የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአእምሮ ከንቱነት

“እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ።” ኤፌ. 4 ፡ 17 ።

አእምሮ እውቀት ፣ የማወቂያ መሣሪያ ፣ የአመክንዮ/የምክንያታዊነት/ ሞተር ፣ የአሳብ ሙግት ፣ የጥበብ አውድማ ነው ። ሰው አዲስ ነገር አወቅሁ የሚለው እርሱ ስለ ደረሰበት እንጂ ዓለም ሲፈጠር ፣ ዘመን ሲቆጠር የነበረ ነው ። አእምሮ ተመጋቢ በመሆኑ እውቀት ካላገኘ ይዝጋል ። ለመጓጓዣ የተሠራ መኪና ህልውናውን የሚጠብቀው በመጓዝ እንደሆነ አእምሮም ራሱን ከዝገት የሚጠብቀው በማወቅ ነው ። አእምሮ ደመ ነፍሳዊ እውቀት ያለው ቢሆንም በየዕለቱ በአፍም በመጽሐፍም የሚነገረውን ይዞ ማዳበር አለበት ። አእምሮ ምክንያታዊ በመሆን ነገርን ከሥሩ ፣ ውኃን ከጥሩ ይቀዳል ። ሕሊናዊ በመሆንም በምሕረት ያልፋል ፣ ጥፋተኛውን ከጥፋቱ ለይቶ ያየዋል ። አእምሮ የፍጭት ሜዳ ነው ። አሳብና አሳብ መፋጨታቸው ብረትና ብረት መሳሳላቸው ነው ። ሁለት ደነዝ ቢላዋ ሲሳሳል ሁለት ስል ቢላዎች ይወጣቸዋል ። አእምሮ አሳብን የሚፈራ አይደለም ። በመምህርም በመጽሐፍም መሠረት ከያዘ ለመስማት የሚፈራ አይደለም ። አአምሮ እንደ ምላስ ማጣጣሚያ የሚኖረው መርዙን ከምግቡ የሚለየው መሠረት ሲኖረው ነው ። መሠረቱን የመሠረተ ሰው የሚያገኘውን አዲስ አሳብ በዚያ ላይ ይክበዋል ። መሠረት ያልመሠረተ ግን የሚሰማው ሁሉ ያፈርሰዋል ፣ የዕለት ቤት ፣ የበረሃ ዳስ ፣ የዘላን ድንኳን አድርጎ ይሠራዋል ። በየዕለቱ አዲስ ሃይማኖትና ፍልስፍና ይዘው ሲሰክሩና ሲያሰክሩ የሚውሉ ሰዎች መሠረት የሌላቸው ሰዎች ናቸው ። ባነበቡት ሁሉ እየተወሰዱ በየሳምነቱ አዳዲስ ፍልስፍና የሚያራምዱ ዘግይተው ማንበብ የጀመሩ ፣ በመምህር ተወቅረው ያልተገነቡ ናቸው ። እውቀት ዲሲፕሊን የሚኖረው በመምህር ነው ። እነዚህ ሰዎች “ደንቆሮ የሰማ ቀን ያብዳል” እንዲሉ ሁለት ሺህ ዓመት የሞላውን ኑፋቄ አዲስ መገለጥ ብለው ይይዛሉ ።

አእምሮ ጥበብን ይመገባል ፣ በጥበብ ይወዛል ፣ በጥበብ ይወረዛል ፣ በጥበብ ይረጥባል ፣ በጥበብ ያረጥባል ። ልብ አድርጉ ጥበብ ማለት ፀጉርን ማንጨብረር አይደለም ። ይህ ጥበብም የጥበብ መገለጫም አይደለም ። ስንፍና ነው ። ጥበብ ክርስቶስ ነውና ክርስቶስ የሌለበት ጥበብ ከንቱ ነው ። ስለ ዓለም ብናውቅ የሠራውን ካላወቅን ምንም አይጠቅመንም ። ባለቤት ስለሌለው ቤት እንደ ማጥናት ነው ። የመጨረሻ ጥበብ እግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔርን ተምሮ የምስክር ወረቀት የሚቀበል ማንም የለም ። ታውቆ አይፈጸምምና ሰው ሁልጊዜ ተማሪ ነው ። በአእምሮ አውድማ ላይ ጥበብ ይወቃል ። ገለባው ከስንዴው ይለያል ። የሚለየውም ነፋስ ነው ። ነፋስ መንፈስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ በአእምሮ ሜዳ ላይ ጥበብን ከገለባ ይለያታል ። አእምሮ በአንደበት የሚነገሩ ነገሮች የሚጣሩበት ነው ። አንደበት በምድር ላይ ካሉ ታላላቅ ኃይሎች ቀዳሚ ነው ። ጦርነት የሚቀሰቀሰውም የሚቆመውም በአንደበት ነው ። እሳትን እፍ ብለን የምናቀጣጥለው እፍ ብለን የምናጠፋው በአንደበት ነው ። “እፍ ያነዳል ፣ እፍ ያጠፋል” እንዲሉ ። አእምሮ በእውቀት ያጣራል ፣ በጥበብ ያስውባል ፣ በማስተዋል ይተምናል ። ያልተጣራ እውቀት ፣ ያልተዋበ ጥበብ ፣ ያልተተመነ ማስተዋል አይባልም ። መረጃና እውቀት ልዩነት አለው ። በዛሬው ምግባችን ላይ ብርቱካን ላይበላ ይችላል ። በእንጀራ ግን መዋል ይቻላል ። እንጀራ መደበኛ ምግባችን ነው ። መረጃ ተጨማሪ የዕለት እውቀት ነው ። ጋዜጣ አንድ ቀን ካለፈው ያደረ የወሬ ቋንጣ ነው ። አእምሮን ሕያው የሚያደርግ እግዚአብሔርን ማሰብ ፣ ጸሎት ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ፣ በጎ እውቀትን መናገር ፣ ማሰላሰል ፣ ያለ ማቋረጥ መማር ተጠቃሽ ነው ።

አሕዛብ በአእምሮ ከንቱነት ይመላለሳሉ ። ክርስቲያኖችም በአእምሮ ከንቱነት የሚመላለሱበት ጊዜ ብዙ ነው ። ሐዋርያው የአእምሮ ከንቱነት ምን እንደሆነ ቀጥሎ ይናገራል፡- “እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ ፤ ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ ።” ኤፌ. 4 ፡ 19-19 ። የአእምሮ ከንቱነት ማወቅ አለመፈለግ ነው ። አለማወቅ በሰላም ለመኖር ፣ አለማወቅ ሃይማኖትን ለመጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ማሰብ የአሕዛብ አመለካከት ነው ። አሕዛብ ያመኑትን በሥጋዊ ኃይል ማስጠበቅ ይፈልጋሉ እንጂ የአሳብን የበላይነት አያምኑም ። በዱላ የሚያስብ በአእምሮ ማሰብ አይችልም ። ሁለቱም አንድ ጊዜ አይሠሩም ። ዱላና አእምሮ ። ዱላ ሲነሣ አእምሮ የዓመት ፈቃዱን ሞልቶ ይሄዳል ። አእምሮ ሲነሣ ዱላን ይጥላል ፣ ያስጥላል ። አለማወቅ ጠንቅ ነው ። አስቸጋሪ በሽታዎች አሉ ይባላል ፣ ከባዱ ጠንቅ ግን አለማወቅ ነው ። ከንቱ አእምሮ ሁለተኛ መገለጫ አለው ። የልብ ደንዳናነት ። ደንዳና የተለያየ ነው ። አንገተ ደንዳና ሲባል ለማቀፍ የማይመች ፣ አንገቱ የወፈረ ፣ ሲወዱት የሚጨንቀው ፣ ሲያቀርቡት የሚርቅ ፣ ወፈፌነት የተጠናወተው ፣ የፍቅርና የጥላቻን ልዩነት የማያውቅ ድንዙዝ ማለት ነው ። ልበ ደንዳና ማለት ደግሞ ፍቅር ወደ ውስጡ እንዳይገባ የሚከላከል ፣ ውለታ ቢስና ይገባኛል ባይ ፣ ቀምቶ ራጭ ፣ ይሉኝታ ቢስ ነው ። የአእምሮ ከንቱነት ልበ ደንዳናነት ነው ። ይህ በሽታ ክርስቲያንንም ሊያጠቃ ይችላል ።

ከንቱ አእምሮ ሦስተኛው ጨለምተኛ ልብ ነው ። በውስጡ ምንም ተስፋ የማይታየው ፣ ሁሉን ነገር በዜሮ የሚያባዛ ፣ ለኖረበት ዘመን ዋጋ የማይሰጥ ፣ የኖሩ ነገሮችን የማያከብር ፣ በአጭር ቃል አጥፍቶ ጠፊ ነው ። ጨለማ ልብ ያለው ሰው እግዚአብሔርን ሳይሆን ጊዜን በማየት ብቻ ሕይወት እንዲህ ነው ብሎ ብይን የሚሰጥ ነው ። ከንቱ አአምሮ አሳልፎ የሚሰጠው ከሕይወት ለመራቅ ነው ። ከሕይወት የራቀ ሰው ከፀሐይ እንደ ራቀ ሰው ይገረጣል ። በሰሜን ንፍቀ ክበብ የሚኖሩ መልካቸው ሊጥ ፣ በምድር ወገብ የሚኖሩ መልካቸው አራራ የሚመስለው ከፀሐይ ጋር ባላቸው ርቀትና ቅርበት ነው ። ነጭና ጥቁር ማለት የመመጻደቂያ ቀለም ሳይሆን ፀሐይን በጣም መቅረብና መራቅ የሚያመጣው ጣጣ ነው ። ፀሐዩ መንግሥት ይባላል ። ንጉሥም ሲቀርቡት ያሳርራል ፣ ሲርቁት ይበርዳል ። በመካከለኛው ስፍራ መቀመጥ ይገባል ።

ከንቱ አእምሮ በመመኘት የተያዘ ነው ። መመኘትም ሴሰኝነትን ወይም ዝሙትን ይወልዳል ። በምስሉ ፣ በፊልሙ ፣ በጨዋታው ሁሉ ከዝሙት ወሬ የማያርፉ አሕዛብ ናቸው ። የአሕዛብነት ምንጩ ግን እግዚአብሔርን ለማወቅ አለመውደድ ነው ። አሕዛብነት ዘር አይደለም ፣ ምርጫ ነው ። የአእምሮ ከንቱነት ምንም አለማወቅ አይደለም ። ስለ ተፈጥሮ ስለ ዘመን ሠራሽ ነገር የሚመራመሩ ፣ ኑሮን እያቀለሉ ሕይወትን እያከበዱ ያሉ ብዙ አዋቂዎች አሉ ። የአእምሮ ከንቱነት የሚድነው እግዚአብሔርን በማወቅ ነው ።

አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ ፣ ዘወትር አንተን እናይህ ዘንድ የልቡናችንን ዓይን አብራልን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 13 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ