የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ / ክፍል አንድ

ቁጭ ብሎ የምናየው አብዛኛው ሰው በአሳብ እየሮጠ ነው ። ስለ ሰላም የሚያወራው በአሳቡ ብዙ ጦርነት ላይ ነው ። አንዳንድ ሰው በአሳቡ ፣ ደግ ነገር ማሰቡን እንደ ከንቱ ነገር ያየዋል ። የተግባር መነሻ አሳብ መሆኑን ይዘነጋዋል ። ክፉ አሳብን ፀንሶ በውስጡ ሲፈራገጥ እየሰማ ደግሞ ዝም ብሎ የተቀመጠ ዝንጉ አለ ። ያ የአሳብ ፅንስ ሲወለድ ልደቱ ሞት መሆኑን ዘንግቷል ። እግዚአብሔር በአሳብ ይመዝናል ። አንዳንድ ሰው ንግግሩ ማር ጠብ ነው ። እግዚአብሔር ግን በልብ ውስጥ ያለውን የመርዝ ቢልቃጥ ያያል ። አንዳንድ ሰው ቀና ነው ፣ ንግግር ባለመቻል ግን ደግነቱን እሬት ይለውሰዋል ። የአሳብ ፍልሚያ ያለባቸው ብዙ ሰዎች እየመጡ ነው ። ዘመናዊው ዓለም እጆቻችንን አለስልሶ አእምሮአችንን ግን ቋጥኝ ያሸከመ ነው ።

በድሮ ዘመን የሰዎች አእምሮ ነጻ ፣ አካላቸው ግን በብርቱ የሚታገል ነበር ። በዚህ ዘመን ደግሞ አካል አጋዥ አግኝቶ ፣ አእምሮ ግን ጫና ውስጥ ገብቷል ። የሚታዩት የሚሰሙት ነገሮች በቀጥታ እያወኩ ያሉት እጅና እግርን ሳይሆን አሳብን ነው ። አሳብ በሱቅ የሚሸጥበት ፣ ከአልጋቸው ሳይወርዱ ሰዎች ብዙ ገንዘብ የሚያጋብሱበት ዘመን ነው ። የዚያን ያህል አእምሮአቸው የተረበሸ ከተማ ነው ። ወላጆቻቸው በስሙ ጠርተውት የማያውቁትን ገንዘብ በሃያዎቹ ዕድሜ ያሉ ልጆች በእጃቸው ጨብጠዋል ። ሰላም ግን የላቸውም ። አለመርካታቸውን በገንዘብ ብዛት የሚያርቁት እየመሰላቸው ብዙ ፕሮጀክት ይዘረጋሉ ፣ ያለ እግዚአብሔር የሚደፍኑት ጣሪያ ይበልጥ እያፈሰሰ ያስጨንቃቸዋል ። ብቻ የሁላችንም አእምሮ መጠኑ ይለያይ እንጂ በትግል ውስጥ ያልፋል ።

“መንፈሳዊ ሕይወትን የምዘልቀው አልመሰለኝም” በማለት ብዙ ሰዎች ደንብረው ይናገራሉ ። መንፈሳዊ ሕይወት እውቀት ያስፈልገዋል ። አሊያ የውጊያው ረቂቅነት ሊያስደነብርና ወደ ኋላ ሊመልስ ይችላል ። ቀድሞ ዓለማዊ ሳሉ አስበውት የማያውቁትን አሳብ አሁን ያሰቡ ሲመስላቸው ራሳቸውን መጥላትና ተፈጥረው እንዳልተፈጠረ መሆንን ይመኛሉ ። እግዚአብሔር ለራሳቸው የተዋቸው መስሏቸው ይደነግጣሉ ። የመንፈሳዊው ዓለም ውጊያ ግን አሳባዊ እንጂ ውጫዊ አይደለም ። ውጫዊው ውጊያማ አካልን ለእሳት ፣ ለስለት ሰጥቶ ሰማዕት የሚያደርግ ነው ። ውስጣዊ ውጊያው ግን ሁሉም ሰው የሚያልፍበት ነው ። ሁሉ ሰው ሰማዕት አይሆንም ፣ ሰማዕት ዘእንበለ ደም የሚባለው ከአሳቡ ጋር ታግሎ እግዚአብሔርን የሚከተለው ሰው ነው ። ውጫዊው ውጊያ ሰው ስለሚያየው አዛኝ ይገኝበታል ። ውስጣዊው ውጊያ ግን ሰውዬው ብቻ የሚሰማው ስሜት ነውና ልቅሶው የብቻው መስሎ ይሰማዋል ። በዚህ ውጊያ የቅዱሳን ገድላቸው መማሪያ ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አብሮነት መጽናኛ ነው ።

ያልተመለሱ ጸሎቶች ሁላችንም አሉን ። አገልጋይ የሆንነው የሁሉንም ጥያቄ መልሱን ስላገኘነው አይደለም ። “ብቻ ጥያቄ አለኝ” እያሉ አገልጋዮችን የሚያስፈራሩ ሰዎች አሉ ፣ አገልጋዩም ጥያቄ አለው ። ሕይወት ግን ምሥጢር ናት ፣ በመታወቅዋ ብቻ ሳይሆን ባለመታወቅዋም ውብ ናት ። የሁሉንም ነገር መልስ ብናውቀው ኖሮ ኑሮ ይሰለቸን ነበር ። አለቃ ገብረ ሃና “እዛም ቤት እሳት አለ” አሉ ። “ሁሉ ሰው ከእግዚአብሔር ሲቀበል እኔ ብቻ ቀረሁ” የሚል ስሜት የአሳብ ውጊያ ውስጥ ይከታል ። ብቻ ራሳችሁን ፈርታችሁ ታውቃላችሁ ? ራሳችሁ ሊያመልጣችሁ ሲታገላችሁ ለየትኛው ፖሊስ ጣቢያ ታመለክታላችሁ ? “ነፍሴን አደራ መድኃኔ ዓለም” ከማለት የበለጠ ጸሎት የለም ። የነፍስን አደራ የሚቀበል እርሱ ብቻ ነው ።

“እነርሱ ምን አለባቸው ?” የምንላቸው የበረቱ የተባሉት መንፈሳውያን ሰዎችም እኛ በምናልፍበት የአሳብ ጦርነት ውስጥ ያልፋሉ ። ደረጃው ይለያይ እንጂ ይህን ውጊያ የማይቀምስ ሰው ሊኖር አይችልም ። ውጊያው አሰላለፍ አለው ። ውስጣዊ ሰልፉ በገነነ ሰዓት ዓለም ከንቱ ሁና ትታየናለች ። “ከዚህ ልውጣ እንጂ ምንም አያምረኝም” እንላለን ። የውስጡ በረድ ሲል ደግሞ የቤት አሳብ ሳይሆን የቤቶች አሳብ ይመጣብናል ። አልጠግብ ባይነት ይዋጋናል ። “አንድ ብቻ ዋስትና አይሆንም ፣ አሥር ያስፈልጋል” እንላለን ። ይህኛው ውጊያ ጋብ ሲል መንፈሳዊ ነገር እውነት መስሎ አልሰማን ይላል ። መጽሐፍ ቅዱስ የቄሶች የአገዛዝ በትር ፣ ጸሎት ራስን ማሞኛ ፣ ስብከት ጊዜ መግፊያ ፣ ምክር ራስን ማታለያ መስሎ ይሰማናል ። ይህ ቀጥተኛ የሰይጣን ውጊያ ነው ። ሰይጣን በወኪል ይዋጋል ፣ ራሱ በቀጥታ ሲዋጋን ግን ይህ ስሜት ይከሰታል ።

የአሳብ ሰልፍ ያለባችሁ ፣ ራሳችሁን የምታጡት መስሎ የሚሰማችሁ ፣ ከራሴ መዳን እሻለሁ የምትሉ ፣ ከሁሉ በላይ የውጊያው ጠባይ ያልተረዳችሁ ትንሽ አሳብ ባካፍላችሁ ፈቃዳችሁን እጠይቃለሁ ። ጌታ ሆይ ባንተ አደባባይ መካሪና ተመካሪ የለምና አንተው በምክርህ አጽናን !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ