ሃይማኖት የለሽነት
በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ እየተጋረጠ ያለው ፈተና አንዱ ሃይማኖት የለሽነት ነው ። በአደባባይ እግዚአብሔር የለም ብሎ መካድ ጊዜ ያለፈበት ፋሽን ሆኗል ። አለ እያሉ ግን እንደሌለ አድርጎ መኖር ዘመናዊነት ተደርጎ ተወስዷል። አባቶች እንደሚነግሩን ሁለት ዓይነት ክህደት አለ ። የጴጥሮስና የአርዮስ ። የጴጥሮስ ክህደት ምንድነው ካልን ጴጥሮስ በአፉ እየካደ በልቡ ያምን ነበር ፣ አርዮስ በአፉ እያመነ በልቡ ይክድ ነበር ። መጨረሻውን ስናየው ጴጥሮስ ሥጋዊ ፍርሃት ይዞት እንጂ ጌታውን ጠልቶ አልነበረምና በንስሐ ተመለሰ ፤ አርዮስ ግን በልቡ እየካደ በአፉ አማኝ መሳይ ነበርና ፍጻሜው አላማረም ። በዚህ ዘመን ያለው የአርዮስ መንገድ ነው ። በአፍ የእግዚአብሔርን ስም መጥራት በልብ ግን መካድ እንደ ትልቅ ሥልጣኔ እየታየ ነው። ዲያብሎስ ዋነኛ መገለጫውና የግል ገንዘቡ የሆነችው ኃጢአቱ ውሸት ናት ። ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት ውሸታቸውን እውነት ለማስመሰል ይጥራሉ ። በአየሩ ላይ የእግዚአብሔር ስም በጣም ይጠራል ፣ እግዚአብሔርን ግን በልቡ የሚያከብር እየተገኘ አይደለም ። ሰዎች በአፋቸው እያመኑ በልባቸው የሚክዱት የመጀመሪያው ምክንያታቸው አብዛኛው ሰው ያምናል ብለው ስለሚያስቡ ከብዙኃኑ ጋር ላለመጣላትና ንግዳቸውን ላለመክሰር ነው ። የእግዚአብሔርን ስም ሕዝብን እንደ መግዣ መሣሪያ ሲጠቀሙበት የኖሩ ነገሥታት በታሪክ ውስጥ አሉ ። ከአጋንንት ጋር ቃል ኪዳን ያላቸው ሳይቀሩ ስመ እግዚአብሔርን ግን እንደ ማደናገሪያ ይጠቀሙበት ነበር ።
ሃይማኖት የለሽት እየተስፋፋ ነው ። የስህተት ትምህርቶች መጨረሻቸው ሃይማኖት የለሽነት ነው ። የስህተት ትምህርት እውነትን ማጣመም ፣ የከበረውን ማዋረድ ነው ። ለእግዚአብሔርም ሌላ መልክ መስጠት አንዱ መገለጫው ነው ። እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው የሚለውን ትምህርት ሦስት አካላትን በመጨፍለቅ አንድ ማድረግ ፣ አንድ አምላክነትን በመበተን ብዙ አማልክት መፍጠር አንዱ የስህተት ትምህርት መገለጫ ነው ። የስህተት ትምህርት ምንጩ ሰይጣንና ፍልስፍና ነው ። ስለዚህም ምሥጢራትን ማቃለል ጥምቀትን ውኃ ነው ፣ ቍርባንን ተራ ማዕድ ነው ማለት ጠባዩ ነው ። ሰይጣን በአንድ ጊዜ በማስጣል ውጤታማ አይሆንም ። ቀስ በቀስ እያቃለለ ፣ የከበረውን ነገር እያሳነሰ ሰዎችን ቅለት ያለማምዳቸዋል ። ለዚህም ትክክለኛነት እንዲሰማቸው ያደርጋል ። ዋናው ኢየሱስን ማወቅ ነው ይላቸውና ኢየሱስ አርአያ የሆነበትን ደግሞም ያዘዘውን ጥምቀት እንዲንቁ ያደርጋቸዋል ። አጥሩን በማፍረስ በመጨረሻ ከሀዲ ይፈጥራል ። የስህተት ትምህርት እግዚአብሔር የለም ብሎ አይጀምርም ፣ መጨረሻው ግን እግዚአብሔር የለሽነት ነው ። እግዚአብሔር ያከበራቸውን በሰማይም በምድርም ያሉትን መናቅ የስህተት ትምህርት ጠባይ ነው ። ራስን ከከበሩት ጋር በማወዳደር ለቅዱሳን ጥላቻን መያዝ ፣ በምድር ካሉት አገልጋዮች ጋር ቁመት መለካካት ሰይጣን ለሰዎች የሚያለማምደው የስህተት ትምህርት ውጤት ነው ። እነዚህ ሰዎች በያዙት አቋም ባይረኩ እንኳ የሚሄዱት ወደ ክህደት እንጂ ወደ እውነተኛው ሃይማኖት አይደለም ። ወደ እውነተኛው ሃይማኖት እንዳያቀኑ አስቀድሞ የተትረፈረፈ ጥላችን ተሞልተዋል ።
ሌላው ሃይማኖት የለሽነት ለሃይማኖት የተቆረቆሩ በማስመሰል ሃይማኖትን መነገጃ ማድረግ ነው ። በውጭው ዓለም በማስታወቂያ ቀሳውስት ስለሚቀጠሩ ሥርዓቱና ትምህርቱ የማያምን ሰው ሊፈጸም ይችላል ። በአውሮፓ ሃይማኖት የሞተው በዚህ መንገድ ነው ። ቅጥረኛ እንጂ ሃይማኖት ያለው ሰው ማገልገል በማቆሙ ካቴድራሎቹ ባዶአቸውን ቀሩ ። በአደባባይ ቆመው እርር ድብን ብለው የሚሰብኩ ፣ የኢየሱስን መከራ በማሰብ የሚያለቅሱ ግን እንደገና ቢመጣ የሚሰቅሉት ሰዎች በዚህ ዘመን አሉ ። ለእነርሱ መድረኩ የተውኔት ጣቢያ ነው ። አሊያም የእውቅናቸውና የቢዝነሳቸው ስፍራ ነው ። እንደውም ታክስ የማይከፈልበት የንግድ ስፍራ የሆነላቸው ብዙ የቤት ቍጥር ተሳስተው የገቡ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ከእነርሱ ውጭ የሚሰብክ ፣ የሚዘምር ፣ የሚጽፍ አይፈልጉም ። ምክንያቱም ንግዳቸው ተቀናቃኝ የመጣበት መስሎ ይሰማቸዋል ። ሃይማኖትን እንደ ኳስ ቡድን የሚደግፉ ፣ የብሽሽቅ መሣሪያ የሚያደርጉ ፣ ለአሸናፊነት የሚወዳደሩ ነገር ግን ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች እየበረከቱ ነው ። ሃይማኖት ያለው ሰው ራሱን የካደ ፣ ጥቅሙን ለወንጌል የሠዋ ፣ ወንድሜ ይዳንልኝ ብሎ የሚጨነቅ ፣ የወገኑን ገመና የሚሸፍን ፣ ያለውን አካፍሎ የሚያድር ፣ ልቡ ስስ የሆነና ለችግረኛ የሚያዝን ነው ። እነዚህ ሃይማኖት የለሾች ግን ሕዝቡን አይወዱትም ። ሕዝቡ የሚፈልገው ምንድነው ( በማለት አዲስ አበላልን ይዘረጋሉ ። ሃይማኖት ፣ ሃይማኖት በሌላቸው ሰዎች እጅ መውደቅ በታሪክ ውስጥ ተደጋጋሚ ክስተት ነው ።
ብዙ ሰው ስመ እግዚአብሔርን ይጠራል ። በእግዚአብሔር የሚያምን ግን ጥቂት ነው ። ያለ እየመሰለው ተበልቶ ያለቀው ቍጥር የለውም ። አዲስ ትውልድ በሁለት መንገድ ሃይማኖትን እየከሰረ ነው ። የመጀመሪያው በማስመሰል ሲሆን ሁለተኛው በፍጹም ክህደት ነው ። እግዚአብሔርን የለም ለማለት የሚደፍሩ ዕለት ከዕለት እየተበራከቱ ነው ። ይህ አሳሳቢ ነው ። የእነዚህ ሰዎች ምክንያት ያለፉበት የጦርነትና ያዩት አሰቃቂ ታሪክ ሊሆን ይችላል ። የሃይማኖት መሪዎች የሚያሳዩት ለዘመን አዳሪነት አሳዝኖአቸው ሊሆን ይችላል ። የውጭው ዓለም ተጽእኖ አሸንፎአቸው ሊሆን ይችላል ። ምክንያቱ ግን ስህተቱን ቆንጆ አያደርገውም ። ደግሞም ያልካደንን መካድ ትልቅ አበሳ ነው ። ሳቅ ስላቅ የሰይጣን ዋነኛ ጠባይ ነው ። ሳቅ ስላቅ ሲበዛ አጋንንት በምድር ላይ ሰልጥነዋል ማለት ነው ። ጋኔን ጎታቾች ሳይቀር መጀመሪያ የሚያዩት የአጋንንትን ሳቅ ስላቅ ነው ። በአጋንንት ዓለም ሳቅ ስላቅ ትልቁ ተግባር ነው ።
በርግጥ በእውነት እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ እሙን ነው ፣ ጨርሶ አይጨልምም ። እግዚአብሔር ራሱን ያለ ምስክር አይተውምና ።
ይቀጥላል
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ታኅሣሥ 8 ቀን 2017 ዓ.ም.