የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአብርሃም ዘር

“አብርሃም ይስሐቅን ወለደ” /ማቴ. 1፡2/ ።
ቅዱስ ማቴዎስ የዘር ሐረግ ቆጠራውን ከአብርሃም እስከ ክርስቶስ ያደርገዋል። ዓላማው ክርስቶስ የአብርሃም ዘር ፣ የዳዊት ልጅ መሆኑን አውቀው አይሁድ እንዲቀበሉት ለማገዝ ነው ። ቅዱስ ሉቃስ ግን ቆጠራውን ከክርስቶስ እስከ አዳም ያደርገዋል /ሉቃ. 3፡23-38/ ። ዓላማው ክርስቶስ የዮሴፍ ልጅ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለመግለጥ ነው ። ቅዱስ ማቴዎስ ከአብርሃም መጀመሩ ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑን ለመግለጥ ነው ። በማቴዎስ ወንጌል ጌታችን ራሱን የሰው ልጅ በማለት 28 ጊዜ ያህል ጠርቷል ። ቅዱስ ሉቃስ ክርስቶስ በምድር አባት የሌለው ፣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ይገልጣል ። ክርስቶስ በአንድ አካል በአንድ ባሕርይ ፍጹም ሰው ፣ ፍጹም አምላክ መሆኑን ወንጌሉ ያትታል ። ክርስቶስ አንድ አካል ፣ አንድ ባሕርይ መሆኑን ያልተቀበሉ ሁለት አካልና ሁለት ባሕርይን ያስተማሩ እነ ንስጥሮስን ፤ አንድ አካል ሁለት ባሕርይ ያሉትን እነ ልዮንን ያስተምራል ። እንደ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ነው ያሉትን እንደ አውጣኪ ሰውነቱን ምትሐት ያደረጉትን ይመክራል ። የክርስቶስ የዘር ሐረግ ቆጠራ በማቴዎስና በሉቃስ ወንጌል የተጠቀሰውን ማጥናት ይገባል ።
ቅዱስ ማቴዎስ ከአብርሃም ጀመረ ። ከአብርሃም በፊት በዚህ ሐረግ ውስጥ የነበሩ ቢኖሩም ከአብርሃም መጀመሩ ለምንድነው ? ማለታችን አይቀርም ። አብርሃም ተጠርቶ ሲወጣ ክርስቶስ የሚወለድበት የዘር ሐረግ ጎዳናው ጥርት ብሎ ታየ ። አብርሃም በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 12 ላይ እስኪጠራ ድረስ ብዙ የትውልዶች ስም ተጠቅሷል ። አብርሃም ከተጠራ በኋላ ግን እስከ ምዕራፍ ሃምሳ ድረስ ሦስት ሰዎች በዋናነት ተጠቅሰዋል ። እነርሱም አብርሃም ፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ናቸው ። አብርሃም አገሩን ለቆ በእግዚአብሔር አመነ ። አዳም ግን ገነት እያለችው እግዚአብሔርን ካደ ። አብርሃም ያለውን እንደሌለ ቆጠረ ፣ አዳም ግን ካለው በላይ ሌላ ፈለገ ። ስለዚህ የትውልድ ሐረግ ቆጠራው ከአብርሃም ጀመረ ። ከአብርሃም በፊት ወደ ኋላ ሲቆጠር እስከ አዳም 3ሺህ 5 መቶ ዓመታት ናቸው ። ከአዳም እስከ ክርስቶስ ግን 2 ሺህ ዓመታት ናቸው ። የሚበዛው ዓመት ያኛው ቢሆንም አብርሃም እግዚአብሔርን ካመነበት ጊዜ አንሥቶ መቊጠር ጀመረ ። ይህ ዘመንም የተስፋ ዘመን ነው ።
አብርሃም ይስሐቅን ወለደ የሚለው ቃል አንድ መስመር የማይሞላ አንድ አንቀጽ የማያህል ነው ። አብርሃም ግን ይስሐቅን ያገኘው በመቶ ዓመቱ ነው ። ብዙ ነገር ሲነገር ሲወራ ቀላል ነው ። ሲገኝም ቀላል ነው ። ሲጠብቁትና ሲያልፉበት ግን ከባድ ነው ። ልመናችን ብዙ ፣ ምስጋናችን ጥቂት የሆነው ለዚህ ነው ። የተቀበልነውን ነገር በአንድ ቃል ብንገልጠውም የዘመናት ናፍቆታችን የነበረ ነው ። እንደ ቀላል ልናየው አይገባም ።
አብርሃም ይስሐቅን ለመውለድ ተስፋ ተቀብሎ ሃያ አምስት ዓመታት መጠበቅ ነበረበት ። በተስፋውና በፍጻሜው መካከል ብዙ ፈተና ቢኖርም ተስፋን የሰጠው የታመነ ነው ። በተስፋውና በፍጻሜው መካከል ያለው ትልቁ እንቅፋት አቋራጭ መንገድ ነው ። አብርሃም እግዚአብሔርን መጠበቅ አቅቶት የሄደበት አቋሯጭ መንገድ እስማኤልን አስገኘ ። እስከ ዛሬ ድረስ የይስሐቅ ዘርና የእስማኤል ዘር ይዋጋሉ ። የአቋራጭ መንገድ የአራት ሺህ ዓመታት ጦርነትን ወለደ ። ሰው በሩጫው እግዚአብሔርን አይቀድመውም ። ሃያ አምስት ዓመት መጠበቅ አለመቻል የአራት ሺህ ዓመታት ጦርነት ተወለደ ። ተስፋ የትዕግሥትን ዋጋ ቢያስከፍልም ፍጻሜው ሰላምና ደስታ ነው ። እባካችሁ ታገሡ ፣ ተስፋን የሰጠው ታማኝ ነው ።
ወዳጆቼ በክብር ያኑራችሁ !
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ