የሰው ልጅ በሥጋዊ አካሉ ውስን ሲሆን በነፍሱ ግን የማይወሰን ነው። አሳቡ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይሄዳል። ምድርና ሰማይን ያስሳል። አሳብ መሰብሰብ አለበት፣ ያልተሰበሰበ እህል ምግብ አይሆንም፣ ያልተሰባሰበች ምእመንም ቤተ ክርስቲያን አትባልም። ያልተሰባሰበ ሕዋስም አካል አይሆንም። አሳብ ካልተሰበሰበ ጸሎት ጣዕምና ግዳጅ ፈጻሚ አይሆንም። ሰዎችን በትክክል ማዳመጥና መርዳት አይቻልም። ምርምርና የቅኔ ፈጠራ አይኖርም።
አሳባችን ከተበተነ ተረጋግተን መቀመጥና የጠራ ውሳኔ መወሰን እንቸገራለን። የአሳብ መሰብሰብ መረጋጋትና ድል ይሰጠናል። የጀመርነውን ሥራ በሰዓቱ ለመፈጸም ያግዘናል።
አሳብ ከተበታተነ በሥራ ስፍራችን ከመቀመጥ መቅበጥበጥ እንጀምራለን፣ በዚህም ጉልበታችን በከንቱ ይባክናል። ቅደም ተከተል ያለው ነገር ማከናወን ስለማንችል ዛሬ ላይ ትልቅ ጉድለት ይፈጠርብናል። ጸሎታችን እርካታ እያጣ ልማድን ለማድረስ ብቻ ይሆንብናል። ቢሆንም ጸሎት ምግብ ነውና አይቆምም። ሰዎች በአሳብ መበታተን ውስጥ ስንሆን በቀላሉ ያውቁታል ፣ ምክንያቱም ሰላማችን ስለሚሽሸ ነው። ብዙ ነገሮችን መያዝና መጣል እንጀምራለን። ቀን ሰላም፣ ሌሊት እንቅልፍ ማጣት ይከሰታል። አትኩሮትን ስለምናጣ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ሕጻናትን፣ ሥራዎቻችንን መጉዳት እንጀምራለን። መንገዱን ከቀልባችን ሆነን ስለ ማንጓዝ ለአደጋ እንጋለጣለን። ብስጩና በቀላሉ የምንቆጣ ሰዎች እንሆናለን። ራሳችንን መቆጣጠር ባለመቻላችን ራስን መውቀስ ውስጥ እንገባለን። ተከታታይነት ያላቸውን ነገሮች አናደርግም፣ ስሜታዊ ድርጊቶችን እናከናውናለን። ውጤት በሌለው ነገር ጊዜያችንን እናባክናለን። ስብከት ለማዘጋጀት ፣ በጽሞና ለማዳመጥ እንቸገራለን።
የአሳብ መበታተን ሁሉን ልያዝና ልጨብጥ ከሚል ፍላጎት ይወጣል። ሁሉን ሀብት፣ ሁሉን ትምህርት፣ ሁሉን ሰው፣ ሁሉን አገር ካልያዝኩ የሚል ሰው የሚደመድመው በባዶ ነው። ጫጫታ ስፍራዎች ፣ እርጋታ የሌላቸው ሰዎች አሳባችንን ይበትኑታል። ዕረፍት የለሽ የሆኑ ሰዎች ዕረፍት የማሳጣ ት አቅም አላቸው። ሰላም ወደ ጎረቤት ይጋባል፣ ዕረፍት የለሽነትም ይገባል። ያልተጨበጠ ነገርን የሚያወሩ፣ በምኞት ብቻ የሚኖሩ ሰዎችን መቅረብ አሳብን በጣም ይበትናል። ብዙ ጓደኞች ማብዛት፣ የት ልሂድ እያሉ ሲያማርጡ መዋል የአሳብ መበታተንን ያመጣል። በጊዜ እውነተኛ ወዳጆችን አለመያዝ፣ ለሰዎች እውነተኛ ጓደኛ መሆን አለመቻል የአሳብ ብክነት ያስከትላል። ብዙ ዕድሎች ፣ የብዙ ሙያ ባለቤት መሆን አደጋ አለው። ብዙ ዕድል ያለው ሰው ተጎጂ ነው፣ ብዙ ሙያ ያለውም ድሃ ነው። በአንድ ነገር ላይ የሚያተኩሩ ውጤታማ ይሆናሉ። ብዙ የትምህርት ዓይነቶች የሚማሩ ሁሉንም ሳያውቁ ይቀራሉ። ነገሮችን በፕሮግራም፣ የሚቀድመውን በማስቀደም የማይከውኑ በአሳብ መበታተንና በጸጸት ይኖራሉ። በሕይወት ውስጥ ከባዱ ኃላፊነት ጊዜን ማስተዳደር መቻል ነው።
ብዙ መረጃዎችን መስማት፣ ስለ ሰዎች ከመጠን በላይ ማወቅ አሳብን በክሎ ይበትነዋል :: ማኅበራዊ ሚዲያን በሥርዓት አለመጠቀም የጤና፣ የአእምሮ ጉዳት ያስከትላል። ወረተኛነትና አዲስ ነገር ብቻ ፈላጊነትን ስለሚያመጣ ራስን ወደ መጥላት ያደርሳል። አጉል ነጻነት የአሳብ መበታተን ያመጣል። ሚስትን ሸኝቶ፣ ባልን አርቆ መኖር የሚያስደስተኝን ማድረግ አለብኝ የሚል ፍላጎት ስለሚያመጣ የአሳብ መበታተን፣ የሞት ጉድጓድ ውስጥ መግባትን ያመጣል። ሰይጣን ዋነኛ ዒላማው የሰው ሕሊና ነው ። በጸሎት ሰዓትና ቃሉን በምናነብበት ጊዜ አሳባችንን ይዋጋል። የምንጸልየውንና የምናነበውን ካላወቅን ጥቅም አናገኝም። ለሁሉ ልድረስ ማለት፣ ሰዎች እንዳይቀየሙኝ እያሉ ለይሉኝታ ብቻ መኖር የአሳብ ዝብርቅን ያመጣል። ድህነትም አሳብን ይበትናል። የሚጠብቁት ሰው ካለ አሳብ ይበተናል። ። በክፉ ነገር የተያዙ ልጆች ካሉን ስጋት አሳብን ይበትናል።
እያደናገሩ መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች የአሳብ መበታተንን ያመጣሉ። የሚጮህ ባል፣ ጨቅጫቃ ሚስት፣ የሚመራበት እቅድ የሌለው ገዥ፣ ዕረፍት እንዳይሰማን የቤት ሥራ የሚያመጡብን ሰዎች፣ ወሬ አቀባዮች፣ አታላዮች ፣ ሌቦች እነዚህ ሁሉ የአሳብ መበታተንን ያመጣሉ።
አሳብን ለመሰብሰብ የተረጋጋ ማንነትን ማዳበር፣ በእምነት መኖር፣ ልክን ማወቅ፣ ሁሉ ቢሰጠንም ሁሉንም እንደማንጨብጥ መረዳት ተገቢ ነው። ከአሳብ አልፎ አዚም ፣ ድንዛዜና እንቅልፍ የሚጥል ስሜት ካለ ሰይጣናዊ ውጊያ ነውና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መገሠጽ ይገባል። በቂ እንቅልፍና ዕረፍት ማድረግ መንፈሳዊ ተግባር ነው። ከመጠን በላይ መተኛት እንጂ መተኛት ስንፍና አይደለም :: የተረጋጉ ሰዎች ጋር መዋል መረጋጋትን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ያለው ብቻ እንደሚሆን መረዳት ያረጋጋል። እንደ ሰው እንሞክራለን፣ ካልተሳካ የእኛ ጥፋት አይደለም። የሰው ድርሻ መሞከር እንጂ ማሳካት አይደለም። ያለው ይሁን ብሎ መረጋጋት ይገባል ::
እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ !
ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም.