የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአበው ተስፋ ተወለደ

አበው መንገዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር አደረጉ ። በጽድቃቸው እንኳን ሌላውን ራሳቸውንም ማዳን ባልቻሉ ጊዜ የክርስቶስን መወለድ ናፈቁ ። አዳም ገነትን አጥቶ ተስፋን ይዞ ወጣ ። ከነበረችው ገነት ይልቅ ፣ የገነት ጌታ የእርሱ ልጅ እንደሚሆን በሰማ ጊዜ ልቡ በደስታ ዘለለ ። ውድቀቱ ያመጣው መዳን ቢሆን ኖሮ እንኳን ወደቅሁ ባለ ነበር ፣ ለወደቀ ሰው የሚሆን ፍቅር ያለው አምላክ ግን አዳምን ከበደሉ በላይ ካሣ ሰጠው ። ተስፋ የሚነገረው/የሚሰጠው በእግዚአብሔር ደግነት ፣ የሚፈጸመውም በእግዚአብሔር ታማኝነት ነው ። አበውም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚቀባበሉት ዕንቈ ነበራቸው ፤ እርሱም ክርስቶስ ይወለዳል የሚል ነው ። የከፋውና ሁሉ የተነባበረበት ሕፃን “ቆይ አባቴ ይምጣ” እያለ እያለቀሰ ይስቃል ። አባቱ እንባውን ያብስለታል ፣ ጠላቶቹን ያሸንፍለታል ። አበውም የክርስቶስን መወለድ ባሰቡ ጊዜ እያለቀሱ ሳቁ ።

ጨርሶ እንዳይጨልም ለማታው ክፍለ ጊዜ ጨረቃና ከዋክብትን ያስቀመጠ እግዚአብሔር ፣ የሰው ልጅም በኃጢአት ፣ በመቃብርና በሲኦል ተጨንቆ እንዳይኖር ልደተ ክርስቶስን ተስፋ አድርጎ ሰጠ ። አንድ ወንድ ልጅ ይወለዳል እየተባለ ለዘመናት ተስፋ ተደረገ ። ያ ልጅ ከተወለደ በኋላም ዳግም ይመጣል እየተባለ ይሰበካል ። ከገነት እስከ ምጽአት ፣ ከውድቀት እስከ ፍርድ ቀን የክርስቶስ መምጣት የሰው ልጆች ተስፋ ነው ። ይህች ዓለም ያለ ክርስቶስ አድራ አታውቅም ። የመጣውና የሚመጣ ጌታ አለን ። በመጀመሪያ ምጽአቱ አዳነን ፣ በዳግም ምጽአቱ ይፈርድልናል ። በመጀመሪያ ምጽአቱ ከሲኦል ወደ ገነት አፈለሰን ፣ በዳግም ምጽአቱ ከገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ያፈልሰናል ። ከክብር ወደ ክብር እንሻገራለን ። በመጀመሪያው ምጽአቱ አጋንንት አፈሩ ፣ በዳግም ምጽአቱ የናቀን ዓለም ያፍራል ። በመጀመሪያው ምጽአቱ ሞት ተገደበ ፣ በዳግም ምጽአቱ መከራ ይገደባል ።

አብርሃም አገሩና ተስፋው ሩቅ ነበረ ። ክርስቶስ ወደሚወለድበት ምድር ተጠራ ። ዕድሜው እየመሸ ቢሆንም ሠርኩን ማለዳ የሚያደርገው ፣ በሞት ላይ ልደት የሚያውጀው እግዚአብሔር በመልካም አሰበው ። ለሞት ሲሰናዳ ለሕይወት ተጠራ ። ሌጣውን ሊሞት መሆኑን አምኖ ከተስፋ ጋር ሊቀበር ሲል እግዚአብሔር የብዙዎች አባት አደረገው ። የብዙዎች አባት መሆኑን እርሱ አላየም ። አብርሃም ጥቂት ልጆችን ብቻ በዓይኑ አየ ። እግዚአብሔር ባየለት ነገር ተደሰተ ። ተስፋ ማለት እግዚአብሔር ባየልን “ነገ” መደሰት ማለት ነው ። አብርሃም የተዘዋወረበትና ድንኳኑን የተከለበት ምድር በኋለኛው ዘመን ክርስቶስ የሚወለድበትና የማዳን ግብሩን የሚፈጽምበት ነው ። አብርሃም ወደ ቤተልሔም በሄደ ጊዜ “እኔ በድንኳን ኖርሁ ፣ አንተ በበረት ተወለድህ ፣ ቤት አልባ ሆንህ” ብሎ ክርስቶስን በሩቅ ተሳለመው ። ወደ ሞሪያ ተራራ ፣ ወደ ቀራንዮ መጥቶ ልጁን ይስሐቅን ሊሠዋ ባለ ጊዜ ፣ በይስሐቅ ሞት የሚድን ዓለም የለምና የክርስቶስን ቤዛነት ናፈቀ ። ከመልከ ጼዴቅ ኅብስትና ጽዋውን ሲቀበል ፣ ዛሬ በሳሌም የተቀበልሁት ኅብስትና ወይን ፣ ነገ በኢየሩሳሌም በታላቁ ካህን በክርስቶስ የሚሰጠው ሥጋና ደሙ ነው ብሎ ተደነቀ ። አብርሃም ያመነውና የኖረው የዛሬው አማኝ የሚያምነውና የሚኖረውን እውነት ነው ። እምነት በዘመናት መካከል አንድ መልክ ለአማኞች በመስጠት የሚታወቅ ነው ።

ይስሐቅን ከሞት ያዳነው ፣ በዱር የተገኘው ፣ ያለ ቦታው የታየው ፣ ኃይል እያለው እንደሌለው የሆነው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። አብርሃም የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለ ፣ ዮሐንስ መጥምቅም “የእግዚአብሔር በግ እነሆ!” አለ ። ያዕቆብ በኤፍራታ ራሔልን ቀበረ ። ራሔል በመውለድ ሞተች ፣ ሕያው ልጅን ሰጥታ እርስዋ አንቀላፋች ። ራሔል በያዕቆብ መወደድዋ ከሞት አላዳናትም ። ወድዶ ከሞት የሚያድን ክርስቶስ ብቻ ነው ። መዝሙረኛው “ወዶኛልና አዳነኝ” ያለው ለዚህ ነው ። የቤተ ልሔም የቀድሞ ስምዋ ኤፍራታ ነው ። ተስፋ ባደረጉት አባቶች ርስት ክርስቶስ ተወለደ ። የይሁዳ አንበሳ የይሁዳ ግዛት በሆነችው ቤተ ልሔም ተወለደ ። የዳዊት ቤትን አልከዳም ብሎ የቀረው ፣ እናቱ በቤተ ልሔም የሞተችበት ፣ የራሔል ልጅ ብንያም ነው ። በታማኙ በብንያም ርስት ክርስቶስ ተወለደ ። ዛሬም እርሱ በሚጠብቁት ርስት በፍቅር ፣ በሰላም ይወለዳል ። ታማኞችን መለኮት አድራሻ ያደርጋቸዋል ። ብዙዎች የከዱትን እኔ አልከዳውም የሚሉ ፣ የቀድሞ ወዳጅነትን የሚያስቡ ዛሬም የክርስቶስ ቤተ ልሔም ናቸው ። እርሱ የሚጸየፈው በረትን ሳይሆን ክዳትን ነው ።

አብርሃም ፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ክርስቶስ ከእኔ ወገን ይወለዳል እያሉ ቤታቸውን ንጹሕ አደረጉ ። መጻተኝነታቸውን ረሱት ። ወደውም ለክርስቶስ ድሀ ሆኑ ። በዓለም መጠላታቸውን ናቁት ። ነገሥታት አብርሃምን ተጋጠሙት ። አንድም ቀን በቤተ መንግሥት አልተጋበዘም ። ሁለት ጊዜ ግን ሚስቱን ነጥቀው ፈርዖንና አቤሜሌክ አስደነገጡት ። አማኒ በቤተ መንግሥት ለግብዣ ሳይሆን ያመነውን እንዲጥል ይጠራል ። እግዚአብሔር ቃሉን አክባሪ ነውና ደግሞም በአብርሃም ላይ የተጠራውን ስሙን አክብሯልና ፣ አሁንም እርሱ የሚወጣበትን ዘር ይከላከላልና ሣራን ከነገሥታት እጅ ፈልቅቆ አወጣት ። ክርስቶስ ከነገሥታት ሳይሆን ከመጻተኞች ቤት መወለድን መረጠ ። በአብርሃም ድንኳን ሥላሴ አደሩ ። ወደ ድንግል ማርያም ሥላሴ መጡ ። አብ አጸናት ፣ ወልድ ልጅ ሆናት ። መንፈስ ቅዱስ አከበራት ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ