የኢትዮጵያ ወጣቶች በሚያልፉባቸው የተለያዩ ችግሮች ምክንያት አሁን ላይ እየታዩ ያሉ ውጤቶች አሉ ።
ገንዘብን የሕይወት ዋስትና ማድረግ
ዓለም በርእዮት መልኩ ባለጠግነትን ታራምዳለች ፣ በሃይማኖት ስምም ባለጠግነት ይሰበካል ። የዚህ ዓለም ገዥ ገንዘብ እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየታወቀ ነው ። ገንዘብን እያሳዩ የፈለጉትን ስህተት የሚያሠሩ ፣ ብሔራዊ እሴቶችን የሚያጠፉ ፣ የአገራትን እጅ የሚጠመዝዙ የዘመናችን ኃያላን አሉ ። ገንዘብ ብዙዎችን ከሃይማኖትና ከጥሪያቸው ለይቷቸዋል ። ፍቅረ ንዋይን ያወግዙ የነበሩ ሰዎች በዚህ መርዝ ተይዘዋል ። በመጀመሪያው የሰው ልጅ ጉዞ የነበረው ኃጢአት በመጨረሻው ዘመን ላይ መንገሡ ግድ ነው ። ስስት ፣ ትዕቢት ፣ ፍቅረ ንዋይ አዳምን ያጠመዱ የኃጢአት ራሶች ናቸው ። እነዚህ ስህተቶች በመጨረሻው ቀን ይሰለጥናሉ ። የሰው ልጅ በቃኝ የማይል ስስታም ፣ ነጥቆ አዳሪ ፣ በሌላው ንብረት የሚቀና ፣ ለመስጠት የሚፈተን ፣ ሁሉን ላፌ የሚል ፣ ብልጣብልጥነት ያሳነሰው ፍጡር ይሆናል ። ወንዱም ሴቱም ተፈጥሮአቸውን ተቀበሉት እንጂ አልፈጠሩትም ። ትዕቢት ግን እግዚአብሔርን ተክቶ እኔ በማለት ይቆማል ። በዚህ ዘመን ሰዎች ራሳቸውን በመሸጥ ፣ ስለ ራሳቸው በግነት በማውራት ፣ መብቴ ነው በሚል ድምፀት ትዕቢትን ጣዖት አድርገው አጥነዋል ። ካለህ አለህ ፣ ከሌለህ የለህም እያለ በግልጽ የሚፈክር ዘመን ይህ የእኛ አናሳ ዘመን ነው ። ሰዎች ገንዘብ ለሰጣቸው ሁሉን ለመሆን ዝግጁ ናቸው ። ገንዘብ ሕሊናን የሚያሸጥ ፣ ሰብአዊ ክብርን የሚያስጥል ፣ ከሃይማኖት ማማ የሚያወርድ ነው ። የወንድምን ፍቅር በመሻማት እንደ ገንዘብ የሚፈታተን ነገር የለም ። ብዙ ሰዎች ወዳጃቸውን በገንዘብ ምክንያት አስቀይመዋል ። ይልቁንም የእርሱ የጋራ ፣ የእኔ የግል የሚል አመለካከት እየዳበረ ነው ። በዚህ ምክንያት በሰው እጅ ያለውን በመብት ደረጃ ለመንጠቅ የሚፈልጉ ፣ ቀማኝነትን ያሳደጉ ወገኖች እየበዙ ነው ። ሰውን ለመኖር የሚያስከፍሉ ፣ አፍነው የሚደራደሩትን ወጣቶች ስናይ ገንዘብ የሰው ልጆችን ምን ያህል እንደ በከለ መገንዘብ ይቻላል ።
የአገር አለመረጋጋት ወጣቶችን እንዳይረጋጉ ያደርጋቸዋል ። አንዳንዱ አገር ጥሎ ሲሰደድ ሌላው ደግሞ በትዕግሥት እንዳይኖርና እንዳይሠራ ያደርገዋል ። በዚህ ምክንያት ወጣቶች በአንድ አዳር ሚሊየነር ስለመሆን ያስባሉ ። በአንድ ጊዜ ባለጠጋ ለመሆን የሚያስብ ሰው የዕድገት ሕግን ያፈረሰ ፣ በነገ ላይ ምንም ተስፋ የሌለው ሰው ነው ። በአእምሮ ሰላምና በመረጋጋት የኖሩት ፣ ሌላውንም ለመርዳት የቻሉት እነዚያ የቀደሙት ወላጆቻችን ሕይወት ነገም እንደሚቀጥል ተገንዝበው የዕለት የዕለቱን መኖር በመቻላቸው ነው ። ትርፍ ነገር አልነበራቸውም ፣ ነገር ግን አልጎደለባቸውም ። እንደ ጎርፍ የሚመጣ ዕድል ጠርጎ የሚሄድ ነው ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለጠጋ ከሆኑት አንዳንዱ አገር ለቆ ተሰዷል ፣ ሌላው እስር ቤት ይገኛል ። ሌላውም በአእምሮ ጭንቀትና በተበላሸ ትዳር ይዳክራል ። የእድገት ሕጎች ነገን ለመኖር ተስፋ የሚሰጡ ናቸው ። እንኳን ሁሉም ነገር ዛሬ ይሁንልኝ ብሎ ማልቀስ ይቅርና ሁሉም ነገር ዛሬ ይሁንላችሁ ተብሎ ብንለመን እንቢ ማለት አለብን ። የሰውን ልጅ የሚያኖረው ያልተፈጸመ ሕልሙ ነው ። በዚህ ዘመን ያሉ ወጣቶች በአብዛኛው ዋጋ ሲጠሩ ፣ ይህን ያህል አምጡ ሲሉ ስቅቅ አይላቸውም ። ይህ የሚያሳየው ጨካኞችና የገንዘብ አምልኮተኞች መሆናቸውን ነው ፣ ፍቅር አልባ የሆነ ሰው አለው ያምጣ የሚል ነው ።
ሁሉንም ነገር ወደ ቢዝነስ የመቀየር ስልት በጣም አደገኛ ነው ። ዛሬ በፐርሰንት ሳይቀር ለቤተ ክርስቲያን የሚያስለምኑ አሉ ። ለገዛ ወላጆቻቸው በገንዘብ የሚሠሩ ትውልዶች እያየን ነው ። ገንዘቡ ቢገኝም ዕድሜው ግን ውድ ሆኗል ። ገንዘብን ለማግኘት የተጠቀሙበት ብልጠት ለመኖርና ሞትን ለማምለጥ አልረዳም ።
ወጣቶች ከሁሉ ለምትበልጠው ጸጋ ለፍቅር ቅኑ!
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም.