የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ/10

7- ዕረፍት ማጣት

የአሳብ ውጊያ ከሚያመጡ ነገሮች አንዱ ዕረፍት ማጣት ነው ። አንዳንድ ሰዎች በእግራቸው ሮጠው ውጤት ያመጣሉ ፣ ሌሎች ደግሞ ተቀምጠው በአሳብ ሲሮጡ ይኖራሉ ። የጀመሩትን ሳይጨርሱ ሌላ የሚጀምሩ ፣ በሕይወት ውስጥ ቀዳሚውንና ተከታዩን ፣ አስቸኳይና የማያስቸኩለውን የማይለዩ ሰዎች ዕረፍት የላቸውም ። ብክነትን ትጋት አድርገው ስለሚመለከቱት ሁሉም ሰንፎ እነርሱ ብቻ የተጉ ይመስላቸዋል ። ነገ ምን እንደሚኖሩ ሳያውቁ ሁሉን ዛሬ መፈጸም አለብኝ ብለው የሚያስቡ ፣ የፍጹምነት አቀንቃኝ የሆኑ ፣ በድርብርብ አጀንዳዎች ነፍሳቸውን የሚወጥሩ አያሌ ናቸው ። ጭንቀትን በጭንቀት ለማምለጥ የሚፈልጉ ሰዎች ራሳቸውን ባልተገቡ ነገሮች በመወጠር ያስፈራቸውን ቀን ለማለፍ ይሞክራሉ ። በእርግጥ በቆሻሻ ውኃም እሳትን ማጥፋት ይቻላል ። ጉዳይን በጉዳይ መተካት ፣ የሚያስጨንቅ ቀንን በዋል ፈሰስ ለማለፍ መሞከር የተለመደ ነው ። በማኅበራዊ መገናኛዎች ፌዝ የበዛበት ነገር ስናይ ጭንቀት ስለበዛና ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ትውልዱ የወሰደው ምርጫ ይመስላል ። መሳቅ ሁሉ መሳቅ አይደለም ፣ እያረሩ እንደ ማሽላ የሚስቁ ብዙ ወገኖች ናቸው ። ከጭንቀት ለማምለጥ ራስን መወጠር ካስፈለገ በሥራ ፣ በትምህርት ፣ ተፈጥሮን በመንከባከብ ፣ ቤተ ክርስቲያንን በማገዝ ቀኑን መሻገር ይቻላል ።

ዕረፍት ማጣት በብዙ መንገድ ይመጣል ። ፍቅር በሚመስል ይሉኝታ የሚኖሩ ሰዎች ዕረፍት የላቸውም ። በሁሉ ቦታ መገኘት የሚችሉ የሚመስላቸው ፣ ለሁሉ መሳቅ ፣ ለሁሉ አለሁ ማለት ግዴታቸው መስሎ የሚሰማቸው ሰዎች ዕረፍት በማጣት ውስጥ ያልፋሉ ። ሰው ሁሉ እየሳቀ እንኳ ያስቀየሙ እየመሰላቸው በውስጣቸው የሚበረግጉ ፣ ተበድለው ይቅርታ የሚጠይቁ ፣ ሁሉን በመፍራት ዝቅ ብለው ሰባራ የሆኑ አያሌ ናቸው ። ሊፈጽሙት የማይችሉትን ነገር ቃል የሚገቡ ሰዎች ለቃላቸው ታማኝ ለመሆን ሲሞክሩ ሁሉም ነገር ድርብርብ ይሆንባቸዋል ። የወደዱትን ሰው መጥላትና መሸሽ ይጀምራሉ ። ራሳቸው በጀመሩት አጉል መንገድ ሰዎች የተለየ ነገር እንዲጠብቁባቸው ያደርጋል ። ስልካቸውን ማጥፋት ፣ ወይኔ እገሌ ባልደወለ በሚል ፍርሃት ውስጥ ማለፍ ይጀምራሉ ። እግዚአብሔር ያላሸከማቸውን ሸክም በመሸከምም ሕይወታቸውን ያደክማሉ ። ከሌላቸው ነገር ላይ ለመቸር የሚሞክሩ ፣ “ዘመደ ብዙ ጠላው ቀጭን ነው” እንዲሉ ሁሉን ላስደስት ሲሉ ሁሉን የሚስከፉ ሰዎች አሉ ።

ቃል መግባት አስቀድሞ አቅምን በመመዘን ሊሆን ይገባዋል ። ስሜታዊና እውነተኛ የሆኑ ሰዎች አሉ ። በስሜት ቃል ገብተው ስሜቱ ሲበርድ የሚረሱ አሉ ፣ አንዳንዶች ግን ስሜታውያን ቢሆኑም እውነተኞች ናቸውና ለቃላቸው ሲተጉ ይወጠራሉ ። በዚያ ሰዓት ማድረግ የሚችሉ ፣ ሁሉም ነገር በትእዛዝ ቃል የሚቀርብላቸው ይመስላቸዋል ። የሚችሉትን ሳይሆን የሚመኙትን ነገር ቃል ይገባሉ ። በዚህ ምክንያት ዕረፍት በማጣት ውስጥ ያልፋሉ ። እነዚህን ሰዎች ልናዝንላቸውና ልናሳርፋቸው ይገባል ። የደጎች ማነስ ዓለምን ያጨልማልና እንዳይጎዱ መንከባከብ ያስፈልጋል ። ሰው የሚያጠቃው ቸሩን ነው ። ንፉግ ተከብሮ ሲኖር ፣ የሚደፈረው ቸር ሰው ነው ። የቸር መጨረሻ መሰደብ ቢሆንም ቸርነት ግን የእግዚአብሔር ጠባይ ነውና ማብዛት ይገባናል ። የሰውዬውን ይሉኝታ በመጠቀም ለመበዝበዝ መሞከር ተገቢ አይደለም ። ሞኙም ብልህ አምላክ እንዳለው ማሰብ ይገባል ።

ዕረፍት ማጣት ከተደራራቢ ኃላፊነቶች ይመጣሉ ። የልጃቸውን ጨርሰው የልጅ ልጃቸውን የሚንከባከቡ ፣ የዕድሩንም የዕቁቡንም ኃላፊነት ሲጥሉባቸው እንቢ የማይሉ ፣ ጎበዝ ተብለው ተወድሰዋልና ሰነፍ ላለመባል የሚቸገሩ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው ላይ ቀንበር አብዝተው ይጎብጣሉ ። ድርሻዬ እስከምንድነው ? አቅሜስ ምን ያህል ነው ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ። የተሳፈሩበት ባቡር መቆሚያ ፌርማታ አጥቶ የሚጋልብባቸው የዘመናት አውታታዎች አያሌ ናቸው ። የምሮጠው ለምንድነው  ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ። ምክንያትና ግብ የሌለው ነገር በምድር በሰማይ ያከስራል ።

ዕረፍት ማጣት ሁሉን እኔ ልሥራው ከሚል ስጉነት ይመነጫል ። ሰውን የማያምኑ ፣ ሁሉም ሰው የሚያበላሽ የሚመስላቸው ተጨናቂዎች ሥራውን ሳይጨርሱት ራሳቸው ያልቃሉ ። ሥራን ለሠራተኛው መስጠት መቻል የአመራር ብቃት ነው ። ሥራን ማከፋፈል ፣ በውልና በተጠያቂነት ስሜት ሌሎችን ባለ አደራ ማድረግ ለእኛም ለሥራውም ለሰዎቹም የኑሮ ልምድ ወሳኝ ነው ። አሊያ እኛ እናልቃለን ፣ ሥራው ግን አያልቅም ። የብዙዎችን ሥራ ፈትነትም እናስፋፋለን ። ዕረፍት ማጣት ብዙ ሥራና ብዙ ትምህርት የሚጀምሩ ሰዎች የሚያልፉበት ነው ። የአንዳንዶች ሩጫ ለዚህች አጭር ዕድሜ አይመስልም ። ሕይወት የሺህ ኪሎ ሜትሮች ሩጫ ናትና ፉት ብለን አንጨርሳትም ፣ እያረፍን የምንጓዛት ናት ። እግዚአብሔር አምላክ ሲፈጥረን ለሳምንቱ ሰንበትን ፣ ለዕለቱ ደግሞ ሌሊትን አዘጋጅቶ ነው ። በስድስት ዓመት ደግሞ አንድ ዓመትን ዕረፍት አውጆ ነው ።

የቤተሰብ ኃላፊነት ዕረፍት ያሳጣል ። “እጸድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠለጠለች” እንደሚባለው ብዙ ቤተሰብ ለሚንከባከባቸው ሰው ሸክም ይሆናሉ ። ሰውን ምንም ብንወደው ሸክም እንቀንስለታለን እንጂ አናስቀርለትም ። ቤተሰብንም መንገዱን ማሳየት እንጂ ሁልጊዜ እሹሩሩ ማለት የወጣት አዛውንትን ማፍራት ነው ። አጉል ባልንጀርነት ዕረፍት ያሳጣል ። ቀን በሥራ ፣ ማታ በመጠጥ የሚደክሙ ሰዎች የአጉል ባልንጀርነት ሰለባዎች ናቸው ። ፊልሙ ፣ ኳሱ ፣ አጉል ንባቡ ገደብ ካልተሰጠው ዕረፍት ያሳጣል ። ጓደኛን ማብዛት የዕረፍት ማጣት መገኛ ነው ። ለልብ ወዳጆች ቅድሚያ መስጠት ይገባል ። “ጓደኛ ያበዛ መከራ አበዛ” እንዲሉ ። ዕረፍት ማጣት ለከፍተኛ የአሳብ ውጊያ ይዳርጋልና ኑሮአችንን መገምገም ያስፈልጋል ። አንድም ገባ ሺህም ገባ ዓለም ጎዶሎ ነው ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ