ምዕራፍ አንድ – ኑሮና ሕይወት
የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ
ማክሰኞ ኅዳር ፪/፳፻፯ ዓ/ም
አንድ ወጣት ለትምህርት ከአፍሪካ ምድር ወደ ጣልያን አገር ይሄዳል፡፡ አንድ ቀንም ትምህርቱን አጥንቶ ፀሐይዋ ዘቅዘቅ ስትል አየር ለመቀበል በጎዳና ላይ ሲጓዝ አንድ በዕድሜ የገፉ አረጋዊ አገኘ፡፡ አረጋዊውም መልኩን በማየት ከሌላ አገር እንደ መጣ ተረድተው፡– “ልጄ ወደዚህ አገር ለምን መጣህ?|” በማለት ይጠይቁታል፡፡ ወጣቱም «ለትምህርት» አላቸው፡፡ እርሳቸውም በሦስት እግር እየተጓዙ «ከተማርክ በኋላ ምን ትሆናለህ?» በማለት በዝግታ ይጠይቁታል፡፡ ወጣቱም ሽምግልናቸውን በማየት ቢደሰቱ ብሎ «ጳጳስ እሆናለሁ» አላቸው፡፡ እርሳቸውም ሳይደነቁ «ጳጳስ ከሆንክስ በኋላ ምን ትሆናለህ?» አሉት፡፡ እርሱም «ካርዲናል እሆናለሁ» አላቸው፡፡ እርሳቸውም «ካርዲናል ከሆንክስ በኋላ?» አሉት፡፡ ወጣቱም በደስታ ዓይኑን ጨፍኖ «ኦ አይገኝም እንጂ
ፖፕ እሆናለሁ» አላቸው፡፡ አረጋዊውም «ፖፕ ከሆንክስ በኋላ?» ቢሉት «ከዚያ በኋላማ በመልካም አስተዳድሬ እሞ ለሁ» አላቸው፡፡ አረጋዊውም ታላቁን ምክራቸውን ሲለግሱት «አየህ ልጄ፡– ጳጳስ፣ ካርዲናል፣ ፖፕ ልትሆንም ላትሆንም ትችላለህ፡፡ መሞትህ ግን አይቀርም፡፡ መጀመሪያ ለማይቀረው አስብ፣ ከዚያ ቀጥሎ ግን ሊሆንም ላይሆንም ስለሚችለው ነገር አስብ» አሉት ይባላል፡፡
ፖፕ እሆናለሁ» አላቸው፡፡ አረጋዊውም «ፖፕ ከሆንክስ በኋላ?» ቢሉት «ከዚያ በኋላማ በመልካም አስተዳድሬ እሞ ለሁ» አላቸው፡፡ አረጋዊውም ታላቁን ምክራቸውን ሲለግሱት «አየህ ልጄ፡– ጳጳስ፣ ካርዲናል፣ ፖፕ ልትሆንም ላትሆንም ትችላለህ፡፡ መሞትህ ግን አይቀርም፡፡ መጀመሪያ ለማይቀረው አስብ፣ ከዚያ ቀጥሎ ግን ሊሆንም ላይሆንም ስለሚችለው ነገር አስብ» አሉት ይባላል፡፡
የሰው ልጆች ስለ ትምህርት፣ ስለ ሥራ፣ ስለ ትዳር፣ ስለ ልጅና ስለ ክብር ብዙ ያስባሉ፡፡ እነዚህን ነገሮች በቀጥታም ሆነ በአቋራጭ ቢያገኙ ዋናው ማግኘታቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ ሲባሉም ከእነዚህ ነገሮች በኋላ እንደሚመለሱ ይናገራሉ፡፡ የጉብዝናቸውን ዘመን ለዓለም፣ የድካማቸውን ዘመን ለእግዚአብሔር፤ የሚፈለጉበትን ዘመን ለሥጋ፣ መፈለጋቸው የሚቀንስበትን ዘመን ለእግዚአብሔር ቤት ለማድረግ የወሰኑ ይመስላሉ፡፡ ተምረን ሥራ እንይዛለን፣ ሥራ ከያዝን በኋላ ትዳር እንመሠርታለን፣ ከዚያም ዓይናችንን በዓይናችን በልጆቻችን በማየት የከበሬታ ሥፍራን በማኅበረሰቡ ዘንድ በመጨበጥ ደስ ይለናል ይላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ግን ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ በሰዎች ላይ ግን ለማንም የማይቀር አንድ ዕጣ አለ፡፡ እርሱም ሞት ነው፡፡ ያስቀመጠውን የማይረሳ ጌታ በጫካ ቢሆን በከተማ በፈለገው ሰዓት ፍጡሩን አያጣውም፡፡ የቤተ መንግሥት ዘቦች፣ ከባቢሎን ግንብ የሚበልጡ አጥሮች የሞትን መልእክተኛ መመለስ አይችሉም፡፡ ሰው ከአፈር መፈጠሩ ምን ያስተምረናል? ብንል ትሑት እንዲሆንና ሞቱን ማሰብ እንዲገባው ያስተምረናል፡፡ ስለዚህ ስለማይቀረው አስቀድሞ ማሰብ ይገባል፡፡
የሰው ልጅ የማይለወጡ ሁለት ቋሚ ባሕርያት አሉት፡፡ እነርሱም፡– ሥጋና መንፈስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ሥጋው ግዙፍ ሲሆን መንፈሱ ግን ረቂቅ ነው፡፡ ለሥጋው እንጀራ ሲያስፈልገው ለመንፈሱ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ያስፈልገዋል፡፡ ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ ሰይጣን «… እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል» በማለት ሲፈትነው «ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል» በማለት መልሶለታል (ማቴ.4፡4፤ዘዳ.8፣3)፡፡ ሰው ሁለት ባሕርያት እንዳሉት ይገልጻል፡፡ እነርሱም፡– ሥጋና መንፈስ ይባላሉ፡፡ እነዚህ በአንድ አካል የተዋሐዱ ሁለት ባሕርያት ፍላጎታቸው ፍጹም የተለያየ ነው፡፡ ሥጋው እንጀራ ሲያስፈልገው፣ መንፈሱ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ እንጀራ ብቻውን የሰውን ፍላጎት
አያረካም ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት ከመብል፣ ከመጠጥ፣ ከልብስና ከመጠለያ ያለፈ ነውና፡፡
አያረካም ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት ከመብል፣ ከመጠጥ፣ ከልብስና ከመጠለያ ያለፈ ነውና፡፡
የሰው ልጅ ግን ለሆዱ እንጀራን ለማግኘት የሚደክመውን ያህል ለመንፈሱ ምግብ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ለማግኘት አለመድከሙ ያሳዝናል፡፡ ካልበላን በሥጋ መኖር እንደማንችል፣ ያለ እግዚአብሔር ቃልም የመንፈሳችን ህልውና ተጠብቆ መቆየት አይችልም፡፡ የጥንት ሮማውያን ምርኮኞቻቸውን ሬሳ አሸክመው ይነዱአቸው ነበር፡፡ ይህ ሸክም ከባድ ሲሆን ምርኮኞቹም መጥፋት አይችሉም ነበር፡፡ ቃሉን የማይመገብ መንፈስም የሬሳ ሸክም ነው፡፡ የበረታ ሥጋ የሞተ መንፈስን መሸከም አይችልም፡፡ ብርቱ መንፈስ ግን የደከመውን ሥጋ ይሸከማል፡፡
የሰው ልጅ የሚታይና የማይታይ ተፈጥሮ አለው፡፡ በማይታየው ባሕርይው እግዚአብሔርን ይመስላል፡፡ በሚታየው ተፈጥሮው ደግሞ እንስሳትን ይመስላል፡፡ ስለዚህ ሰው ምድራዊም ሰማያዊም ነው፡፡ በሥጋው እንስሳትን መስሎ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይወልዳል፣ ይዋለዳል፡፡ በነፍሱ ደግሞ መላእክትን መስሎ ይዘምራል፣ ይቀድሳል፡፡ በሥጋው ጊዜያዊ ሲሆን በነፍሱ ግን ዘላለማዊ ነው፡፡
በአንድ ሣንቲም ላይ እንዳለ ሁለት ገጽታ የሰው ሁለንተናም ኑሮና ሕይወት በመባል ይጠራል፡፡ ኑሮ ያለ ሕይወት ሙት ሲሆን ሕይወት ያለ ኑሮም የማይገለጥ ነው፡፡ ሰዎች ሰላም ሲሰጡን «ኑሮ እንዴት ነው? ሕይወትስ?» በማለት ይጠይቁናል፡፡ በርግጥም የሚጠየቅ ጥያቄ ነው፡፡ ነገር ግን ጥያቄውም ሆነ መልሱ የልማድ ንግግር መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ኑሮ የዚህ ዓለም ቆይታችን ነው፡፡ ሕይወት ግን ኢየሱስ ክርስቶስን ካመንበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዘላለም የሚቀጥል ነገር ነው፡፡ ሰዎች በትልልቅ ተቋማት ገብተው የሚማሩት የእንጀራ እውቀትን እንጂ የሕይወት እውቀትን አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን ኑሮ ብዙ ሊቃውንቶች ሕይወታቸው የወደቀ ባልሆነ ነበር፡፡ የሕይወት እውቀት የሚገኘው ከሕይወት ባለቤት ከእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
ኑሮ መራራም ጣፋጭም ነው፡፡ ቍሳዊ በመሆኑ የውስጥን ጥማት ማርካት አይችልም፡፡ ኑሮ ማዘን መደሰት፣ ማግኘት ማጣት፣ መነሣት መውደቅ፣ መወደድ መጠላት፣ መከበር መዋረድ ያለበት በሁለት ተቃራኒና አንጻራዊ ሁኔታዎች የተዋቀረ ነው፡፡ ኑሮ በደሳሳውም ጎጆ ሆነ በቤተ መንግሥት ትንሽ ነው፡፡ ሰው ትንሽነቱን የሚያገኝበትና የሚደብቅበት ቦታ ቢኖር ኑሮ ነው፡፡ መሸነፉ፣ ማዘኑ፣ መድከሙ፣ ተስፋ መቍረጡ፣ በስሜት መውደቁ የተሸፈነው በኑሮ ውስጥ ነው፡፡ ኑሮ ለባለቤቱ እንደሚመስለው ምሥጢር ነው፡፡ ኑሮ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ጎዶሎ ነው፡፡ ያጎደለው ግን አምላካዊ ጥበብ በመሆኑ የሰው ጥረት ሊሞላው አይችልም፡፡ ጎዶሎው የጸሎት ርዕስ ነው፡፡ «ጎዶሎ ከሌለ እግዚአብሔር ይረሳል» እንደሚባለው፡፡ ኑሮ በክርስቶስ ሕይወትን ካላገኘ የሬሳ ሸክም፣ ጨው የሌለው አልጫ፣ የማይደፈር ጨለማ ነው፡፡
ከዘላለም አገር ሆነን ስናየው ግን ኑሮ ቀላልና አስደሳች ነው፡፡ ትልልቅ ነገሮች ትልቅ ሆነው የሚታዩት ከምድር ስናያቸው ነው፡፡ ከሰማይ ስናየው ግን ትልቁ ተራራ እንኳ ትንሽ ነው፡፡ በአጠቃላይ ኑሮ ራሱን የሚተረጉም መዝገበ ቃላት የለውም፡፡ የኑሮ ትርጉም ያለው በሕይወት ውስጥ ነው፡፡ ያለ ሕይወት ኑሮንም መኖር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ወደ ቀጣዮቹ ምዕራፎች ከመዝለቃችን በፊት በክርስቶስ ያለውን ሕይወት ወራሽ መሆናችንን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ምክንያቱም የጽሑፉ ዓላማ ግንዛቤን ማስፋት ሳይሆን በእምነት ማቆም ነውና፡፡
ከመጀመሪያዎቹ ሰዎች አንሥተን ብንመለከት የሰው ዕድሜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የኑሮ ትግል ግን በርትቷል፡፡ ዕድሜው ትንሽ ትግሉ ብዙ ሆኗል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የምናሳልፈው ዕድሜ በሰማይ ከምናሳልፈው ጋር ሲነጻጸር የዓይን ጥቅሻ ያህል ነው፡፡ ከዘላለም አንጻር ስናየው የዚህ ዓለም ቆይታችን አንዲት ሰዓት እንኳን አይሞላም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ያሳለፍነው የዕድሜ ልክ መከራችን በመንግሥተ ሰማያት የአንዲት ሰዓት ደስታ ይካሳል (ሮሜ.8፡18)፡፡ የመጽሐፍ መግቢያ የመጽሐፉ ቅምሻ እንጂ ሙሉ መጽሐፉ እንዳልሆነ በትልቁ የሕይወት መጽሐፍም የዚህ ዓለም ኑሮ እንደ መግቢያ ነው፡፡
ቢሆንም ትግል ባይኖር የድል ደስታ፣ በሽታ ባይኖር የጤና ምስጋና አይኖርም ነበር፡፡ ጣፋጭን ያጎላው መራራ ነው፡፡ አንድን ነገር ሳንፈልገው ከምናገኘው ዋጋ ከፍለን ስናገኘው ያስደስታል፡፡ አክብረንም እንይዘዋለን፡፡ አዎ ትግሎች ሳይቀር ለደስታችን ተዋቅረዋል፡፡ የዚህ ዓለም ቆይታ ጊዜያዊ ቢሆንም ዘላለማዊ ውሳኔ የሚደረግበት በመሆኑ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ይህ ዓለም ቆይታው ትንሽ ቢሆንም በጎ ለመሥራትም ሆነ በክፉ ሥራችን ለመፀፀት ዕድል ያለበት ዓለም ነው፡፡ የወዲያኛው ዓለም ግን የምርጫችንን ውጤት የምንቀበልበት ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል» (ማቴ.6፣33) ብሏል፡፡ ቀዳሚዉ መንግሥቱና ጽድቁ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ኑሮ ግን ተጨማሪ ነው፡፡ የሚቀድመውንና የሚከተለውን ማወቅ ትልቅ እውቀት ነው፡፡ የብዙዎች ሰዎች ችግር ቀዳሚውንና ተከታዩን አዘባርቆ መኖር ነው፡፡ ከምሳ ቀጥሎ መክሰስ ወይም የእራት መዳረሻ አለ፡፡ የዚህ ዓለም ኑሮም ዋናው ሳይሆን የሰማይ መዳረሻ ነው፡፡ በትልልቅ ሆቴሎች ከዋናው ምግብ በፊት የባለጠጎችን አምሮት የሚከፍቱ ቀላል ምግቦች ይከታተላሉ፡፡ ዋናው ገና መሆኑን የማያውቅ እስከ መጨረሻው ይመገባቸውና ዋናው ምግብ ሲመጣ ይጠግባል፡፡ ይህ ዓለም ዋና የመሰለውም ሰው በቀላል ነገሮች ጠግቦ ዋናውን ሕይወት ይገፋል፡፡ በትልልቅ በዓላት የዋዜማ ድግስ አለ፡፡ በዋዜማው ጨርሶ የጠገበ ሰው በዋናው በዓል ላይ መቆም ያቅተዋል፡፡ ይህ ዓለምም ለሰማዩ ዋዜማ ነው፡፡ ነጋዴ ዋና ይዞ ነው የሚነግደው፡፡ ትርፍ ዋዣቂ ነው፡፡ ዋናውን የማያውቅና የማይጠብቅ ነጋዴ መሆን አይችልም፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ትርፍና ኪሣራውን አጥርቶ አያውቅም፡፡ ሕይወትም ብዙ የምናተርፍባት ብዙ የምንከስርባት ንግድ ናት፡፡ በሕይወት ውስጥ ዋናው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሌላው ግን ትርፍ ነው፡፡ ስለዚህ ዋናውን ላለማስነካት መጠንቀቅ አለብን፡፡
ይህን ዓለም እንደ ዘላለም ቤቱ የሚኖር ሰው ምስኪን ነው፡፡ እንደ አውሬ እያጉረመረመ የሚበላ፣ እየነጠቀ የሚያድር ነው፡፡ ማጣቱና መውደቁ የጠለቀ ሀዘን ውስጥ የሚከተው ነው፡፡ ይህ ዓለም ጊዜያዊ ቤት ነው፡፡ መጽሐፉ እንደሚለው የድንኳን ኑሮ ነው (2ቆሮ.5፣1)፡፡ ድንኳን በቶሎ ይፈርሳል፣ ዓለምም ለማለፍ ይቸኩላል፡፡ ድንኳን ምንም በጥሩ ካስማ ቢተከል መነዋወጹ አይቀርም፡፡ ዓለምም የተረጋጋ ሰላም የለውም፡፡
ታዲያ በዓለም ላይ መኖር እንዴት ይቻላል? እንል ይሆናል፡፡ መርከብ በውሀ ውስጥ ሳይሆን በውሀ ላይ መሄድ ይችላል፡፡ ክፍተት ከሰጠ ግን ውሀው እየሞላው መስጠም ይጀምራል፡፡ ክርስቲያንም በዓለም ላይ መኖር፣ መማር፣ መሥራት ይችላል፡፡ ለዓለም ከንቱ አሳብ ግን ትንሽ ክፍተት ከሰጠ መስጠም ይጀምራል፡፡ መርከብ በውሀ ላይ እስከሄደ ድረስ ወደ ወደቡ ሲደርስ ውሀው ከበላዩ ከሆነ ግን እዚያው ይሰጥማል፡፡ ክርስቲያንም በዓለም ላይ መኖር ይችላል፡፡ ወደ ወደቡ ወደ ሰማይ ለመድረስ ግን ቀዳዳዎችን መድፈን አለበት፡፡
በዛሬው ዘመን የሰው ልጆች የኑሮ ፍርሃት ጨምሯል፡፡ የዚህ የመጀመሪያው ምክንያት ያለ ሕይወት ኑሮን መኖር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚቀድመው ስላልቀደመ የሚከተለው አልገጥም እያላቸው ነው፡፡ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የሰው ልጆች በአንድ ዓይነት ትምህርት፣ በአንድ ዓይነት ሥራ አይኖርም ወደሚል እምነት ውስጥ ገብተው ይባክናሉ፡፡ ሁለት ዓይነት ሥራ፣ ሁለት ዓይነት ትምህርት ይማራሉ፡፡ የእውቀት ስስት ይዟቸው በዚህ ባጣ በዚህ እበላለሁ ብለው ይማራሉ፡፡ መማርም መሥራትም ተገቢ ቢሆንም ዋስትና ግን አይሆንም፡፡ እኛ ሁሉን ይዘነውስ ሌላው ምን ሆኖ ይኑር?
ሥጋ መፍራት ልማዱ ነው፡፡ የታረደውን በሬ ስናይ ሥጋ ሞቶ እንኳን እንደሚንቀጠቀጥ እንረዳለን፡፡ ባለ ቅኔው፡–
«ጥንቱንም ሲፈጥረው ሥጋ ብለውት፣
ሲጨነቅ ይኖራል የለውም ዕረፍት፤» ብሏል፡፡
ሥጋ የሚለው ቃል ሥጋት ከሚለው ቃል የወጣ ሲሆን በትእዛዝ አንቀጽ ሥጋ ወይም ፍራ ተብሏል፡፡ ባለ ቅኔውም ሥጋ መፍራት ልማዱ መሆኑን ሲገልጥ ነው፡፡ ሰው ልቡን በእምነት ካላሳረፈ በቀር ቢመንንም ቢነግድም ዕረፍት አይኖረውም፡፡
የጽሞና ጊዜ
የሚታይና የማይታይ ተፈጥሮ ስለያዝህ ተፈጥሮህ ራሱ የዚህ ዓለም ሰው ብቻ እንዳልሆንህ ይገልጻል፡፡ ሰማያዊ ነህ – ፈላስፋው «ዛሬ ማታ እንደሚሞት ሆነህ ተዘጋጅ፣ ለዘላለም እንደሚኖር ሆነህ ግን ሥራህን ሥራ» ያለውን አስተውል፡፡ ከሁሉ በላይ ለእውነት ተፈጥረህ ለውሸት አትኑር፡፡ የሚቀድመውን አስቀድም በመጀመሪያ፡–
– የማይቀረውን ሞት፣
– መንግሥቱንና ጽድቁን፣
– ዋናውን፣
– ሕይወትን አስብ፡፡
ጸሎት
ለአነሣሥህ ጅማሬ፣ ለዓመታትህ ፍጻሜ፣ ለአሠራርህ ገደብ፣ ለአቅምህ ልክ የለህምና የወዳጅ ጦር ያቆሰለኝ ልጅህ አመሰግንሃለሁ፡፡ ዓለሙን ሳየው አንተ ሳታሳልፈው ቶሎ ለማለፍ እየቸኰለ ነውና በማዕበል፣ በእሳት ውስጥ እባክህ መንገድ ስጠኝ፡፡ ጽንሱ ከእናቲቱ ጋር እንደተቆራኘ እኔም ያላንተ አልኖርምና ከፊትህ አትጣለኝ፡፡ የማይቀረውን ማሰብ ትቼአለሁ፣ ሰው አያየኝም ብዬ በምታየኝ በአንተ ፊት ብዙ በድያለሁ፤ ብዙ ሰው አቍስያለሁና አቤቱ ማረኝ፡፡ ሥጋዬ የሬሣ ሸክም እንዳይሆንብኝ አንተው ገላግለኝ፡፡ ከመልአካዊ ተፈጥሮዬ እንስሳዊ ተፈጥሮዬ አይሎብኝ ተዋርጄአለሁና ዕድሜም እውቀትም ያለወጠኝን ልጅህን በሚለውጥ ፍቅርህ ለውጠኝ፡፡ ከሚያልፈው ትግል ውስጥ የማያልፈውን ትምህርት እንዳልጥል እርዳኝ፡፡ ጠዋትና ማታ በማላሳርፈው ስምህ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሜን፡፡
———————-ይቀጥላል———————–