የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ /5

2- ለራስ ማዘን

ለራስ ማዘን እንደ ሱስ ያለ ነገር ነው ። የለሙትን ሳይሆን የፈረሱትን ፣ የቆሙትን ሳይሆን የሞቱትን ፣ የገቡትን ሳይሆን የወጡትን እያሰቡ ወደ ውስጥና ወደ ውጭ ማንባት ነው ። በሕይወት ውስጥ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ራሳችን ለራሳችን ጣዖት የሚሆንብን ጊዜ አለ ። ብዙ ነገሮችን አትኩሮ ማየት ለኀዘን ይዳርጋል ። ሰዎችን በጣም አትኩሮ ማየት ሕይወትን ያመሰቃቅላል ። አንዳንድ ነገሮችን አለማወቅና አለመስማት ሰላምን ይጠብቃል ። “ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” እንዲሉ “አጥብቆ ጠያቂም የእናቱን ይረዳል ።” ራስንም ያለ እግዚአብሔር ምሕረት መመልከት ተስፋ ቢስ ያደርጋል ። የቀድሞ ጉልበት ፣ የቀድሞ መልክ ዛሬ የለምና ይህን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል ። ሰው ከተወለደበት ቀን ጀምሮ እየሞተ ያለ ፍጡር ነው ። ጥርሱ ሲሰበር ፣ ዓይኑ ሲደክም ወደሚጠላው ሞት እየተጓዘ ነው ። ሞት የአጠቃላይ መጠሪያ እንጂ በየቀኑ በምንሰማውና በምናየው ነገር በጥቂቱ እየሞትን ነው ። እነዚያ በአካል ሲሞቱ እኛ በአሳብ መሞታችን እርግጥ ነው ።

ከሳ ደረቴ መነመነ ፣
ሕመም የለብኝ ምንድን ሆነ ?
የድሮ መልኬ ይጥፋኝ ወይ ?
ሰው ኑሮውን መሳይ ።

ለራስ ማዘን ተክዬ አልበቀለም ፣ ወልጄ አላደገም ፣ ራእዬ አልሠመረም ፣ ትግሌ ድል አላገኘም ፣ ለፍቼ አላደኩም ፣ ነግጄ አላተረፍኩም ፣ አምኜ አልተጠቀምኩም ፣ ወድጄ አልተወደድኩም ፣ ደግ ሆኜ ደግ አላገኘሁም ፣ ተመርቄ አልተደሰትኩም … በሚሉ አሳቦች የሚመጣ ውስጣዊ መተረማመስ ነው ። ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ፣ ሰውን ማራቆት በሚወዱ ሰዎች ያመነውን እንዳላመነ ፣ የሠራውን ደግ ክፉ እንደሆነ ሲነገርበት የሰው ልጅ አለመኖር ይሰማዋል ። በችግር ያሳደጋቸው ልጆቹ ወቃሽ ከሳሽ ሲሆኑበት ፣ ትዳሩ በአደባባይ ሲያራቁተው ፣ ወዳጆቹ ሲክዱት ፣ ፍቅር የምጣድ ብልጭታ ያህል እንኳ ዕድሜ ሲያጣበት ልቡ ስስ እየሆነ እያዘነ ይመጣል ። ሰዎች በወረታቸው እንደሸሹት ሳይሆን በእርሱ ችግር እንደ-ራቁት ሲያስብ በግምት ይቃጠላል ። “ከሰው ብዙ አትጠብቅ” የሚል የዘመኑ ምክር ከሰው ምንም አትጠብቅ ተብሎ የሚተረጎም ነው ። ከሰው ካልተጠበቀ ግን ከማን ይጠበቃል  ሰው የሰውነቱን ያህል መገኘት አለበት ። ደግ ማድረግ ባይችል እንኳ ለተደረገለት ደግ ነገር ማመስገን ያሻዋል ። አውሬ እንኳ መጋቢውን በሚያከብርበት ዓለም ያጎረሱንን መንከስ የጭካኔ ጭካኔ ነው ። ሰው ለመሆን ጥረት የሚያደርግ ሰው ፣ ሰው መሆን ባቃታቸው እያዘነ ከመጣ ከመልካም መንገዱ እየላላ ይመጣል ። ሁሉም ሰው የራሱን ሩጫ መፈጸም አለበት ።

የሰው ልጅ በዚህ ዘመን ዓሣ እንደ-ላሰው ድንጋይ ሙልጭልጭ እያለ ነው ። ጠበቅ ያለ ሃይማኖት ፣ ጠብቅ ያለ ፍቅር ከክህደትና ከጥላቻ በላይ እየከበደው ነው ።

“ረጅም መቀነት ሳይስቡት ይጠብቃል ፣
የዘመኑ ፍቅር ሳይጀምሩት ያልቃል ።”

“በሰም የተጣበቀ ጥርስ ፣ ቢስቁበት አያደምቅ ፣ ቢበሉበት አያደቅቅ” እንዲሉ የዘመናችን ፍቅርም ለደስታም ለመጠቃት ቀንም አልሆን እያለ ነው ። የዚህ ዘመን የሰው ልጅ ትልቅ ፈተና ወረት ነው ። ወረት የኑሮ ዘይቤ ሁኖ መጥቷል ። ማስታወቂያው ሁሉ ትላንት አዳንቆ ያስገዛንን ነገር ዛሬ ጣሉት እያለ የሚያባብል ነውና ወረት የዘመኑ ጎርፍ ሁኗል ። በዚህ ዓለም የቀረን አንድ ደቂቃ ከሆነም በዚያች አንድ ደቂቃ እውነቱን ኖረን ማለፍ ክብር ነው ። ሽንገላ በበዛበት ፣ ሰዎች በቃላቸው በማይገኙበት ዘመን በራስ ማዘን ሊከሰት ይችላል ። ምን እንደሚፈልጉ ከማያውቁ ሰዎች ጋር መኖር ፣ ምን እንደሚፈልግ የማያውቅ ሕዝብን መምራት በራስ ማዘንና ቀጥሎም ጨካኝ እያደረገ ይመጣል ። እግዚአብሔር ልብን ካልጠበቀ በራስ ማዘን ወደ ክፉ መንገድ ይመራልና ማራቅ ይገባናል ። ሰው ለፈጠረው አምላክ ካልሆነ ፣ ላልፈጠርነው ለእኛ ባይሆን አይደንቅም ። ምን ልስጥ እያሉ መጨነቅ ፣ ዘመደ ብዙ ጠላው ቀጭን መሆን በራስ ማዘንን ያስከትላል ።

የሚወዱትን ጽድቅ ትቶ የማይወዱትን ኃጢአት መሥራት እነዚህ ሁሉ በራስ ማዘንን ያመጣሉ ። ለራስ ማዘንና በራስ ማዘን ልዩነት አላቸው ። ለራስ ማዘን ሰው ተሳሳተ እኔ ልክ ነኝ የሚል ሲሆን በራስ ማዘን ደግሞ እኔ ተሳሳትኩኝ የሚል ስሜት ነው ። ሰው በራሱ ቀብር ላይ ተኝቶ ለራሱ እንደማልቀስ ለራስ ማዘንም እንዲሁ ነው ። ለራስ ማዘን እኔ የተጎዳሁ ነኝ ፣ የሞትሁ ነኝ ብሎ ማሰብ ነው ። በዚህ ምክንያት ሰይጣን የመግቢያ አሳብ በማግኘት ውጊያ ይጀምረናል ። የአሳብ ፍልሚያም ይመጣብናል ። ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው ለራስ በማዘን የተጎዱ ሰዎችን ነጻ ሊያወጣ ነውና ወደ እርሱ በእምነት እንቅረብ ። “እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን ፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት ፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል ።” ኢሳ. 61 ፡ 3 ።

አንተ የጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ ሆይ እንዲሁ ደስ አሰኘን !

ይቀጥላል

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ