የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ /7

4- የኅብረቶች መፍረስ

የአሳብ ውጊያ ከሚያመጡ ነገሮች አንዱ የተለያዩ ወዳጅነቶች በጠላትነት ፣ አንድነቶች በመለያየት መደምደማቸው ነው ። አንድ ኅብረት እንዲጠናከር ዕድሜ ፣ ገንዘብ ፣ ምኞት ፣ ሃይማኖት ፣ እውቀት ፣ ፍርሃት ተከፍሎበታል ። ይህን ሁሉ ዋጋ ያስከፈለ ኅብረት ንቃቃት ሲገጥመው ድንጋጤ ፣ መፍረስ ሲደርስበት ኀዘንና የአሳብ ውጊያ ይመጣል ። “ሞኝ ካመረረ ፣ በግ ከበረረ” እንደሚባለው አንዳንድ ሰው ዳግም ኅብረትንና ወዳጅነትን ሊጠላ ይችላል ። ማንም ሰው ነገ የሚያፈርሰውን ኅብረት ዛሬ አይጀምርም ። ኅብረት ሲጀመር ለዘላለም ታቅዶ ነው ። ለዓመት ያሉት ለዕለት ሲያልቅ የማይደነግጥ የለም ። ደንግጦ መቅረት ግን ራስንና ሰዎችን እንዲሁም ታሪክን አለማወቅ ነው ። ራስን ስንል እኛም በሰው ላይ ተለውጠናል ። ሰዎችን ስንል ሰዎች እንደ ተልባ ስፍር ሸርታታ ናቸው ። ታሪክ ስንል እየሆነ ያለው ሲሆን የነበረ ነው ። የሚደገም እንጂ የሚጀመር ምንም ነገር የለም ። ሠርክ አዲስ ክርስቶስ ብቻ ነው ። መዋደድ እንዳለ መጣላትም አለና ልብን ማስፋት ተገቢ ነው ። ለኅብረቶች መፍረስ ምክንያት መሆን ግን አይገባም ። መለያየት የተጀመረው ገና በዓለመ መላእክት ነው ። ዓለመ መላእክት በሰይጣን ሲፈተን እግዚአብሔርና መላእክት እንዲሁም መላእክት እርስ በርሳቸው ተለያዩ ። መለያየትን ጠንስሶና ጠምቆ ለፍጥረት ያስተማረ ሰይጣን ነው ። ሰይጣን በመለያየት ግዛቱን ያሰፋል ፣ እግዚአብሔር ግን በአንድነት ይከብራል ።

የኅብረት ሁሉ መነሻ ፣ የኅብረት ሁሉ መቀደሻ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሰላምና አንድነት ነው ። ከራስም ሆነ ከሰዎች ጋር አንድ ለመሆን አቅም ያስፈልጋል ። ያንን አቅም የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ላለፈው ስርየት ፣ ለሚመጣው ንጹሕ ልብ የምናገኘው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው ። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ኅብረት አደጋ ከገጠመው ላለፈው ይቅርታን ያላገኘ አእምሮ ፣ ለሚመጣው ተስፋ የሌለው ልብ ይገዛናል ። ትላንት ላይ መዘግየት ፣ ነገ ላይ ማርፈድ ሁለቱም የሕይወት አደጋ ናቸው ። እውነተኛ ሰላምና ኅብረት ከማስታወቂያና ከድራማ ያለፈ ነው ። ኅብረት እውነት ካጣ አሰልቺ ሥራ ይሆናል ። እውነተኛ ኅብረት ግን የመተንፈስን ያህል ቀላልና አስደሳች ይሆናል ። ከትዳራችን ጋር ያለን ሰላም ፣ ልጆቻችን ላይ ባሳደርነው የማይገባ ቍጣ ከቤት መኮብለላቸው ፣ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ዓይንና ናጫ መሆናችን እነዚህ ሁሉ የአሳብ ውጊያን ያስከትላሉ ።

ትዳር እንደ አሁን የተጎዳበት ዘመን የለም ። ሰው ምሥጢሩን የሚሰማለት ፣ ገመናውን የሚያይለት መንፈሳዊ አባት ከሌለው ችግሩ ሚሊየኖችን ሊያውክ ይችላል ። “የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ” እያሉ የትዳራቸውን ገመና ለ120 ሚሊየን ሕዝብ የሚናገሩ ሰዎች መንፈሳዊ አማካሪ እንደሌላቸው ያሳያል ። ሰው የሚሰማው አንድ አባት ካላገኘ ለሚሊየኖች የአእምሮ መበከል ምክንያት ይሆናል ። ሲፋቀሩ የማናውቃቸውን ባለትዳሮች ሲጣሉ በአደባባይ እየሰማን ነው ። የወሬ ማድመቂያ ከመሆን ውጭ ቤታቸውን ሊያተርፉ አይችሉም ። መግቢያ መውጫ ሲያጡ ፣ የዘሩትን ምሥጢር መሰብሰብ ሲያቅታቸው የአሳብ ውጊያ ውስጥ ይገባሉ ። በአደባባይ መፈራረዳችን ምን ያህል የበቀል ልብ እንዳለን ፣ ትላንት ላሳለፍነው ፍቅር ዋጋ መስጠት እንደማንችል ያሳያል ። አንገት የተፈጠረው ግን ዞሮ ለማየትም ነው ይባላል ።

በአንድ የአሜሪካ የምርጫ ቅስቀሳ ሰልፍ ላይ፡- “ክርስቶስ ሆይ ከክርስቲያኖች አድነን” የሚል መፈክር ይታያል ። ክርስቲያኖች ሰው ሲታመም በድሎ ነው ፣ ሲያጣ እግዚአብሔር ቀጣው እያሉ መፍረድ ይወዳሉ ማለታቸው ነው ። በርግጥም ኃጢአተኞችን የወደደ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ነን ለማለት በጣም ያስፈራል ። ፍርድ እንጂ ለወደቁት የመነሻውን መንገድ አናሳይም ። አንድ ፀሐፊም፡- “ክርስቲያኖች በቍስለኞቻቸው ላይ ይተኩሳሉ” ብሏል ። ይህን ውሸት ነው ለማለት አቅም የለንም ። በቍስል ላይ የምንተኩስ ነን ። ብዙዎች ክርስቶስን በክርስቲያኖች እየለኩ ከኅብረት ርቀዋል ። ፍጹም ቤተ ክርስቲያን ይፈልጋሉ ። ቢያገኙ እንኳ እነርሱ መግባት አይችሉም ፣ ምክንያቱም ፍጹም አይደሉምና ። በአገራችን የአጀማመር ጀግንነታችን ብዙ ነው ። የጀመርንበት ቦታ ቢታይ ኖሮ ሁላችን ዋጋ እናገኝ ነበር ። እግዚአብሔር ግን የፈጸምንበትን ቦታ ያያል ። ብዙ ሰዎች ፣ ብዙ እቅዶች ፣ ብዙ አገልጋዮች መንገድ ቀርተዋል ። የድንጋይ ብርድ ልብስ ለብሰው ያሉ ሙታን ስለበዙ ቀና ያለውን ሰው “ረበሽከን” በማለት በብረት ዘነዘና አናቱን ብለው ያፈርሱታል ። ቀና ብል የብረት ዘንግ ይጠብቀኛል ብሎ ብዙ ሰው ዝቅ ብሏል ። የአሳብ ድንክ ለመሆን ፈቅዷል ።

ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ኅብረት መላላት ፣ የትዳርና የቤተ ክርስቲያን አንድነት መፈታት ፣ ወዳጅነት እንደ ፋሽን መለዋወጡ ፣ ገመናችን አደባባይ መውጣቱ ይህ ሁሉ አሳብ ውጊያን ያስከትላል ።

ይቀጥላል

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ