የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ /6

3- በመጠን አለመኖር

የምንኖርበት ዓለም የመጠን ዓለም ነው ። ከመጠኑ ካለፈም ካነሰም ጉዳት የሚሰፈርበት ዓለም ነው ። ልብሱ ፣ ጫማው ፣ አልጋው ልክ አለው ። በዚህ ዓለም ምንም ስለሌላቸው የሚያለቅሱ ድሆች ያሉትን ያህል ልካቸውን ባለማወቅም የሚያነቡ ባለጠጎችም አሉ ። የሚፈልገውን የማያውቅ የሚባለው በመጠን የማይኖር ሰው ነው ። ዓለማችንን እንደ ካስማ ወጥሮ የያዛት ሥነ ምጣኔ ይመስላል ። ሥነ ምጣኔ በመጠን መኖር ፣ የዓለምን ሀብት ለሁሉም ማብቃቃት ነው ። የሰው ልጅ በመጠን መኖር ካልቻለ ትዳሩን ሊረሳ ፣ ልጆቹንም ላያሳድግ ይችላል ። ለዚህ ዓለም ኑሮ ገንዘብ ብቻውን በቂ ፍላጎት አይደለም ። ለገንዘብ ሲሮጡ ፍቅርን የረሱ አያሌ ናቸው ። ገንዘቡ ከተገኘ በኋላ ፍቅርን ቢያስሱት አይገኝም ። ገንዘብ ሐሰተኛ ወዳጅና እውነተኛ ጠላት ማትረፊያ ነው ።

በመጠን አለመኖር “አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል” የተባለውን ያመጣል ። በቃኝ ያላለ ሰው ከመጠኑ በላይ ይበላል ፣ የመጠኑንም ያጣዋል ። ያውም ከሕመም ጋር ። ከሚያስፈልገው በላይ የሚወስድ የሚያስፈልገውንም ያጣዋል ፣ ምግብ አታሳዩኝ ብሎ የወደደውን እንዲጠላ ያደርገዋል ። ልካቸውን ባለማወቅ በእስር ቤት ራሳቸውን ያገኙ ባለ ገንዘቦች ሁሉ ድህነት በጤና ብለዋል ። አሥር ልብስ ቢገዛ የሚለበሰው አንዱ ነው ። አሥር ክፍል ቤት ቢሠሩ የሚያድሩት አንዲት አልጋ ላይ ያውም ጭብጥ ብለው ነው ። ዓለም አገኘሁ ተብሎ የሚያግበሰብሱበት ሳይሆን የልክ ዓለም ነው ። በዚህች ሕይወት የሚበቃን በቃኝ ስንል ብቻ ነው ። ገንዘብ ቍጥር ነው ። ቍጥር ማለቂያ የለውምና ልንረካ አንችልም ። የበቃኝ ኑሮ መረጋጋትን ፣ እርካታን ፣ የጸሎት ሕይወትን ይሰጣል ። ከሰይጣን ወጥመድም ያስመልጣል ።

በመጠን መኖር ያልቻሉ ሰዎች አውታታ ናቸው ። ቤት አላቸው አያርፉበትም ፣ ትዳር አላቸው አይደሰቱበትም ። ልጆቻቸውን ሊያገኙ በሚገባቸው ዕድሜ ሳያገኙ ለዘላለም ተለያይተው ይቀራሉ ። ቤተሰብ የሚጸናው በአቅርቦት ብቻ ሳይሆን ፍቅርን በመስጠትም ነው ። የፍቅር ትልቅ መግለጫ ለሚወዱት ጊዜ መስጠት ነው ። አቅርቦት አንዳንድ ጊዜ ከቀይ መስቀልም ከቀይ ጨረቃም ይገኛል ። ገንዘብ ፍቅርን አይተካምና ለቤተሰብ ጊዜ መስጠት ይገባል ። በሰንበት ማረፍ ያልቻሉ ሰዎች ለእግዚአብሔር ጊዜ የላቸውም ። ጊዜ ለሰጠ እግዚአብሔር ጊዜ ማጣት ይገርማል ። የዚህ ችግር በመጠም አለመኖር ነሰው ። ስድስት ቀን ሠርቶ ያልሞላለት በሰባተኛው ቀን ሠርቶ ሊሞላለት አይችልም ። ሰው እግዚአብሔርን ሊቀድም ብዙ ዘመን ሩጫ ጀምሯል ፣ ግን አልተሳካለትም ። እግዚአብሔር ይህን ሰውነት ሲሠራው እንዲያርፍ አድርጎ ነውና በሰንበት በአምልኮተ እግዚአብሔር አለማረፍ ከገዛ ተፈጥሮ ጋርም መጣላት ነው ።

እስራኤል የምድሪቱን ሰንበት ባለማክበራቸው ለ490 ዓመታት ያህል እግዚአብሔርን አሳዘኑ ። ምድሪቱ ስታርፍ ታገግማለች ፣ እነርሱም በሰባት ዓመት ለአንድ ዓመት ያህል ያርፋሉ ። እግዚአብሔር በስድስተኛው ዓመት በረከት ሰባተኛውን ዓመት እንደሚያኖር ያውቃሉ ። እንኳን ሰው ምድርም ለካ ማረፍ አለባት ! ሁልጊዜ ማረሻ እየወጋት መኖር የላባትም ። የማገገም ዓመት ሲኖራት ብዙ ፍሬ በስምንተኛው ዓመት ትሰጣለች ። ያላረፈች መሬት አቅሟ እየደከመ ፣ ፍሬዋ እየጨነገፈ ይመጣል ። ብዙ የሚሰጡ መሪዎች ማረፍ አለባቸው ። አሊያ ባላረፈ አእምሮ የሚወስኑት ውሳኔ አገርን ይጎዳል ። እስራኤል የምድሪቱን ሰንበት ባለማክበራቸው 70 ዓመት ከምድሪቱ ተነቅለው ምድሪቱም ሰንበቷን አከበረች ። ሰውም ሰንበትን ካላከበረ ፣ እየዋተተ ሲኖር ወይ በእስር ቤት ወይ በአልጋ ላይ ያከብራል ። ይህ ሕግ ነውና ተፈጻሚነት ይኖረዋል ።

በመጠን አለመኖር ብዙ የአሳብ ውጊያ ያመጣል ። የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን መለየት አይችልም ። የገዛውን ልብስ ሳይለብሰው ሌላ ይገዛል ። እገሌ የገዛውን መኪና መግዛት አለብኝ ይላል ። የውድድር ኑሮ ውስጥ ይገባል ። ጥሎ ለማለፍ ይፈልጋል ። በዚህ ውስጥ የአሳብ ጦርነት ይጀመራል ። ደስታ ማጣት ትዳርንና ወዳጅነትን እየጎዳው ይመጣል ። ለልጆች ፍቅር መስጠት ይሳነዋል ። ሌላውን ለማስደሰት መጀመሪያ መደሰት ግድ ይላል ።

ይቀጥላል

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ