ሰኞ፣ መስከረም 29 2004
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓመቷ ውስጥ አራት ዐበይት የዘመን ክፍሎች (ወቅቶች) አላት፡፡ ይህም በባሕረ ሐሳብ (ቁጥር ያለው ዘመን) ይታወቃል፡፡ በቤተ ክርስቲያን በየዕለቱ የሚነበቡት የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች፣የሚዘመረው መዝሙር፣የሚቀደሰው ቅዳሴና የሚሰጠው ትምህርት አራቱን ወቅቶች መሠረት ያደረገ ነው፡፡ አራቱ ወቅቶች ወይም የዓመት ክፍሎች የሚባሉት መፀው፣በጋ(ሐጋይ)፣ጸደይ(በልግ) እና ክረምት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መባቻ መስከረም 1 ቀን ሲሆን፤ የየወቅቶች መባቻ ደግሞ በየሦስት ወሩ 26ኛ ቀን ነው፡፡
መፀው- ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25
በጋ- ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25
ጸደይ- ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25
ክረምት- ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25
በዚሁ መደላድልና በቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊት መሠረት አዲሱ ዓመት በገባ በ26ኛው ቀን፣ መስከረም 26 ቀን 2004 ዓ.ም. ዘመነ መፀው ተቀብለናል፡፡ መፀው አበባ ማለት ነው፡፡ መገኛ ቃሉ (ግሱ) መፀወ አበበ፣አበባ ያዘ፣አቆጠቆጠ ማለት ነው፡፡ የአበባ (ጽጌ) ወራትም ይሰኛል፡፡ በመፀው ውስጥ ሦስት ንኡሳን ክፍሎች ይገኛሉ፡፡
1) ዘመነ ጽጌ (መስከረም 26- ኅዳር 5)
ዘመነ ጽጌ ስድስት እሑዶችን (ሰንበታተ ክርስቲያን) ይዟል፡፡በዚህ ንኡስ ክፍል በሙሽራና በሙሽራዪቱ ምሳሌ ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያኑ በጽጌ (አበባ) መነጋገራቸውን በመኃልይ ይታሰብበታል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ማርያምና ሕፃኑ ኢየሱስ ወደግብፅ መሰደዳቸውና በስደት መከራ ማየታቸው ይታሰብበታል፡፡ አርባው ቀን የጽጌ ጾም፣ ጾመ ቍስቋም ተብሎ ይጾማል፡፡(መኃ.7፡7-14፤ኤፌ.5፣21-33፤ራእ.21፡31-40፤መዝ.127፡2-3፤ዮሐ.3፣25-36)
2) ዘመነ አስተምሕሮ (ኅዳር 6-ታኅሣሥ 6 ወይም 12)
አስተምሕሮ ማለት ምህላ ወይም ልመና፣ምልጃ ማለት ነው፡፡ በዚህ ንኡስ ክፍል ስለአምላክ ቸርነትና ትዕግስት፣ ሰንበትን ስለመቀደስ ምስጋና፣ጌታ በአይሁድ ምኩራቦች ስለማስተማሩና ባሕርን፣ነፋስን ስለመገሠፁ፣ዓይነ ስውራንን ፣በሽተኞችን ስለማዳኑ፣ስለዳግም ምጽአቱ ይታሰብበታል፡፡ (ሰቆቃወ ኤር. 3፡22-26፤ሮሜ.5፡10-21፤1ኛ ዮሐ.2፡1-17፤ሐዋ.22፡1-11፤መዝ.78፡8፤ማቴ.6፡5-15)
3) ዘመነ ስብከት (ታኅሣሥ 7 ወይም 13– ታኅሣሥ 28)
ዘመነ ስብከት ምዕመናን በጾምና ጸሎት ለክርስቶስ ልደት የሚዘጋጁበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ንኡስ ክፍል ያሉት ሦስት እሑዶች የየራሳቸው መጠርያ አላቸው፡፡ የመጀመርያው ስብከት፣ሁለተኛው ብርሃን፣ሦስተኛው ኖላዊ ይባላሉ፡፡ ዘመነ ስብከት በየዓመቱ የሚጀመርበትን ወይም የሚውልበትን እሑድ ማግኘት የሚቻለው በሚከተለው የአቆጣጠር መንገድ ነው፡፡ ታኅሣሥ 1 ቀን ማክሰኞ ቢውል ስብከት ታኅሣሥ 13 ይሆናል፡፡ ረቡዕ ቢውል ታኅሣሥ 12፣ሐሙስ ቢውል ታኅሣሥ 11፣ዓርብ ቢውል ታኅሣሥ 10፣ቅዳሜ ቢውል ታኅሣሥ 9፣ እሑድ ቢውል ታኅሣሥ 8፣ ሰኞ ቢውል ታኅሣሥ 7 ቀን ስብከት ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት የ2004 ዓ.ም. ታኅሣሥ 1 ቀን እሑድ ስለሚውል ስብከት ታኅሣሥ 8 ቀን ይሆናል፡፡
ዐውደ ስብከት
1) አንደኛው እሑድ ፣ከታኅሣሥ 8 ቀን እስከ ታኅሣሥ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ስብከት ይባላል፡፡ በዚህም ስለክርስቶስ መምጣት በኦሪተ ሙሴ፣ በነቢያት፣ በመዝሙር ተነግሮ መቆየቱ ይታሰባል፡፡ (ዘዳ.18፡15-22፤ዕብ.1፡1-14፤ 2ኛጴጥ.3፡1-9፤ ሐዋ.3፡17-26፤ መዝ.143፡7፤ ዮሐ.1፡44-51)
2) ሁለተኛው እሑድ፣ ከታኅሣሥ 15 ቀን እስከ ታኅሣሥ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ብርሃን ይባላል፡፡ በዚህም ክርስቶስ ብርሃን ሆኖ እንደሚመጣ በትንቢት ተነግሮለት መቆየቱን የሚያሳስብ ነው፡፡ (ኢሳ.60፡15-22፤ሮሜ.13፡11-14፤ 1ኛዮሐ.1፡1-10፤ ሐዋ.26፡12-18፤ መዝ.42፡3-4፤ ዮሐ.1፡1-18)
3) ሦስተኛው እሑድ፣ከታኅሣሥ 22 ቀን እስከ ታኅሣሥ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. ኖላዊ ይባላል፡፡ በዚህም ጌታችን ጠባቂ ሆኖ መምጣቱን አስቀድሞ ተነግሮለት እንደቆየ ይታሰብበታል፡፡ (ሕዝ.34፡11-16፤ ዕብ.13፡16-25፤ 1ኛጴጥ.2፡21-25፤ ሐዋ.11፡22-30፤ መዝ.79፡1፤ ዮሐ.10፡1-21)
ቤተ ክርስቲያን ከዓመት እስከ ዓመት ከመስከረም ዮሐንስ እስከ መስከረም ዮሐንስ ባሉት ቀናትና ሳምንታት፣በዓላትና አጽዋማት የሚነበቡትን ንባባት፣ የሚሰበኩትን ምስባካት (የመዝሙረ ዳዊት ሦስት መስመር ንባብ) ከብሉይና ሐዲስ ኪዳናት፣ በዕለተ እሑድ የሚዘመሩትን መዝሙራት ከቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት፣ የሚቀደሱትን ቅዳሴያት ከመጽሐፈ ቅዳሴ ለይቶ የሚያስረዳና የሚያሳይ መጽሐፍ ግጻዌ ይባላል፡፡ ግጻዌ ማለትም መለየት፣ መረዳትና ግልጥ ሆኖ መታየት ማለት ነው፡፡
ምንጭ
መሠረት ስብሐት ለአብ፤ ትውፊታዊ ኀሳበ ዘመንና ታሪኩ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አቋም ፣1981 ዓ.ም.፡፡
ዓሥራት ገብረ ማርያም፤ መርሐ ሕይወት ሦስተኛ መጽሐፍ ፣1993 ዓ.ም.፡፡
ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ፤ መጽሐፈ ግጻዌ ሐዲስ ዘተሰናአወ በአርባዕቱ ክፍላተ አዝማን ፣1989 ዓመተ ሥጋዌ፡፡