እንደ እኔ የእሳት እራትነት አንተ ባትጠብቀኝ ኖሮ አልኖርም ነበር። አልሆኑም ፣ አልተሳኩም ብዬ ያዘንኩባቸው ትንሽ ቆይቼ ሳያቸው ለካ ድል ናቸው:: ያለ መሆን ድል፣ ያለ መሳካት ምርኮ፣ ኑሮን ከስሮ ሕይወትን አትርፎ መግባት ካንተ ዘንድ ብቻ ይገኛል። ትዳሬ ለማድረግ ያሰብኩትን እነ እገሌ ነጠቁኝ እላለሁ፣ ለካ የሩቁን አይተህልኝ ነው። የአንጀት ምስጋና ያለው ለምነው ካገኙት ይልቅ ባለመሳካቱ ከተናደዱበት ነገር ነው። ቆይተው ሲያዩት ሁሉም ነገር ተቃራኒ ነው። የጠበቁት የተመኙት ሲሆን ደስ ይላል ፣ አለመሳካት ግን በጌታ እውቀት ውስጥ ያለ የኋላ እሸ ት ነው::
ያንን ሰው ያንን አገር ካላገኘሁ ስል ለካ የከለከልከኝ ዛሬን እንዳይ ነው። ከማይበሉት እንጀራ፣ መርዝ ካለበት ገበታ የሚከለክል ያንተ ፍቅር ነው። ስለ ወጣሁት ተራራ ብቻ አይደለም፣ በጅምር ስለ ቀረው ነገር ምስጋና ይገባሃል :: ስለ ሞላው ሸለቆ ብቻ አይደለም ፣ እያለቀስኩ ከእጄ ስለ ተነጠቅሁት ነገር ውዳሴ ይገባሃል። ዛሬን አይቼ ለመንሁ፣ ነገን አይተህ ከለከልከኝ። ያመሰገንሁበት ስኬት ቆይቶ ያሳዝነኛል፣ ያላመሰገንኩበት አለመሳካት ቆይቶ ያስደስተኛል:: ባወቅህ ማረኝ፣ ባወቅህ ከልክለኝ። እኔ የእሳት እራት ነኝ፣ የእሳቱን ማማር እንጂ ማቃጠል አላውቅም። በማር ቃል የተናገረ ይወስደኛል፣ ያደነቀኝን የመጨረሻው ስጦታዬ ነው እለዋለሁ:: ስሱ ልቤ ላንተ ጠንካራ ነው:: ለኃጢአት አንድ ጊዜ ለጽድቅ ሁለት ጊዜ አስባለሁ።
ሳትጠይቀኝ ክፉውን ከልክለኝ። ነጻ ፈቃዴን ፈርሜሃለሁ፣ እያለቀስኩ ፈንጂውን ከእጄ ንጠቀኝ። አንተ ከሌለህበት ቤተ መንግሥት አንተ ያለህበት የውሻ ቤት አቤት ውብ ነው። እነዚያ የተፋረሱ ሽያጮች፣ እነዚያ የተሰረዙ ቀጠሮዎች፣ እነዚያ ታይተው የጠፋ ፍቅሮች እንኳን አልሆኑ የምለው ከርሞ ነው ። ሁሉን ሞክሬ ካላየሁ ስልህ ከሞት ትምህርት የለም ብለህ ከለከልከኝ :: ሞትን በልቅሶ ለወጥክልኝ፣ ስላልሆኑ አለቀስኩ፣ ሞትና ጸጸት እንደ ቀረልኝ ዘግይቼ አወቅሁ፡፡ አሁንም አንተን ለማወቅ ዘግይቻለሁ ፣ የደስታዬ ተቃዋሚ አድርጌሃለሁ፤ አንተ የሌለህበትን ሐሤት እፈልጋለሁ፣ ያላንተ መዝራት ለካ መበተን ነው! ለካ አንተ የሌለህበት ፍቅር ከጥላቻ በላይ ነው ! አንተ የሌለህበት ትዳር የመቃብር ሙቀት ነው። ችክ ባልኩበት ነገር ፣ ካልሰጠኸኝ እሞትብሃለሁ ባልኩት ዕድል ይኸው ስቀጣ እኖራለሁ :: አንድን ዕዳ ለመክፈት ሃያ ሰላሣ ዓመት አቃጥላለሁ። ባወቅህ ማረኝ ፣ ለእውቀቴ እንዳትተወኝ:: ዘመኑ አስፈሪ ነው፣ ሰውን ለማወቅም ሺህ ዘመን የማይበቃ ነው።
እባብ ለመደ ተብሎ ቀበቶ አያደርጉትም። አውሬው ዛሬ ለመደ ማለት እስከ መጨረሻው አይነካም ማለት አይደለም። የሌላውን ደም የሚያፈስ ወይን አፈሰሰልኝ ፍቅሩ ለእኔ ልዩ ነው አይባልም። ተኩላም ምንም ቤተኛ ቢሆን የበግ እረኛ አያደርጉትም :: ከሞት የዳንኩት ወደ ሞት ሰፈር ባለ መሄዴ አይደለም፣ አዳኝነትህ ስለበዛልኝ ነው። መርዙን ባታረክሰው የለሰለሰኝ ሁሉ ገዳዬ ይሆን ነበር። ሰውን በሰው ማየት አቅቶኝ ሌላውን የሚገድል የእኔ ጠባቂና ጠበቃ ነው እላለሁ። የእሳት እራት ነኝ፣ አዳምን ከሲኦል ያወጣህ ፣ ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶን ያዳንህ፣ ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ ያተረፍህ፣ ሶስናን ከከሳሾች የታደግህ ለሞት ወዶ ገብ የሆንሁትን ብዙ ጊዜ አዳንከኝ።
አውቃለሁ ብዬ ስጠፋ በድምፅም በጅራፍም ብዙ ዘመን መለስከኝ። በሚያም ሥርዓት አሳልፈህ ሕይወት ስጠኸኝ። ማታውን አስቀድመህ ጠዋቱን ላክልኝ። ሰዎች የደበቁኝን የመንገዱን ምሥጢር ገለጥክልኝ። የአንበሳውን ጋማ ስዳብስ አንተ ግን ጥርሱን ውኃ አደረግህልኝ :: ከገዳዩ መብል እንዲወጣ ሶምሶምነቴን ረዳኸው ። ለቀኑ ደስታዬ ዘላለሜን ስረብሽ አይሆንም አልከኝ። ገዳዩን ስጨብጥ ገላገልከኝ። ከሞት ጋር ቃል ስጋባ አፋታኸኝ። ችሎታዬ ያልሰጠኝን፣ ምርጫዬ የማያስገኝልኝን ቸርነትህ ቸረኝ።
እኔ የእሳት እራት ነኝ። ሁሉም ነገር እኔ ከሄድኩበት ጥሩ የሚሆን፣ ተኩላን በግ የማደርግ ይመስለኛል። እኔ ጥሩ አይደለሁም እያለኝ ከባለቤቱ ይልቅ አውቃለሁ የምል ነኝ። በገደል ላይ በቀጭን ገመድ ካልሄድሁ የምል፣ ለዝና ሕይወቴን መቃብር ላይ የምጥል ነኝ። ሳላይ የምፈርም፣ በስሜት የምከንፍ፣ በምርጫዬ የምደነግጥ፣ አንድ ጊዜ አይቼ አሥር ጊዜ የምቆራርጥ ሰነፍ አናጢ ነኝ። የዋህነት ርቆኝ ጅልነት የተጣበቀኝ ፣ እንደ እኔ አለማስተዋል በወኅኒ ነበርኩኝ። አንተ ግን የመቃብርን ደጃፍ ፊት ለፊቴ ላይ ዘጋኸው። ከአራዊት መንደር፣ ከጅብ ሰርግ ውስጥ በሰላም ወጣሁ ። አንተን ያደከምኩህ የእሳት እራት ነኝ፣ ቀለም የሚማርከኝ፣ ፈገግታ የሚስበኝ፣ ጥርስ የሚሸነግለኝ ሚዛኔ ደካማ የሆንሁ ብኩን ነኝ። እደጅ የማድረውን እቤት አሳደርከኝ ::
እሳት በነደደ ቊጥር ዘሎ የሚገባው የአገሬ ወጣት የእሳት አራት ነው። እሳት ማቃጠሉን አያውቅ ይሆን? ያነደዱት ዳር ቆመው ይሞቃሉ። ለማየት ሲያሳሳ የአገሬ ወጣት ፈጥኖ ይቀጠፋል። በሽታው ብዙ ነው፣ ደስታን ፍለጋ ይሆን ወይንስ ተስፋ መቁረጥ እስኪባል የአገሬ ወጣት እሳት ውስጥ ዘሎ ይገባል። አንዳንዱ ይሞታል፣ ሌላውም እየተሰቃየ ይኖራል። የነደደ እሳት ውስጥ የምገባ ነኝ። ስህተት ለመመለስም ዕድል ላይሰጥ ይችላል። እሳቱ ለብልቦ ብቻ ላይቆም ይችላል። ሌላውን የሚገድል እኔን የሚያፍር እየመሰለኝ ብዙ ዘመን ተሞኝቻለሁ። ያንተ ጥበብ ግን ሲያወጣኝ አይቻለሁ። የእንደገና አምላክ ባትሆን ኖሮ የለሁም ነበር።
የእሳት እራት ውብ ናት፣ ውበትም ይማርካታል። የእሳት እራት ምንም ጎጂነት የላትም፣ በዘመዶችዋ ተናዳፊነት ግን ሁሉም ያባርራታል። ውበታቸውና ቅንነታቸው ያልታወቀላቸው ብዙዎች ናቸው። በአካባቢያቸው ለክተን ፣ አጠገባቸው ካሉት ክፉዎች ጋር ደምረን የገፋናቸው ብዙ ናቸው። የእሳት እራት የምትመለስ እየመሰላት እሳት ውስጥ ዘላ ትገባለች። ሞትን ፈርቶ ወደ ሞት እንዴት ይኬዳል? በተሰበረ ጀልባ እደርሳለሁ ተብሎ እንዴት ይታሰባል? ጭንቀት የእሳት እራት ያደርጋል። የሰው አገር በፊልምና በተግባር የተለያየ ነው:: ብዙዎች እንደ እሳት እራት ውበትን ፣ የተቀባባ ቁንጅናን አይተው ቀሩ። አቤቱ ባለማወቅ የጠፋውን፣ ልቡ የዋህ የሆነውን ትውልድ አድን!
የመጣሁበትን መንገድ ዞር ብዬ ሳየው በጣም አስፈሪ ነው ። ያለፍኩትን ገደል ስሙን ስሰማው አልፌው እንኳ ፈራሁ፡፡ በክህደት ስቀልድ፣ በሰይጣናዊ ግብር ስጫወት አንተ ግን ትጠነቀቅልኝ ነበር። ጤናዬ አንተ ነህ። ይገባሃል ብለህ ጨርቅን በአካሌ ላይ ያስቀረህልኝ አንተ ነህ። በራሴ ጠፋሁ ባንተ ዳንኩ። ዛሬ ግን ተመስገን እልሃለሁ። እንኳን አልሆነ እያልሁ ስለ ተበላሸው ነገር ምስጋና አቀርባለሁ:: ባለፈው ይቅር በለኝ ፣ በሚመጣው ጠብቀኝ ፤ በአማኑኤል ስምህ፣ በፈሰሰው ደምህ፣ በማርያም እናትህ አሜን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 7 ቀን 2017 ዓ.ም.