የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የኢትዮጵያ ወጣቶች

“በወጣትነት የለቀሙትን እንጨት በስተርጅና ይሞቁታል ።” /ጃፓኖች/

ወጣትነት እኔ ከተናገርሁ ሁሉን አሳምናለሁ የሚል ሁሉን ያለ ማወቅ ጠባይ ነው ። ወጣትነት እኔ ከተነሣሁ ሁሉን ጸጥ አደርጋለሁ የሚል የኃያልነት ስሜት ነው ። ወጣትነት እኔ የደረስኩበት ምሥጢር አለና ሁሉ ይሰማኝ የሚል የአውቃለሁ ባይነት መድረክ ነው ። ወጣትነት የሕይወትን ሩጫ በዕለት እፈጽመዋለሁ የሚል እሽቅድድም ነው ። ወጣትነት እኔ ብቻ ልናገር የሚል ጆሮን ቆርጦ የጣለ ችኩልነት ነው ። ወጣትነት ትልልቆች ደካማ ስለሆኑ እንጂ ምንም ከባድ ነገር በዓለም ላይ የለም የሚል የሁሉን ቻይነት ትኩሳት ነው ። ሁሉም ወጣት እንዲህ ያስባል ማለት አይደለም ። ወጣትነት ግን ይህን ስሜት ያመጣል ። ወጣትነት ሁለተኛ ልደት ነው ። ሰው ራሱን በእውቀት የሚወልድበት ነው ። እኔ ማን ነኝ ? የሚለውን ጥያቄ ጠይቆ በመልሱ የሚደሰትበት ነው ። “ራስን ማወቅ ትልቅ መልስ ነው” እንዲሉ ። ወጣትነት ብዙ ተስፋ አለውና ደስ ይላል ። በአንድ አለመሳካት ግን ተስፋ ይቆርጣልና ሊታዘንለት ይገባል ። ወጣትነት ግለት አለው ። እንደ ፍም እሳት ሳይሆን እንደ ቅጠል እሳት የሚግለበለብ ነው ። ወጣትነት ኃይል ነው ። ኃይል መሪ ያስፈልገዋል ። መኪና ኃይል አለው ። ትልቁ ኃይል ግን ትንሽ መሪ ያስፈልገዋል ። ወጣትነትም መካሪና ዘካሪ/አስታዋሽ ያሻዋል ። ወጣትነት ውበት አለው ። ባይቀባቡ ፣ ሰው ሠራሽ ነገር ባይጠቀሙ ወጣትነት በራሱ ውበት ነው ። እንስሳም በወጣትነቱ ያምራል ። ወጣትነት ከለጋነት ያለፈ ከደረቅነት የመለሰ ነው ። ወጣትነት የሕጻንነትና የጎልማሳነት ድልድይ ነው ። ወጣትነት ሁለተኛው የዕድሜ እርከን “እሳታዊ ዘመን” ነው ።

እሳት በትክክል ከተጠቀሙበት ያበስላል ። በሥርዓት ካልተያዘ ያወድማል ። ወጣትነትም እሳት ነው ። የሚያሰለጥነው ከተገኘ አገርን የሚጠቅም ፣ ወገንን ቀና የሚያደርግ ነው ። ወጣትነት ልሂድ የሚል ጉልበት እንጂ ወዴት መሄድ እንዳለበት የሚያውቅ ላይሆን ይችላል ። ወጣቶች መናገር ስለቻሉ አገር መምራት ይችላሉ ማለት አይደለም ። መታዘዝን የማያውቅ ወደ ማዘዝ መምጣት የለበትም ። የዕድገት ደረጃውን ያልጠበቀ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ። በየዕድሜው የሚደረስበት ደረጃ ቢኖር አገር ክብር ያገኛል ። ወጣቶች ገንዘብ አያያዝ ስለቻሉና ኪሳቸው ስለሞላ ቤት መምራት ይችላሉ ማለት አይደለም ። ወጣቶች ሰው አያያዝ ስለሚያውቁና ብልጦች ስለሆኑ ወላጆች ምሩን ብለው ቤቱን የሚለቁላቸው አይደሉም ። ወጣቶች እንግሊዝኛ ስለተናገሩ ዓለም አቀፍ እውቀት አዳበሩ ማለት አይደለም ። የትምህርት ምስክር ወረቀት ስለያዙ የሕይወት ብስለት አላቸው ማለት አይደለም ። በታላላቅ ተቋማት ስለሠሩ ታላቅ ሆኑ ማለትም አይደለም ። ወጣትነት የሚታረም እርሻ እንጂ ንጹሕ ማሳ ላይሆን ይችላል ።

ወጣቶች ሆይ እናንተ ያወቃችሁት በዓለም ላይ ያለው ብቸኛ እውቀት አይደለምና እውቀትም በየዘመኑ ያድጋልና ሌሎችን ለመስማት ፈቃደኛ ሁኑ ። እስከ ዘላለም የምንማር ነንና በሃያና በሠላሳ ዓመት እውቀትን ጠነቀቅናት ብላችሁ አታስቡ ። ዓለምን የሚገዛው ሥልጣን እንጂ ኃይል አይደለምና በጉልበት ሁሉን እቀይራለሁ ከሚል አስተሳሰብ ውጡ ። ይህች ዓለም የወጣቶች ብቻ ሳትሆን የሕጻናትም ፣ የጎልማሶችም ፣ የአረጋውያንም ዓለም ናትና ለሌላው ዕድል ስጡ ። ሁሉን ከያዛችሁ ሁሉን ታጣላችሁ ። ምኞት ካበዛችሁ በስካር ደንዝዛችሁ ትቀራላችሁ ። ሁሉንም ነገር በተራ ማድረግ ካልቻላችሁ በጭንቀት አእምሮአችሁን ታበላሻላችሁ ። እናንተ የደረሳችሁበት እውቀት አሳባዊ እንጂ ተግባራዊ ላይሆን ይችላል ። መሰልጠን ማለትም የራስን ይዞ የሌላውን መልካም መቀበል ነው ። የሌላውን ጨርቅ ለመልበስ ቆዳችሁ መላጥ አያስፈልጋችሁም ። ሕይወት ረጅም መንገድ እንጂ በአንድ ትንፋሽ የምትጠናቀቅ አይደለችምና እያረፋችሁ መጓዝን አትርሱ ። የሃይማኖት ትምህርት በኮርስ አያልቅምና ዘላለም የምትማሩትን እግዚአብሔር ጠንቅቄዋለሁ ብላችሁ አታስቡ ። እናንተ በወሬ የሰማችሁትን እውቀት አረጋውያን በሕይወት በማለፍ ያውቁታልና የተግባር ድሀ እንደ ሆናችሁ እመኑ ።

በወጣትነት የዘራችሁትን በሽምግልና ታጭዳላችሁ ። በወጣትነት ስርቆት ከጀመራችሁ እስከ ሽምግልና ስማችሁ አይጠፋም ። አመንዝራ ከሆናችሁም ወደ ማታ ላይ ለማኝ ትሆናላችሁ ። ሱስ ውስጥ ከገባችሁ በየቀኑ ከርታታ ትሆናላችሁ ። በወጣትነት ገንዘብን በአግባቡ ከተጠቀማችሁ በሽምግልና መልካም ማረፊያ ታገኛላችሁ ። ትልልቅ ሰዎችን ካከበራችሁ ለትልቅ ቦታ ትታጫላችሁ ። ሹሙኝ ብላችሁ ማመልከቻ ካስገባችሁ በጣም ትናቃላችሁ ። እውቅና ሳይሆን እውቀትን ከፈለጋችሁ በመብራት ትታሰሳላችሁ ። የሙያ አባቶቻችሁ ቢመቱአችሁ ዝቅ ብላችሁ ዱላ ከተቀበላችሁ እንጀራችሁ ይሰፋላችኋል ። ወላጆቻችሁን መውቀስ ካቆማችሁ ምርቃት ይተርፋችኋል ። አገራችሁን ስትወዱ የሌላው አገር መዝናኛችሁ ይሆናል ። ታማኝነትን ስታዳብሩ ዋጋችሁ ከፍ እያለ ይመጣል ። ብዙ ገንዘብን ሳይሆን ብዙ ፍቅርን ስታተርፉ ለክፉ ቀን ገላጋይ ትሆናላችሁ ። በአጭር ቃል እንጨቱ የሚሰበሰበው በወጣትነት ሲሆን እሳቱን የምትሞቁት በሽምግልና ነው ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፡- “ሽምግልናችንን ያልናቀች ወጣትነታችን የተባረከች ናት” ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ማታችሁ ያማረ ይሁን ። ሳቃችሁን ያስመሽላችሁ ። አሜን

የብርሃን ጠብታ 24

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 18 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ