የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ/12

የመጨረሻ ክፍል

ተጽእኖውና መፍትሔው

የአሳብ ውጊያ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች በብዙ የማይታይ ትግል ውስጥ ይሆናሉ ። የሚታየው ታጋይ ወንድምም ፣ ጓደኛም ቢጠራ ይሸነፋል ። የአሳብ ውጊያ ግን ፖሊስ የማይጠራበት ፣ ወንድሜ ድረስልኝ የማይሉበት ነው ። ቢሆንም በእግዚአብሔር ዓይን ግን ቀላል ነው ። የአሳብ ውጊያ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች ሁሉም ነገር ቢኖራቸውም ምንም የሌላቸው ያህል ይሰማቸዋል ። የአሳብ ውጊያ በአብዛኛው ስሜት እንጂ እውነት አይደለምና ። ዘመኔ ገሰገሰ እያሉ ከሚገሰግሰው ጊዜ ጋር የአሳብ ሩጫ የሚጀምሩ የአሳብ ፍልመኞች አሉ ። ችግር በእንቅስቃሴ እንጂ በአሳብ ብዛት አይወገድም ። ጨለማ ላይ ቢያፈጡ ጨለማ አይርቅም ። ጥቂት ብርሃን ጨለማን እንደሚያሸንፍ ሁሉ ጥቂት እንቅስቃሴም ችግርን ድል ይነሣል ። የሆነው ሁሉ ሆኗል ። መፍትሔው ምንድነው ? ብሎ ስለ መፍትሔው ማሰብ የአንድ ልከኛ ሰው ጠባይ ነው ። ስህተቶቻችን ፣ ተዉ እየተባልን የገባንባቸው ሁኔታዎች የሚያሳዝኑ ቢሆኑም ከእነርሱ መማር ያለ መሳሳት ያህል ነው ። የፈረሱት ኅብረቶች ፣ የተናደው ትዳር አሳዛኝ ቢሆንም ከቻልን እንደገና ለመጠገን መሞከር ፣ አሊያ የዚህ ችግር የመጀመሪያና የመጨረሻ እኛ አለመሆናችንን ማሰብ አቅም ይሰጣል ።

በሰው እጅ ስላለፉት ፣ በአደጋ ስላጣናቸው ሰዎች ስናስብ ጌታችን በሰው እጅ እንደ ሞተና መራራ ስቃይን እንደ ተቀበለ በማሰብ የእኛ ሰዎች ከእርሱ እንደማይበልጡ ማመን አለብን ። የሚሆነው ሲሆን የነበረ ነው ። አዲስ ነገር ምንም የለም ። “ዓለም አዲስ የምትመስለው ታሪክን ያላነበበ ሰው ነው” እንዲሉ ።

የአሳብ ውጊያ ከሚያመጡ ነገሮች አንዱ እንደበደልነው ሳያውቅ ከእኛ ጋር የሚኖረው ሰው ሊሆን ይችላል ። ጥሩነቱ በየዕለቱ መቅጫ ሆኖብን “ተናግሬ ባርፍስ ?” የሚል የአሳብ ውጊያ ውስጥ ልንገባ እንችላለን ። ኑዛዜን መልካም የሚያደርገው ሁለታችንም በምንናውቀው በደል ነው ። ሁለታችንም በማናውቀው በደል መናዘዝ የሚያስፈልገን ለእግዚአብሔር ብቻ ነው ። ሰላም ለማግኘት ብለን የሌላውን ሰላም መንካት አይገባንም ። አንዳንድ የበደልናቸው ሰዎች በሕይወት የሉምና እንጨነቃለን ። ሕያው እግዚአብሔር ግን እነርሱን ይወክላልና እርሱን ይቅርታ መጠየቅ ይገባል ። የአሳብ ውጊያ ብዙ ተጽእኖዎች ያሉት ሲሆን በጸሎት ሕይወታችን ላይ ደካማ ያደርገናል ።

እግዚአብሔር ጸሎቴን አልሰማም የሚለው አሳብ በራሱ የአሳብ ውጊያ ያመጣል ። እግዚአብሔር ያልሰማው ጸሎት የለም ። ያልመለሰው ጸሎትም የለም ። እኛ እንደምንፈልገው ስላልመለሰ ዝም ያለን ይመስለናል ። ጠብቁም መልስ ነው ፤ አይሰጣችሁምም መልስ ነው ። ጸሎት ከአሳብ ውጊያ የምንድንበት ትልቁ መሣሪያ ነው ። ለእግዚአብሔር የሚናገር ሰው ለራሱም ሆነ ለሰው ካልተናገርሁ የሚል ምጥ የለበትም ። ጸሎት ስናቆም ግን ችግራችንን ባሰብነው ቍጥር ያስፈራናል ። ትንሹ ትልቅ እየመሰለን ያውከናል ። እግዚአብሔርን ስናይ ችግራችን አንሶ ይታየናል ። እምነት ብናጣ እንኳ መጸለይን ማቆም የለብንም ። ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚያደርግልን ስለ ታማኝነቱም ነውና ። ጸሎት የጸጋው መንገድ እንጂ የእኛ የብቃት መንገድ አይደለም ። ጸሎቴ አልተሰማም የሚል ሰው በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ሞገስ አላገኘሁም የሚል መረበሽ ይገጥመዋል ። ይህ ስሜት ደግሞ ወደ ጠቆረ ሰማይ እንደሚያንጋጥጥ ምስኪን ሰው ያደርገዋል ።

ጌታችን በቀትር የጨለመበት ፣ በቀትር ለጨለመባቸው ሰዎች ተስፋ ለመሆንም ነው ። እርሱ በሰው ልጆች የስቃይ መልክ ባይገለጥ ኖሮ የሁላችን መጽናኛ አይሆንም ነበር ። “የማልፍበትን ጌታ ያውቀዋል” ብለን ስናስብ ያን ጊዜ ዕረፍት ይሰማናል ። ከሁለት መልካም አንዱን መምረጥ ባለመቻል የሚሰቃዩ የአሳብ ታጋዮች አሉ ። ለዚህም መጸለይ ፣ ቃለ እግዚአብሔርን ማስተንተንና መንፈሳውያን አባቶችን መጠየቅ ይገባናል ።

የአሳብ ውጊያ የመርሳትን ችግር ያመጣል ። አእምሮአችን በተደጋጋሚ አንድ አሳብ በመሞላቱ አዲስና እውቀት ነክ ነገርን መያዝ ያቅተዋል ። አንድ ነገርን ለማትረፍ ብለን ብዙ ነገርን እናጣለን ። አለመሆንና አለመሳካትም የሕይወት ገጽታ ነውና በደስታ መቀበል መልካም ነው ። የአሳብ ውጊያ ሞት ፣ ሞት የሚያሰኝ ስሜትም ሊያመጣ ይችላል ። እኔ ብሞት ማንን አጎዳለሁ? በሚል ስሜት ሰይጣን ሕይወትን ሳይሆን ሞትን ሊያስመርጠን ይፈልጋል ። ሰይጣን ሞትን የሚያስመርጠን በከንቱ መንገድ ለዘላለም የእርሱ እንድንሆን ነው ። የሞት አሳብ ሲመጣ ከዳዊት መዝሙር ጋር በመሆን ጠላትን መገሠጽ ይገባናል ። “አልሞትም በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ።” መዝ. 117፡17 ።

የሰው ልጆች ችግር ተመሳሳይ ነው ። ሩቅ አገር ካለው ሰው ጋር ብቻ ሳይሆን የዛሬ አምስት ሺህ ዓመት ከነበረው ሰው ጋር ፈተናችን ተመሳሳይ ነው ። ብቻችንን የሆንን ሲመስለን ውጊያ እያንገዳገደን ይመጣል ። የአሳብ ውጊያ ግን የእኛ ብቻ ሳይሆን የሚሊየኖች ፈተና ነው ። ወደ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት ስንገሰግስ ጨለማን እየራቅን እንመጣለን ። የአሳብ ውጊያ በበረታ ሰዓት ያለማቋረጥ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት ይገባል ። አንድን ነገር ላለማሰብ በጣርን ቍጥር ይበልጥ እናስበዋለን ። አሳብ ግን በአሳብ ይሻራል ። የሞት አሳብ በሕይወት አሳብ ይሻራል ።
አሜን !

ተፈጸመ

አነቃቅቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን ። ለዘላለሙ አሜን ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ