መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የእግዚአብሔር ቀኝ

የትምህርቱ ርዕስ | የእግዚአብሔር ቀኝ

 ቀኝህ በኃይሉ ከበረ ፣ ቀኝህ ያለ አጋዥ ገነነ ፣ ቀኝህ ጦም አዳሪውን አጠገበ ፣  ቀኝህ የተፍገመገሙትን ደገፈ ፣ ቀኝህ ጥቅመ ሰናዖርን አፈረሰ ፣ ቀኝህ የሰዶምን ምድር ደመሰሰ ፣ ቀኝህ ፈርዖንን አስጥሞ ምስኪኖችን አሻገረ ፣ ቀኝህ ናቡከደነፆርን ሣር አስግጦ ዳንኤልን አተረፈ ፣ ቀኝህ ሥጋ ማርያምን ለበሰ ፣ ቀኝህ በሥጋና ደም ተዛመደን ፣ ቀኝህ በመስቀል ላይ ዋለ ፣ ቀኝህ ሞትን ሰበረ ፣ ቀኝህ ሲኦልን በዘበዘ ፣ ቀኝህ ያመኑትን በእሳት በሰይፍ ውስጥ አሳለፈ ፣ ቀኝህ ይህችን ቀን ፈጠረ ። የእግዚአብሔር ቀኝ ቡሩክ ነህ ። የእግዚአብሔር ክንድ ልዩ ነህ ። ደዌን ነቃዩ ፣ ሞትን አርካሹ የእግዚአብሔር ቀኝ ወዴት ነህ ?
ቂም ሳይለቀኝ ጸሎት ፣ በቀል ይዤ አገልግሎት ፣ እልህ አንቆኝ ስብከት ፣ እየተናደድሁ ምጽዋት ፣ እየገደልሁ መሥዋዕት ፣ እያስለቀስኩ ስብሐት እስከ መቼ ነው ? የእግዚአብሔር ቀኝ ሆይ አስጥለኝ ። ከራሴ ጋር ክርክር እስከ መቼ ነው ? ጽድቅን እያየ ኃጢአትን የረገጠውን ይህን ሥጋዬን ምን ላድርገው ? የምወደውን ትቼ የማልወደውን የማደርግ ጎስቋላ ሰው ነኝ ። ክብሬ ጌታዬ ሆይ ራሴን ከራስህ አስታርቅልኝ ። የጽድቅ መሻቴን መታዘዝ ፣ ስለ ድካሜ ማልቀሴን ሰማዕትነት አድርግልኝ ። ከሰዎች ጋር ክርክር እስከ መቼ ? ፊታቸው ሲጠቁር ሰማይ የጠቆረ  ፣ ሰላምታቸው ሲቀዘቅዝ በመንበርህ የሌለህ ይመስለኛል ። ማመኔ በሰው እንጂ ባንተ አይደለምና የእግዚአብሔር ቀኝ ሆይ ከፍ አድርገኝ ። ከጭቃ ኑሮዬ አውጥተህ በዓለቱ ላይ አቁመኝ ። ሰውን እያየሁ እንዳልኖር እርዳኝ ። የኖርኩላቸው ቀርቶ ያልኖርኩልህ አንተ ግን አዳንከኝ ። ሕሊናዬን ክሰህ በፊትህ አቆምከኝ ። ከሰይጣን ጋር ክርክር እስከ መቼ ? ተከሳሹን ከሳሽ ፣ ተኰናኙን ኰናኝ መፍራቴ ለምንድነው ? እላለሁ ። አንተን ብቻ በማየት ልክበር ።
በሽታን እንጂ ኃጢአትን አልፈራም ። እንደ ባለጌ ልጅ እየተቀጣሁ እሳደባለሁ ። እኔው በድዬ ይቅርታ መጠየቅ እሻለሁ ። የሥጋን ሞት እንጂ የነፍስን ሞት አልፈራም ። የሥጋ ሞት የግድ ፣ የነፍስ ሞት ግን የፈቃድ ነው ። በደሉና ተቀጡ እላለሁ ። የዳር እሳት መሐል እንደሚደርስ ዘንግቻለሁ ። የእግዚአብሔር ቀኝ ሆይ ከከበረ አስተሳሰብ ላይ አውለኝ ።
ቃልህን ከመስማት ጋር መታዘዝን ፣ ድሀን ከመርዳት ጋር መጸለይን ፣ ከፍቅር ጋር ምጽዋትን ፣ ከአገልግሎት ጋር አሥራትን ፣ ከኑሮ ጋር ስብከትን ፣ ከጽድቅ ጋር ክህነትን ፣ ከበረከት ጋር ኑሮን ፣ ካንተ ጋር ሕይወትን ስጠኝ ። ብዙ መናገር ጆሮዬን ደፈነው ፤ ብዙ ማየት ልቤን አደነደነው ። ከውጭ መዓት ይልቅ የልቤ ጥንካሬ ያስፈራኛል ። አንተ ለቅጣት ስታመቻች ልብ እንደ ፈርዖን ይደነድናል ። ጌታዬ ሆይ ሰው ክቡር መሆኑ ጠፍቶኝ ስንት ሞተ እላለሁ ። ሰውን ቍጥር አድርጌ ዜና እናፍቃለሁ ። አንድ ሰው ብዙ መሆኑን ዘንግቼ ማዘን ትቻለሁ ። የዓመት አሳቤን ትቼ የዕለት ነዋሪ ሆኛለሁ ። ዓለምን በአንድ ዓይነት ቋንቋ ስለምታስተምርበት ጥበብህ ምስጋና አቀርባለሁ ። ምኞቴ ከርከም ብሎ እስቲ ልዋል ብያለሁ ። የዘመን ጌልጌላ የምኞት ሸለፈቴን እስከ ወዲያኛው ገርዞ ይጣለው ። የዓለምን ከንቱነት እንዲህ በመስክ ላይ ስላስተማርከን ተመስገን ። የክፍሉ ትምህርት አልገባ ብሎን ይኸው ቤተ ክርስቲያንም ተዘጋ ። ተምረን በጽድቅ ይከፈትልን ። አሜን ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይሁን ። ከልባችን እስከ አርያም ። ከዛሬ እስከ ዘላለም ድረስ አሜን ።
የነግህ ምስጋና 20
መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም