ልጁ የስምንተኛ ክፍል የመሸጋገሪያ ፈተና ተፈተነ ። እቤቱ ገብቶ ግን በጣም ይጸልያል ። ጸሎቱም፡- “እግዚአብሔር ሆይ፥ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሐዋሳ እንድትሆን እለምንሃለሁ” የሚል ነው ። ጸሎቱ ብርቱና በጩኸት የተሞላ ደግሞም ስለ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ መሆኑ ግራ ያጋባቸው ቤተሰቦቹ ልጁን ጠርተው ፡- “እንዲህ ያለ ጸሎት የምትጸልየው ለምንድነው ?” አሉት ። ልጁም፡- “አይ ፈተናውን ስፈተን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ማን ነች ? የሚለውን አዲስ አበባ ማለት ሲገባኝ ሐዋሳ ብዬ ስለመለስኩ መሳሳቴን አወቅሁ ፣ ስለዚህ የእግዚአብሔር የኢትዮጵያን ዋና ከተማ ሐዋሳ እንዲያደርግልኝና ውጤት እንዳገኝ እየለመንኩት ነው” አለ ይባላል ።
እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ አምላክ ነው ። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም በማለት ከተፈጥሮ በላይና ሊገጥሙ የማይችሉ ነገሮችን መተረክ ተገቢ አይደለም ። ምክንያቱም የተፈጥሮን ሕግና ውበት የሠራ ራሱ እግዚአብሔር በመሆኑ ያከብረዋልና ነው ። እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው በማለትም ለስህተታችን የእርሱን ድጋፍ መፈለግ አይገባም ። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ናት ። እግዚአብሔር ሐዋሳ ማድረግ ይችላል ። ነገር ግን እግዚአብሔር ቻይነቱን ለልጆች ጨዋታና ለውድድር አያውለውም ። ደግሞም የእግዚአብሔር ቻይነት ለስህተታችን ሽፋን የሚሰጥ ሳይሆን ስህተታችንን የሚያርም ነው ። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሐዋሳ ላይ ሲሆን ብዙ ነገሮች ይዘባረቃሉ ። እንደ አዲስ መጀመር ይጠይቃል ። ልጁ ግን እርሱ አንድ ጥያቄ ከሚሳሳት ሚሊየን ነገሮች ቢተራመሱ እየፈቀ ነው ። ምክንያቱም ሚሊየን ነገሮች ከእርሱ አንድ ጥያቄ አይበልጡምና ነው ። ልጅነት የሚያስበው እንዲህ ነው ።
እግዚአብሔር በስህተታችን እንድንታረም ይፈልጋል ። የምንኖረው ገና የማናውቀው ነገር ስላለ ነው ። ላለ መውድቅ እንማራለን ፣ ወድቀን ለመነሣትም እንማራለን ። ሁሉንም ነገር ማወቅ አንችልም ፣ አይጠበቅብንም። ሁሉንም ነገር ካወቅን ውጤቱ ምንም አናውቅም ማለት ነው። ሁሉንም ነገር ልንመልስ አንችልም ። መኖርን አጓጊ ከሚያደርገው ነገር አንዱ ገና የማናውቀው ነገር መኖሩ ነው ። አሊያ የሚመጡት ቀኖች ድግግሞሽ ይሆናሉ ። ቀጣዮቹን ቀኖች እንግዳ የሚያደርጋቸው ሌላ ጥያቄና ፈተና ይዘው የሚመጡ በመሆናቸው ነው ።
መሳሳትን የሚፈራ ሰው መሞከር አይችልም ። መሳሳት ለሰው ልጅ መጨረሻ አይደለም ። እንደውም የማወቅ መነሻ ነው ። ሰው የተማረውን ሊረሳ ይችላል ፣ የተሳሳተውን ግን አይረሳም ። የማይረሱ ትምህርቶችን ያገኘነው ከስህተት በኋላ ነው ። ውኃ ከተበጠበጠ በኋላ እንደሚጠራ እንዲሆንም ከብዙ ትርምሶች በኋላ ሰላም ይሆናል ። ቋንቋ የማንለምደው ለምንድነው ? ስንል መሳሳትን ስለምንፈራ ነው ። ፍጹምነትን የሚከተሉ ሰዎች ካወቁት ውጭ ለማወቅ አይደፍሩም ። ሙከራ የጥራት እናት ነች ። ፍጹምነትን የሚከተሉ ግን አይሞክሩም ። እርግጥ ነው የሚደናቀፍ የሚንቀሳቀስ ነው ፣ ከመቀመጫው የማይነሣ ገልቱ አይደናቀፍም ። ከስንፍና ፍጹምነት ፣ የመሥራት ስህተት ይሻላል ። ከመነሻው ፍጹምነትን የሚፈልግ አይጀምርም ። ከፍጹምነት የሚጀምርም የሚሄደው ወደ ጎዶሎነት ነው ። አንድን ሰው ቅዱስ በማለት የሚጀምር ሰው ርኩስ ወደ ማለት መሄዱ አይቀርም ። ፍጹምነትን ስንፈልግ ከራሳችንና ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር አንችልም ። ትልቅ ስልጣኔና ትልቅ መንፈሳዊነት መሳሳትን እንደ አደጋ አለመቊጠር ነው ። ገና የሚሞት ሥጋ ይዘን በመታመም ከተደነቅን አስቸጋሪ ነው ። አለመደነቅ ጉልበትን ይጠብቃል ።
ስህተታችንን በሌላ ስህተት ማጥራት አይቻልም ። ደም በደም አይጠራም ። ደም ግን በውኃ ይጠራል ። በምንም መንገድ ስርቆት በግድያ አይሸፈንም ። ዝሙትም በሌላ ዝሙት አይጋረድም ። መሸፈኛው ንስሐ ብቻ ነው ። መሳሳትን ማመን ለቀጣይ ቀን ክብር መስጠት ነው ። መሳሳታቸውን የሚያምኑ ብቻ እንደገና መጓዝ ይችላሉ ። አለመውደቅ ክብር ነው ፣ ወድቆ መነሣት ግን የበለጠው ክብር ነው ። ሁልጊዜ ከመቶ መቶ የሚያመጡ ተማሪዎችን ዘጠና ከመቶ ሲያመጡ እንቆጣቸዋለን ። እነዚህ ተማሪዎች ግን የፍጹምነት ተከታይ ስለሚሆኑ አንድ ስህተት የተሳሳቱ ቀን መኖርን እየጠሉ ይመጣሉ ። ለብዙ ሰው ከመሳሳቱ በላይ ሰው ምን ይለኛል ? የሚለው ነገር ያስጨንቀዋል ። ሰው እንደ እርሱ የሚሳሳት መሆኑን ይዘነጋል ። በዋናነት የምንኖረው ከእግዚአብሔርና ከኅሊና ጋር ነውና መጀመሪያ ክብር መስጠት ያለብን ለእግዚአብሔርና ለኅሊና ነው ።
ስህተታችን እንዳልተሠራ ቢሆንልን እንመኛለን ። ይህ ሞኝነት ነው ። ስህተት ግን የማይካስ ማለት አይደለም ። የክርስቶስ ምሕረት የስህተታችን ትልቁ ካሳ ነው ። “እንዴት እኔ ይህን አደረግሁ ?” እንላለን ። እንዴት እኛ ይህንን አናደርግም ? ሌሎች ያደረጉትን ኃጢአት ያላደረግነው ያንን የማያደርግ ሥጋ ስለ ተሸከምን ሳይሆን የእግዚአብሔር ክንድ ስላገዘን ብቻ ነው ። እንዴት እኔ ይህን አደርጋለሁ ? ማለት መመጻደቅ ነው ። አንድ አባት፡- “በዚህ ዘመን ለምን ተፈጠርሁ ? ማለት መመጻደቅ ነው” ያሉትን አልረሳም ። አዎ ስህተቱ በትክክል ተፈጽሟል ። ነገር ግን በመማር ይስተካከላል ። የበደልነውን መካስ ፣ የቀማነውን መመለስ ይገባል ። ትላንት የስህተት ዛሬ ፣ የእርምት ቀን በመሆኗ ልንደሰት ይገባናል ። “አንድም የተሠራ መንገድ ፈልግ ፣ አሊያ መንገድ ሥራ ፣ ፍላጎት ካለ መንገድ ይኖራል ።” ለስህተት ሳይሆን ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን ይገባል ። ብዙ ሰዎች ከስህተት ለመመለስ የማይፈልጉት ብዙ ዘመን እውነት ብለው ስላደረጉት ያኖሩበት ዓመት የተሰረዘ ስለሚመስላቸው ነው ። ከኖርንባቸው ብዙ የስህተት ዓመታት አንዱ የእውነት አዳር ይበልጣል ። እባካችሁ ቀጥሎ ያለውን ጥቅስ አብራችሁኝ በሉ፡- “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ።” /መዝ. 83፥10/ ።
ጸሎት ማለት የእኛ ፈቃድ በሰማይ የሚሆንበት ሳይሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ በምድር ላይ የሚሆንበት ነው ። ጸሎታችን ለስህተታችን ይቅርታን እንጂ ትክክለኛነት አይሰጥም ። የተፈጥሮና የእግዚአብሔር ሕግጋት በተሰመረላቸው መስመር ይሄዳሉ እንጂ በጸሎት ለማስተጓጎል ብንሞክር የሚሆነው ድካም ብቻ ነው ። ምክንያቱም የተፈጥሮ ድንጋጌም የእግዚአብሔር ሕግ መሆኑን ማወቅ አለብን ። ስህተት የሆኑ ነገሮችን ትክክል ለማድረግ እንሞክራለን ። እንጸልያለን ። ይህ እግዚአብሔርን የስህተታችን ተባባሪ ማድረግና ስሙን በከንቱ መጥራት ነው ። ደግሞም እግዚአብሔርን አለማክበር ነው ። ከማያምኑ ጋር ጓደኝነት እንጀምርና እግዚአብሔር እውቅና እንዲሰጠን እንጸልያለን ። ጸሎታችን ሥሙር የሚሆነው ቃሉን ስናውቅ ነው ። ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚያደርግልን በቃሉ ሚዛን ነውና ። እግዚአብሔርን መቅረባችን የእርሱን ጠባይ ለመውረስ እንጂ እርሱን በእኛ ደረጃ ዝቅ ለማድረግ መሆን የለበትም ። በዘመናት የቤተ ክርስቲያንን ጉዞ ከተፈታተኑ ነገሮች አንዱ ቤተ ክርስቲያን ከቃሉ በታች ናት ወይስ ከቃሉ በላይ ናት ? የሚለው ክርክር ነው ። ቤተ ክርስቲያን ከቃሉ በላይ ናት የሚለው አስተሳሰብ ነው “ፖፑ አይሳሳትም” የሚለውን ትምህርት የወለደው ። ቃሉ ሁሉን ያርማል ፣ ቃሉ ግን በማንም አይታረምም ። ራሱ እግዚአብሔርም አያርመውም ። ምክንያቱም የወጣው ከፍጹምነቱ ነውና ።
አደጋን ከሚቀንሱ ነገሮች አንዱ መብረድ ነው ። ፍሬን የተበጠሰበት መኪና የሚያምርበት ነዳጅ ሲቀንስ እንጂ ሲሰጥ አይደለም ። እንደ ተሳሳትን ባወቅነው ነገር መማርና መደሰት እንጂ ልክ እንዲሆኑ መጸለይ ተገቢ አይደለም ። ልብ አድርጉ ዝንጀሮን ባቆነጀናት ቊጥር እያስጠላች ትመጣለች። ስህተትም በተቀባባ ቊጥር እየጎላ ይመጣል ። ኖረን ስላልጨረስን እንኳን ተሳሳትን ። ቶሎ ከተማርን አዲስ ነገር እናውቃለን ። ስህተታችን ላይ ከዘገየን ግን ብዙ ነገሮች ያልፉናል ። ጳውሎስ የኋላውን ቢያስብ ነፍሰ ገዳይ ነው ። እርሱ ግን “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” አለ /ፊልጵ. 3፥13/ ።
እባካችሁን ዛሬ ያስቀየማችሁትን ሰው አጥፍቻለሁ ይቅር በለኝ በሉት ። ጥቁር ድንጋይ ተሸክማችሁ ለምን ትኖራላችሁ ? የዛሬ ትክክለኛነታችሁን ጣሉት ። ይቅርታ መጠየቅ ለዚያ ሰው ወይም ለእኛ ክብር መስጠት ሳይሆን ይቅር ተባባሉ ላለው ጌታ ክብር መስጠት ነው ። ደግሞም ትክክል እንዳልሆነ ኅሊናችሁ ለሚመሰክርላችሁ ነገር ዛሬ ቆራጥ ሁኑ ።
እግዚአብሔር በመልካም ያስበን ።
ተጻፈ አዲስ አበባ
ቅዳሜ ሚያዝያ 27/2010 ዓ.ም.