የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአጥቢያ ኮከብ

 

ወዳጄ ሆይ !

ቤትህ ሥርዓት ከሌለው ደስታ እየራቀህ ይመጣል  ። ቢሮህ ሥርዓት ከሌለው ሥራህ ይበላሻል ። አገልግሎትህ ሥርዓት ከሌለው ሰሚ ያጣል ። ኑሮህ ሥርዓት ከሌለው ጎዳና ላይ ይጥልሃል ። አገርህ ሥርዓት ከሌለው ጻድቅ ይጨነቅባታል ። ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከሌላት ውበትዋ ይጠፋል ። ፍቅርህ ሥርዓት ከሌለው የምትወደው ይጠላሃል ። ጠብህ ሥርዓት ከሌለው ወንጀለኛ ያደርግሃል ። ቸርነትህ ሥርዓት ከሌለው መበተን ይሆናል ። አለባበስህ ሥርዓት ከሌለው ያራቁትሃል ። አቀራረብህ ሥርዓት ከሌለው ሁሉ ይደፍርሃል ። ቅጣትህ ሥርዓት ከሌለው ልጅ ገዳይ ያደርግሃል ። አኗኗርህ ሥርዓት ከሌለው ቶሎ ይጥልሃል ። 

ወዳጄ ሆይ !

የፈጸሙት ተልእኮ ልደት ያዩበት ምጥ ነው ። ያስረከቡት አደራ የነፍስ አርነት ነው ። በሰዓት መድረስ ትልቅ ውለታ ነው ። በቁም የረዱትን ስቀው ይቀብሩታል ። አግኝቶ ያጣው ቶሎ ቶሎ ይከፋዋልና ታገሠው ። አጥቶ ያገኘ ምድር ይጠበዋልና ምክረው ። ከፍታህ ዝቅተኞችን በመርገጥ ፣ ህልውናህ በሌሎች ሬሳ ላይ አይሁን ። የፍቅር ሰው ለመባል ሁሉም ትክክል ነው አትበል ። ግልጽ ጥላቻ የፍቅር ያህል ነው ። ግልጽ ንግግር ሰሚውን ያከበረ ነው ። እጅግ ግልጽነትም የሚያስገምት ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

በስሜትህ ላይ ያገኘኸው ድል በጦር ሜዳ ከምታገኘው ድል በላይ ነው ። ምስክርነት የሰይጣንን ሥራ ማፍረስ ነው ። መልካም ቃል የቀን ጉልበት ነው ። ፀሐይ ሳትጠልቅ ሥራህን ፣ ጨረቃ ሳትሰወር ተግባርህን ፣ ከዋክብት ሳይጠፉ ድርሻህን ፈጽም ። ፀሐይ የተባለ ደግ አባት ፣ ጨረቃ የተባለች እናት ፣ ከዋክብት የተባሉ ወንድምና እኅቶች ናቸው ። ፀሐይ አንዲት ናት ፣ አባትም አንድ ነው ፣ ጨረቃም አንዲት ናት ፣ እናትም አንድ ናት ። ከዋክብት ብዙ ናቸው ፣ እኅትና ወንድሞችም ብዙ ናቸው ። 

ወዳጄ ሆይ !

ሳይማር ማስተዋል ያለው ፣ ማስተዋል ከሌለው ምሁር የተሻለ ነው ። ማስተዋል ትምህርትን ይጠቀልላል ፣ ትምህርት ግን ማስተዋልን ላያመጣ ይችላል ። ጸሎት ትተህ ወሬን ስትመርጥ የሚመጣውን መከራ ለመሸከም ራስህን አዘጋጅ ። ክፉ ቀን እየጠበቅህ የወደቀ ሰውን በቃላት አትጉዳ ። በዚህ ዓለም አንድ ቀንም ለመከራ ረጅም ነውና ጨርሼዋለሁ ብለህ አትመካ ። መልካም ተግባር የሚሠራ ስታገኝ ተቀላቀለው ። ስሜ አልተጠራም ብለህ በጎ ሥራህን አታቁም ። ተራሮችን ካላየህ ኮረብቶች ተራራ ይመስሉሃል ። በሜዳ ያደገ ስለ ጉብታ የሚያወራው እንደ ዳሸን ተራራ ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

በአንድ ጊዜ ጳጳስ ሁን ቢሉህ ከአናጕንስጢስነት/ከአንባቢ ከተላላኪ/ ጀምረህ መሠረት እየያዝህ እደግ ። ትልቅ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ስትጓዝ አትኑር ። ምድር ጊዜያዊ ቤት ናትና ማጣትህም ጊዜያዊ ነው ። በአካል ተባብረህ በልብ ከምትለያይ በአካል ተለያይተህ በልብ መቀራረብ ይሻላል ። የአንድነት ትርጉም አንድ አዳራሽ ውስጥ መሰብሰብ ሳይሆን አንድ መንፈስ መያዝ ነው ። የማይደግፍ ባለጠጋ ልጅ ልመና ከልክል ነው ፣ ልጁ አለ እያለ ሁሉ ይጨክንብሃልና ። ልጄ ይጦረኛል ብለህ ሀብትህን አታሟጥ ፣ የድርሻውን ብቻ ስጥ ። ልጅ ከጦረው እጁ የጦረው ይሻላል ። 

ወዳጄ ሆይ ! 

በምድር ላይ ያለው የመኖር ትርፍህ ከምትወደው ጋር ማሳለፍ ነው ። የማትችለውን ነገር እችላለሁ ብለህ አታውራ ፣ በግዳጅ ፈጽም የተባልህ ቀን መድረሻ ታጣለህና ። ያንተ ባልሆነ ጌጥ አታጊጥ ። ድህነትም ከጨዋነት ጋር ሀብት ነውና አትቀላምድ ። በእግዚአብሔር ቃል አታፊዝ ፣ በነገረ እግዚአብሔር ላይ አትቀልድ ። የሕጉ የመጀመሪያው ጠባቂ ንጉሡ ነው ። የበላይ ያከበረውን ሕግ የበታች አይዳፈረውም ። 

ወዳጄ ሆይ !

የወደቀውን ሰው እግዚአብሔር አያልፍም ። ወደሚፈሰው ደም እግዚአብሔር ያያል ። የምትሰጠውም ፍርድ  የነገ መውደቂያህ ይሆናል ። ባልገባህ ነገር መጸለይ ክብር ነው ። ሁሉን ተናግረህ ስለማትዘልቀው ዝም በል ። ፍርድህ በቀል ፣ ቅጣትህ ንዴት ማብረጃ አይሁን ። ፍርድና ቅጣት ትምህርት ብቻ ይሁን ። የሌላው ሌሊት ቀን ይከተለዋልና አትጨክን ፣ ያንተ ቀንም ሌሊት ይከተለዋልና መብራት የሚሆን ተግባር ፈጽም ። 

የክብር ቀን ይሁንልህ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ