፡ የተናገራቸው ቃሎች ፊደል ሳይሆኑ ሕይወት፣ ፍልስፍና ሳይሆኑ መንፈስ ነበሩ (ዮሐ.6፡63)፡፡ ከተናገራቸው ሕይወት አድን ቃሎች በማቴዎስ 11፡28 ያለው ቃል ልብን የሚገዛ ቃል ነው፡– «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡»
ሁላችንም ወደ እግዚአብሔር ለመምጣት እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ይህን ሱስ፣ ይህን ኃጢአት ስተው፣ ንጹሕ ስሆን ነው የምመጣው እንላለን፡፡ ነገር ግን ራሳችንን አጽድተን መምጣት ብንችል ኖሮ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ባላስፈለገው ነበር፡፡ እርሱ የሞተው ሰው ራሱን ከኃጢአት ማዳን ስላልቻለ ነው፡፡ በምድር ላይ የሚገኙት ሃይማኖቶች ሰው ወደ እግዚአብሔር መምጣት ያለበት ታጥቦና ታጥኖ፣ ፀድቶና ተለውጦ ነው ይላሉ፡፡ ክርስትናው ግን የምንፀዳውና የምንለወጠው ወደ ክርስቶስ ስንመጣ እንደሆነ ይነግረል፡፡ ሰው ራሱን ለማዳን አምላክነት ያስፈልገዋል፡፡
ንስሐን በሚመለከት በሃይማኖቶች ሁሉ ያልተቋጨ ክርክር አለ፡፡ አንደኛው ወገን ሰው ወደ ክርስቶስ መምጣት ያለበት አስቀድሞ ንስሐ ገብቶ ነው ሲል ሌላው ወገን ደግሞ ንስሐ የሚገባው ወደ ክርስቶስ ሲመጣ ነው ይላል፡፡ ኃጢአተኛው ንስሐ ለመግባት ኃጢአቱን በንጹሕ መስታወት ማየት፣ ተጸጽቶ ለመወሰን እርሱን አፍቅሮ የሞተለትን ጌታ መመልከት ያስፈልገዋል፡፡ በክርስቶስ የቅድስና ብርሃን ፊት ካልቆመ ኃጢአቱ ሊታየው፣ በቀራንዮ ፍቅር ፊት ካልቆመ የበደሉ ክብደት ሊታየው በፍጹም አይችልም፡፡ ስለዚህ ኃጢአተኛው አስቀድሞ ወደ ክርስቶስ ይመጣል፡፡ ከዚያም ልቡ ለንስሐ ይዘጋጃል፡፡ ለኃጢአተኞች የበደልን ፍርድ ከመንገራችን በፊት የበደላቸው ስርየት የሆነውን ታላቁን ፍቅር ልንነግራቸው ይገባል፡፡ ለዚህ ነው «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ያለው፡፡
ብዙ ክርስቲያኖች የበደል ሸክም ተጭኗቸው ቀድሞ ወደ ክርስትና ሲመጡ የነበራቸው ደስታ ርቋቸዋል፡፡ ሌሎችም እግዚአብሔርን እየበደልኩት እንዴት በቤቱ እኖራለሁ? በማለት በአጉል ትሕትና ተይዘው ወደ ዓለም ኮብልለዋል፡፡ እንደ እነርሱ አሳብ ኃጢአትን ለማድረግ በሚቻልበት ቦታ ሆነው ኃጢአታቸውን እየፈጸሙት ነው፡፡ ኃጢአትን ሳይጨርሱት ንስሐ መግባት ግድ ነው፡፡ የተቀሩትም በድፍረት ኃጢአት ተይዘው ብከፋ ብከፋ ከእነ እገሌ አልከፋም እያሉ በመሻል መስፈርት ተረጋግተው ተቀምጠዋል፡፡ የሚበዙትም «የሃይማኖት አባቶች ይህን እያደረጉ በእኛማ ምን ይፈረዳል?» እያሉ ከንስሐ ርቀው ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች አንድ የሃይማኖት አባት ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያውቁ ከሆነ እውቀታቸው ከሃይማኖት አባቶች በላይ በመሆኑ ይበልጥ ይፈረድባቸዋል፡፡
ብቻ ደካማነታችን ከተሰማን ጥሪው ይመለከተናልና ወደ ጌታችን ቀርበን «ጌታ ሆይ፣ በጎ የመሆን ፍላጎት እንጂ አቅም የለኝም፡፡ ሙከራዎቼ ሁሉ ሊለውጡኝ አልቻሉም፡፡ አንተ ብቻ ትለውጠኛለህና እንደ ቃልህ አሳርፈኝ» ብለን መጸለይ አለብን፡፡
ከበደል ባሻገር የኑሮ ሸክም የተጫናቸው ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ እንደ አገልጋይነታችንም ያሳዝኑናል፡፡ የሚያሳዝኑን በችግር ውስጥ ስላሉ ብቻ ሳይሆን ሊረዳቸው የተዘረጋውን የእግዚአብሔርን እጅ ማየት ባለመቻላቸውም ነው፡፡ እንደ ሳማ በሚለበልብ ትዳር ውስጥ የሚኖሩ፣ ምግባረ ብልሹ ልጆችን የተሸከሙ፣ ጣዕም በሌለው ባለጠግነት የሚዋኙ፣ ሰላም በራቀው ቤተሰብ የሚኖሩ፣ ጉድለት በሚፈራረቅበት ኑሮ የሚንገላቱ፣ ሥር በሰደደ በሽታ የተያዙ፣ የስህተታቸውን ዋጋ ከፍለው መጨረስ ያቃታቸው፣ ዝም ብለው በአሳብና በጭንቀት ማዕበል የሚንገላቱ፣ በፍቅር እጦት ምክንያት የብቸኝነት ብርድ የሚያንዘፈዝፋቸው … ሰዎች በዙሪያችን አሉ፡፡ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ በተነሣው በመጀመሪያው ቀን እንኳ በስልኮቼ አሰቃቂ የሆኑ ልቅሶዎችን ሰምቻለሁ፡፡ እነዚህ አልቃሾች ይህን ጽሑፍ እንድገፋበት ረድተውኛል፡፡
በዚህ ሁሉ የሰቀቀን ድምፅ ውስጥ «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ» የሚለው ድምጽ የኑሮ መድኅን ነው፡፡
የተሸከምነውን ሸክም እንደ ተሸከምን ለመጓዝ ካልቻልን ታክሲ እንጠብቃለን፡፡ ታክሲው ሲመጣ ሸክማችንን ለታክሲው አሸክመን በታክሲው ምቾት ተዝናንተን እንጓዛለን፡፡ የመንገዱንም ጉዳይ ለሾፌሩ ስለጣልነው ዓይናችንን ጨፍነን እናዜማለን፡፡ እንዲሁም በእምነት ወደ ክርስቶስ ስንመጣ የሚከብደንን ሸክም ሁሉ ለእርሱ ትተን በዕረፍቱ አርፈን መጓዝ ይገባናል፡፡ ሸክም ያለ ቦታው አያርፍም፡፡ የሚያንገደግድ ሸክም ተሸክሞ ላቡ እንደ ውሀ እየጎረፈ የሚጓዘው ሰው ለምን አይጥለውም? ብንል ሸክም ያለ ቦታው ስለማያርፍ ነው፡፡ እንዲሁም የሕይወትና የኑሮ ሸክማችንን ከክርስቶስ በቀር የሚያሳርፍልን ማንም የለም፡፡
በዛሬው ዘመን ሰዎች ሁሉ ሲገናኙ የሚለዋወጡት የእግዚአብሔርን ሰላም ሳይሆን ፍርሃታቸውን ነው፡፡ የአንዱ ፍርሃት ከሌላው ይለያል፡፡ የተቃጠለ አየር ስለሚለዋወጡ ጥቂት እንደ ቆዩ ነፍሳቸው በፍርሃት ትታፈናለች፡፡ ይልቁንም በአንደበታችን የሽንፈት ቃሎች ስንናገር የእግዚአብሔር ኃይል እየራቀን ይመጣል፡፡ እንደ ዋዛ የምንናገራቸው «እግዚአብሔር ቢኖርማ እንዲህ ይሆን ነበር? የእኔ ዕድል ጠማማ ነው፡፡ አልፎ አወራው ይሆን? . . .» የሚሉት ንግግሮች የተለመዱ ስለሆኑ ምንም አይመስሉንም እንጂ የጭንቀትን ዘመን የሚያራዝሙብን ናቸው፡፡ ሰይጣን መረጃ የሚያገኘው ከአንደበታችን በመሆኑ የሽንፈት ቃሎች ስንናገር አሁንስ ደክሞታል ብሎ ጦር ያስከትትብናል፡፡ ይህን ስንል ልባችን ወድቆ በአንደበታችን እናስመስል ማለት አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር አቅም በላይ የሆነ ፈተና አልገጠመንምና ልባችንም አንደበታችንም ሊፀና ይገባዋል፡፡ ድካማችንንም በጸሎት ለእግዚአብሔር መንገር ያስፈልገናል፡፡
በሰለጠነው ዘመንና ዓለም ሁሉም ነገር ዋስትና ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሰዉ፣ መኪናው፣ ቤቱ… ዋስትና አለው፡፡ የዋስትና ተቋማትም በታማኝነት መኪና ሲጠፋ መኪና ይተካሉ፡፡ ዋስትናችንን አሳድገናል በማለትም ሰዎች የሕይወት ዋስትና እንዲገቡ ያባብላሉ፡፡ ነገር ግን ለጠፋ ሕይወት ገንዘብ እንጂ ራሱን ሕይወት ሲተኩ ታይተው አያውቁም፡፡ ስለዚህ ዋስትናቸው ከቁሳቁስ አያልፍም፡፡ ላዘመሙ ትዳሮች፣ መረን ለሆኑ ልጆች፣ ለታወከች ነፍስ መፍትሔ የላቸውም፡፡
የምንኖርበት ዓለም ጥፋትና ክስረት የሚፈራረቅበት በመሆኑና ዘወትርም በልዩ ልዩ አደጋዎች ውስጥ ስለምናልፍ ዋስትና እንፈልጋለን፡፡ እኛ የምንፈልገውን ዋስትና የታወቁ የኢንሹራንስ ድርጅቶች ሊያሟሉት አይችሉም፡፡ እኛ ራሳችንን አልተቀበልነውም፣ ሰላማችን እንደ ባሕር የሚነዋወጽ ነው፣ በትዳር ምርጫችን ደስተኞች አይደለንም …፡፡ ታዲያ የኑሮ መድ ናችን ማን ነው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ የዚህ መጽሐፍ ዓላማ በማዕበልና በፍርሃት ለሚንገላቱ ወገኖቻችን የነፍሳቸውን መልሕቅ ለመወርወር ነው፡፡ መጽሐፉ ያሳያል እንጂ አንባቢውን ተክቶ አይደርስም፡፡ እውነቱን ይናገራል እንጂ ለአንባቢው አያምንለትም፡፡
የመጽሐፉ ፍሰት ከብሉይ ኪዳን እስከ አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ለእኛ ሕይወት ያለውን ዕቅድ ያሳያል፡፡ የዓለምን ከንቱነትና የእግዚአብሔርን ቋሚነት ለማሳየት ይጨነቃል፡፡ እያንዳንዱን ምዕራፍ አንባቢው ሲጨርስ የጽሞና ጊዜ በመጠየቅ ከአንባቢው ጋር ይደራደራል፡፡ የአንባቢው እሺታ በራሱ ኃይል የለውምና ወደ ጸሎት ያልፋል፡፡ መጽሐፉ አንባቢው ከአምላኩ ጋር እየተገናኘ በጸሎት መንፈስ ሆኖ እንዲያነበው የተዘጋጀ ነው፡፡ ብዙ ሀዘንተኞች የጽሑፉን ጅምር አይተው እንድፈጽመው ከዓመት በላይ
ወትውተውኛል፡፡ እናንተም እንደምትበረቱበት ጸሎቴም እምነቴም ነው።
—– ይቀጥላል
ወትውተውኛል፡፡ እናንተም እንደምትበረቱበት ጸሎቴም እምነቴም ነው።
—– ይቀጥላል