አእምሮ የክብር ሚዛን ነው። በቁመናው በአለባበሱ የተከበረ ሰው በአእምሮው መራቆት ሊንቁት ይችላሉ። ለላዩ ሲጨነቅ ለውስጡ አላሰበምና። ቁመናው ፣ አካሉ የማይማርክ ሆኖ አእምሮው የበለፀገ ሰው ግን በግድ ያሸንፈናል። ቆንጆዎችና ቁመተ መለሎዎች ለዓለም ያደረጉት አስተዋጽዖ መለኪያን ማዛባት ብቻ ነው። ስንቱ መልክና ቁመናቸውን በማየት ብቻ ገብቶ ሲቆስል ይኖራል። ቆንጆ ሳማ ነው ፣ ሲለበልብ ይኖራል። መጽሐፍ ቅዱስ ውበትን ለማድነቅ የተጻፈ ባይሆንም የሳጥናኤልን ውበት ግን ያደንቃል። ሳጥናኤል ወደ ሰይጣንነት የወደቀው ውበት መሰናክል ሆኖበት ነው።
እግዚኣብሔር መልከ ቀናውን ኤልያብን ሳይሆን ግብረ ቀናውን ነቢዩ ዳዊትን መርጧል። መልክ ያለፉበት፣ ያልደከሙበት ነው። ሰው የሚደነቀው ባገኘው ሎተሪ ሳይሆን በለፋበት ጥሪት ወይም ሀብት ነው። ይህ ዘመን ከቅንነት ይልቅ ለቁንጅና ዋጋ በመስጠቱ እየወረደ ይገኛል። ውጫዊ መልክ ዋጋው እያነሰ ይመጣል፣ የውስጥ መልክ ግን እየከበረ ይመጣል። ውጫዊ መልክ የቀትር ፀሐይ ነው፣ ብርሃኑ እየቀነስ ይመጣል፣ ውስጣዊ መልክ ግን የጠዋት ፀሐይ ነው፣ ብርሃኑ እየደመቀ ይመጣል።
አእምሮ እንደ አካል ነው። አካል ምግብ፣ እንቅስቃሴና ዕረፍት ይፈልጋል። አእምሮም የእውቀት ምግብ ይፈልጋል፣ በመማርና በማስተማርም መንቀሳቀስ አለበት። ዕረፍትና የማገገሚያ ጊዜም ይፈልጋል። የሁሉንም የአካል ክፍሎች ዕዳ የእኔ ብሎ የተሸከመ አእምሮ ነው። የሚያስነቅፈው ብዙ መተኛት እንጂ በቂ እንቅልፍ ለአእምሮ ጤንነት አስፈላጊ ነው። የዕረፍት ጊዜ ግድ ነው፣ ሰንበት የተሠራው ተፈጥሮአችንን አገናዝቦ ነው። ስፖርት ፣ ተፈጥሮአዊ ነገሮችን ማየት፣ ስልኮችን መዝጋት አእምሮ ንቁ እንዲሆን ያደርጋል። አእምሮ ጥሬ ትርጉሙ እውቀት ማለት ነው። የሰው ልጅ የክብሩ መገለጫ ነው። ስንጸልይ አእምሮዬን ገንዘብ አድርግልኝ ማለት ይገባናል።
አእምሮ ጤናማ ዕድገትና ዘመን እንዲያገኝ የሚከተሉት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡ –
እውቀት ያስፈልገዋል። መኪና ዕድሜ የሚኖረው ሲንቀሳቀስ ነው፣ የተሠራው ለዚያ ነውና። አእምሮ የማወቂያ መሳሪያ ፣ ከእውቀት ጋር የተፈጠረ ነው። ምግቡ እውቀት ነውና ልናቀርብለት ይገባል። አሊያ አእምሮ እየዛገ ይመጣል። የእውቀት መንገዶችም መማር፣ ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ መኖር ፣ በችግር ውስጥ ማለፍ ነው። የማያነብና ተመሳሳይ የምቾት ኑሮ የሚኖር ሰው አእምሮው አያድግም። አእምሮ ካለበት ከወረደ ገዳይ ይሆናል፤ አእምሮ ባለበት ከቆመ ምክንያተኝነትን ያጣል፤ አእምሮ እየበሰለ ከመጣ ሰዎች የእርሱ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ይረዳል፣ አንድ ክቡር ተግባር ትቶ ለመሔድ ይነሣል። የመርሳት በሽታን የምንከላከለው ፣ ከአሮጌውና ከአዲስ ትውልድ ጋር የምንግባባው በማንበብ ነው። በተከፈተ አፍ ራስ ይታያል እንዲሉ በተናገርን ቁጥር ክብር እንዲኖርን ማወቅ አለብን። ኑሮ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው :: ደጎች የሰማይን ውበት የምንማርባቸው ሲሆኑ ክፉዎች ደግሞ የዓለምን ምንነት ያሳውቁናል።
ንጽሕና የአእምሮ መጠበቂያ ነው። ይቅርታ ማድረግ የአእምሮ እጥበት ማድረግ ነው። የሌላውን ንብረትና ላብ አለመብላት ፣ የሚያጸጽት ነገር አለማድረግ አእምሮን ንጹሕ ይደርጋል። ንስሐና ይቅርታ አእምሮን የመቀደስ አቅም አላቸው። የበደልናቸውን ሰዎች ይቅርታቸውን ማግኘት አለብን። አሊያ በታሰረ ሕሊና የትም መድረስ አንችልም።
አእምሮ የሞት ዘመን አለው። አንዳንድ ሰዎች እንዴት አይሰማቸውም? እንላለን። አእምሮ ታሞ ታሞ ይሞታል። ያን ጊዜ ጸጸትም ይቆማል። የተነባበረ በደል ፣ በግፍ ላይ ግፍ መሥራት አእምሮን ለሞት ያበቃል። መጨረሻው እንደ ፈርዖን መስጠም ይሆናል።
በጎ ሥራ መሥራት ፣ ከሰዎች ጋር መወያየት፣ አሳብ መለዋወጥ፣ ማሰላሰል ፣ ጨዋታ አእምሮን ሕያው ያደርጋል። የአንድ ደቂቃ ንግግር መስማት አዋቂ አያደርግም። አጭር ጽሑፍ፣ አጭር ቪዲዮ መስማት እንጀራ መብላት ሳይሆን በከረሜላ የምግብ ፍላጎትን መዝጋት ነው። ለዓለም ውጤታማ ነገር ያመጡ ኮሳሳ የሚባሉ ሰዎችና ገለል ብለው ወይም የከተማ መናኝ ሆነው የተመራመሩ ሰዎች ናቸው። ቀለል ያለ ነገር መምረጥ አዋቂ አያደርግም።
በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ አእምሮን ከፍ ያደርጋል። መጸለይ አቅልን ከመሳት ይጠብቃል። ምጽዋት ደስታን ያመጣል። ሱባዔ መግባት ለታላቅ ተግባር ያዘጋጃል። ፍቅር መስጠት ነጻነትን ያጎናጽፋል። የታመመና የታሰረን መጠየቅ ልብን ሙሉ ያደርጋል። ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ውጤትን ያመጣል። የምንፈልገውን ማወቅ ከብስጭት ያወጣል።
የአእምሮን ሕያውነት እንጠብቅ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም.