“በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ በነቢያት፡- ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።” (ማቴ. 2 ፡ 22-23 ።)
ሄሮድስ የሚለው ስም ኋላ ላይ ስመ መንግሥት ሆኗል ። በአገራችን ዐፄ እንደሚባለው ሄሮድስም ስመ መንግሥት በመሆን አገልግሏል ። ሄሮድስ በሚለው ስም ብዙዎች ተጠርተዋል ። ዋነኛው ግን ታላቁ ሄሮድስ ተብሎ የሚጠራው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ37 ዓመት ጀምሮ እስከ 4 ዓ.ም. ድረስ ሥልጣን ላይ የነበረው ፖለቲከኛ ሰው ነው ። ይህ ሰው ሮማውያን የአባቱን የአንቲጳስን ውለታ አስበው ከፍ ያደረጉት ሲሆን በይሁዳ የነበረውን ሥልጣን በተቃዋሚዎች አጥቶ ወደ ሮም በሄደ ጊዜ ንጉሥ አድርገው ለአጥቢያው ሾሙት ። ሄሮድስም አስመሳይ ነበርና ከሮማ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እስከ ቤተ ጣዖት ድረስ መሥዋዕትን በመሠዋት ታማኝ መሆኑን ገለጠ ። በሮማውያን ወታደራዊ ኃይል ታግዞ ዳግም የእስራኤልን ምድር ተቆጣጠረ ። ታላቁ ሄሮድስ በዓለም ላይ በተለያዩ ሥራዎቹ ይታወቃል ። ለሮም ንጉሥ መቀመጫነትና ለክብሩ በመሠረታት ቂሣርያ ይታወቃል ። ደግሞም ሁለተኛውን መቅደስ በማደስም የታወቀ ነው ። ይህ የመቅደስ እድሳትና መስፋፋት በ19 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የጀመረ ሲሆን የተጠናቀቀው በ64 ዓ.ም ነው ። በሚያሳዝን መልኩ 6 ዓመት አገልግሎት ሰጥቶ በ70 ዓ.ም. በሮማውያን ፈረሰ ። ሄሮድስ ፖለቲከኛ ስለነበር የሥልጣኑ ምንጭና ደጋፊ የነበሩትን ሮማውያንን እንዲሁም የሚገዛቸውን አይሁድን በእኩልነት ደስ ለማሰኘት ይሞክር ነበር ። ለሥልጣኑ በጣም የሚሳሳ በመሆኑ ሚስቱንና ሦስት ወንዶች ልጆቹን ፈጅቷል ።
ሄሮድስ ጌታችንን ለመግደል በመነሣቱ ይታወቃል ። ብዙ የቤተ ልሔም ሕፃናትንም አስጨፍጭፏል ። ጌታ ወደ ግብጽ ከተሰደደ በኋላ ሄሮድስ የቆየው ለ3 ዓመታት ያህል ነው ። ሲሞት መንግሥቱ ለሦስት ልጆቹ ተከፋፈለ ። ይሁዳን ወይም ዋናውን ደቡባዊ ግዛት አርኬላዎስ ሲገዛ ፣ በሰሜን ያሉትን ሁለት ግዛቶች ሄሮድስ ፊልጶስና ሄሮድስ አንቲጳስ ገዝተዋል ። እነዚህ ሦስት የሄሮድስ ልጆች ንግሥናን ፈልገው ወደ ሮም ቢሄዱም አስተዳዳሪነቱ ጸናላቸው እንጂ ንጉሥነቱን አላገኙም ነበር ። የአርኬላዎስ ከኢየሩሳሌም መሄድን ታሳቢ አድርገው አይሁድና ሳምራውያን ወኪል በመላክ አርኬላዎስ እንዲነሣ ጥያቄ አቀረቡ ። በተነሣውም ዓመፅ ለመቀጣጫ እንዲሆን ሁለት ሺህ ሰዎች በስቅላት ተቀጡ ። በአርኬላዎስ ላይ የነበረው ጥላቻ እያየለ መጥቶ ሮማዊ ወኪል በእርሱ ፈንታ ተሾመ ። አርኬላዎስም በ6 ዓ.ም. ሥልጣኑን አጣ ።
ታላቁን ሄሮድስ በመሸሽ ግብጽ የነበሩት ሕፃኑ ኢየሱስ ፣ እናቱ ማርያምና አረጋዊው ዮሴፍ ሞቱ እንደ ተሰማ ተመለሱ ። አባቱን በግብር ይመስል የነበረው የይሁዳው ገዥ አርኬላዎስ ስለነበረ ወደ ናዝሬት መሄድን መረጡ ። ምክንያቱን የአባቱን ሥራ እያስፈጸመ ፣ በሺህ የሚቆጠሩ የይሁዳ ነዋሪዎችን እየገደለ ነበርና ። የጌታን መመለስ ቢሰማ አባቱ ያልቻለውን ነገር ለመፈጸም ይነሣ ነበር ። ስለዚህ አርኬላዎስን ላለማነሣሣት ወደ ናዝሬት ሄዱ ። ቍጠኞችን ማነሣሣት ተጨማሪ እሳት በምድር ላይ መለኮስ ነው ። በዚህም የኃጢአት ብዛት መጨመርና የኃጢአት ሎሌ መሆን ይመጣል ። አርኬላዎስ ጌታን መግደል አይችልም ፣ እርሱን አገኘሁ ብሎ ግን ብዙዎችን ይገድላል ። በዚህም ለብዙዎች ማለቅ ምክንያት ላለመሆን ወደ ናዝሬት ሄዱ ። ጌታን አገኝ ብሎ ታላቁ ሄሮድስ የቤተ ልሔም ሕፃናትን ገደለ ፣ ዛሬም ኢየሱስን የምትጠላ ዓለም እርሱን ያገኘች እየመሰላት ተከታዮቹን ትገድላለች ።
ጌታችን ወደ ናዝሬት መሄዱ ትንቢትን ለመፈጸም ነው ። ትንቢት ከእርሱ የመጣ መገለጥ ሲሆን ፍጻሜና እውነት የሚያገኘው በራሱ በክርስቶስ ነው ። የነቢያት ዓይናቸው ፣ እውነተኛ ለመባልም ማኅተማቸው ምጽአተ ክርስቶስ ነው ። ናዝሬት በሰሜናዊው ገሊላ የምትገኝ በኮረብታ ላይ የተመሠረተች ፣ ታሪክ የሚታይባት ማማ ነበረች ። ጌታችን ለልደቱ ናዝሬትን አልመረጠም ። ያለ አባት በምድር ተወልዷልና የናዝሬት ነዋሪዎች ግራ ስለተጋቡ ከትችታቸው ዘወር ማለት ይገባል ። ጊዜ የማይሽረው ሐሜት የለምና ሰዎች በከንቱ ስማችንን ሲያጠፉ ባለመስማት ዘወር እንበል ። በእውነቱ በጌታ እንደ ታየው ከአምስት ዓመት በኋላ ማንም አያስታውሰንም ። ጉድ አንድ ሰሞን ነው ይባላል ። ጌታችን የናዝሬቱ ኢየሱስ ይባላል ። በብሉይ ኪዳን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የለዩ ናዝራውያን የሚባሉ አሉ ። ጌታችን ግን በናዝሬት በማደጉ ናዝራዊ ተባለ ። ናዝሬትን ለምን መረጠ (
ናዝሬት የንቁዎች ፣ የአትንኩኝ ባይ ኃይለኞች ከተማ ናት ። ሁሉም የዓለም ማኅበረሰብ የሚኖርባት ፣ ለሥልጣኔ ቅርብ የሆነ ሕዝብ ያለባት ከተማ ናት ። ናዝሬት ላይ መቆም ከመላው ዓለም ጋር መገናኘት ነው ። ናዝሬት ወደ ይሁዳ ወይም ወደ ደቡብ የሚወስደው መንገድ አውራ ጎዳናው ተዘርግቶባት ሰሜንና ደቡብ እስራኤልን ታገናኛለች ። ከግብጽ ወደ ደማስቆ የሚያልፉ ቃፊሮች ናዝሬት መሸጋገሪያቸው ነበረች ። ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ የሮማ ወታደሮች የሚያልፉት በዚህች ከተማ ነው ። በመገናኛዋ ናዝሬት ሰማይና ምድርን ያስታረቀው ኢየሱስ አደገ ። ሰው ሠራሽ የሆነውን ትብታብ የማይወደው ፣ አስጨንቆ ሳይሆን አስደስቶ የሚገዛው ኢየሱስ ለውጥን በሚወዱ መካከል አደገ ። ዓለምን ያለ መዶሻ ያነጠው የአብ ልጅ የማርያም ልጅ ተብሎ በሥጋ በመጣ ጊዜ በናዝሬት መዶሻ የያዘ አናጢ ሁኖ አገለገለ ። ናዝሬት በአክራሪ አይሁዶች የተናቁ ፣ ደግ አይወጣባቸውም ተብለው ተስፋ የተቆረጠባቸው ሰዎች መኖሪያ ናት ። በናዝሬት የመልካሞች መልካም ኢየሱስ ክርስቶስ አደገ ። የናዝሬቱ ኢየሱስ ሲባል የዓለም ጌታ ነው ፣ የሕዝቦች ቋንቋ ነው ማለት ነው ። በናዝሬት ብዙ ቋንቋ ይነገራልና ። የናዝሬቱ ኢየሱስ ሲባል የኃጢአተኞች ወዳጅ ማለት ነው ። ሰዎች ለንቀት የሰየሙትን ስያሜ እርሱ የእውነት አደረገው ። ስድብን ወስደነው ስንጠቀምበት ተሳዳቢው መሣሪያዬ አልሠራም ብሎ ይተወዋል ።
ናዝሬት ዓለምን የምታገናኝ አውራ ጎዳና ናት ፣ ወደ አባቱ ለመድረስ ጎዳና ፣ ወደ ወለደው ለመግባት በሩ የሆነው ኢየሱስ በናዝሬት አደገ ። ልበ ሰፊው በልበ ሰፊዎች ከተማ አደገ ። ተቆርቋሪው አትንኩኝ በሚሉ ፣ ሊቀርቧቸው በማያስቸግሩ ቀናዎች መካከል አደገ ። ናዝሬት በሰዎች የተጠላች በጌታ የተወደደች ናት ፣ ኢየሱስም አናጢዎች የናቁት አባቱ የወደደው የማዕዘን ራስ ደንጊያ ነው ።
ክብር ምስጋና ለናዝሬቱ ኢየሱስ ይሁን ! አሜን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም.