የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእግዚአብሔር ባሪያ/2

ፓፒረስ እየተባለ የሚጠራ በዓባይ ወንዝ ዳርቻ በሚበቅለው የሸምበቆ ተክል የሚሠራ ጥንታዊ የመጻፊያ ወረቀት ነው ። ሙሴ አምስቱን ብሔረ ኦሪት የጻፈው በዚህ ጥንታዊ መጻፊያ ፓፒረስና በብራና እንደሆነ ይታመናል ። ይህ የሸምበቆ ተክል ሙሴ ወደ ዓባይ ወንዝ በደንገል ተደርጎ በተጣለ ጊዜ ደግፎ የያዘው ፣ እንዳይርቅ የከለለው ፣ ነፋስ እንዳይወስደው የጠበቀው ፣ እንዳይታይ የሸፈነው ነው ። የዓባይ ወንዝ ምንጩ ኢትዮጵያ ነው ፣ ወንዙ ያፈራው ሸምበቆ ፓፒረስን ሲያስገኝ ሙሴ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ጻፈበት ። ዓባይ የሚነሣበት ምንጩ ኢትዮጵያ ናትና ሙሴ ኢትዮጵያይቱን ሴት አገባ ። ኢትዮጵያና ሙሴ የሚተዋወቁት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1600 ዓመት ቀደም ብሎ ነው ። ሙሴ ኢትዮጵያይቱንም አገባ ። ያ ወንዝ የተጣለው ሕፃን ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ ሕዝቡን ያሻግር ዘንድ እግዚአብሔር ጠራው ። ሙሴን ለእስራኤል ታዳጊነት ያዘጋጁ ሁለት ሴቶች ሊረሱ አይገባም ። ሦስተኛይቱ ሴትም የፈርዖን ልጅ የሆነችም ልዕልት ናት ። ልትደነቅ ይገባታል ። አባቷ ሰው ያንቃል ፣ እርሷ ደግሞ ሕፃን ታሳድጋለች ። ሰው በአባቱ መመዘን የለበትም ። ቤተሰቦች በሥጋ ቅርብ ቢሆኑም በአሳብ ግን ልዩ ናቸው ። የአባትን ዕዳ ልጅ መሸከም በክርስቶስ የተሰረዘ ነው ።

የዓባይ ወንዝ ዳር ያለው የሸምበቆ ተክል እንደ ደግ ሰው አግዟታል ። ነፋስ ደንገሉን ሊወስደው ሲል ይይዝላታል ። እስከ አንገቷ ወደ ወንዙ ጠልቃ ደንገሉንና ሕፃኑን ለሸምበቆው አደራ ብላ ትወጣለች ። ሕፃኑ በውኃው ዥዋዥዌ ቢጫወትም ያች ሴት ግን በምጥ ትውል ነበር ። ሸምበቆ ድጋፍ ፣ ባሕር መሠረት የሆነውን ያንን ደንገል በሩቅ በዓይኖቿ የምትጠብቀው አንዲት ሴት ነበረች ። ሰጎን እንቁላሏን ያለ ማቋረጥ ካላየች እንቁላሉ ይበሰብሳል የሚል አስተሳሰብ አለ ። ያንን ደንገል ያለ ማቋረጥ ካላየች ያ ደንገል ሊርቅ ፣ ውኃ አስገብቶ ሊሰጥም ይችላል ፤ ባለ ራእዩም ሊሰጥም ይችላል ። ባለ ራእዩን እንዲህ የምትንከባከበው ያች ሴት ልትደነቅ ይገባታል ። ከሚታዩ ሰዎች ጀርባ የማይታዩ ሰዎች አሉ ። ይህች ሴት እናት አይደለችም ፣ የእናት አንጀት ግን ተሰጥቷታል ። እናት ሁነው እንደ እህት የሚያስቡ ፣ እህት ሁነው እንደ እናት የሚያስቡ አሉ ። አባትነት ከሚሰየምበት የአብ ዙፋን እናትነትም ይሰየማል ። ያልወለዱም የእናት አንጀት አላቸው ። እናትነትን ዋጋ የሰጠው ምጡ ብቻ አይደለም ፍቅሩም ነው ። በአካል የሚያምጡ ከምጥ በኋላ ይታደሳሉ ። በአሳብ የሚያምጡ ግን ከአሳብ በኋላ ይዳከማሉ ። ከአንድ አሳብ ኩንታል ተሸክሞ መዋል ይቀላል ። የአሳብ ጭነት ላግዝህ የማይባል ፣ መሸከሙን የተሸከመው ብቻ የሚያውቀው ነው ። ይህች የእናትነት አንጀት የነበራት ሴት የንጉሥን አዋጅ ሽራ ሕፃኑን ወንድሟን ትጠብቃለች ። እናቱ ለምን አትጠብቅም ቢባል የሦስት ወር አራስ ናት ። እንዳትጎዳባት በማለት ነው ። ወዲህ የእናት ውለታን ትከፍላለች ፣ ወዲህ ለወንድሟ ውለታ ታቆያለች ። ሕይወት ለማዳን ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላ ነበር ። ቆይታ ግን ትጠብቅ የነበረው አንድ ሚሊየን እስራኤልን እንደሆነ ተረድታለች ። ከባለ ራእዩ ጀርባ ባለ ራእዩን የጠበቁ ሰዎች አሉ ። ጾታቸው የተናቀ ፣ አቅማቸው የደከመ ፣ ከእልፍኝ የማይወጡ ይሆናሉ ፤ ኃያላንን ግን የሚያሰናዱ እነዚህ ናቸው ። አመድ ሁነው እሳት ያደረጉንን ልናመሰግን ይገባናል ። የእሳት ልጆችም አመድ በመሆናቸው ልናዝን ይገባናል ።

ሁኔታው እስራኤል ከረሀብ ሸሽተው ሰባ ነፍስ ሁነው ወደ ግብጽ የወረዱበት ነው ። ነገር ግን “ከእባብ ጉድጓድ አምልጦ ዘንዶ ጉድጓድ” የሚባለው አባባል የተፈጸመበት ነው ። ሞት ሸሽተው ወደ ሞት እየሄዱ ነበረ ። ተስፋ አድርገው የወጡት ገደልነው ያሉትን ዮሴፍን ነው ። ሟቹ ሕይወት ሰጪ ሆነ ። ዮሴፍ ሞቱ በከነዓን ሲነገር በግብጽ ግን ነግሦአል ። ክርስቶስም አይሁድ ገደልነው ብለው ሲደሰቱ በሰማይ የድል ነሺነቱን ምሥጋና እየተቀበለ ነው ። በዚያው በከነዓን የዮሴፍ ወንድሞች ገዳይ ሁነው አባቱ ደግሞ አልቃሽ ሁኖ ተቀምጠዋል ። በዚያው በኢየሩሳሌም የክርስቶስ ሰቃዮችና የክርስቶስ ወዳጆች ሐዋርያት ነበሩ ። ገደልነው ባሉትና በሸጡት በዮሴፍ ከረሀብ እንደ ዳኑ ዛሬም በሠላሳ ብር በተሸጠው ክርስቶስና በሰቀሉት ጌታ እስራኤል ከመላው ዓለም በሚመጣ ጎብኚ እንጀራ ትበላለች ። ክርስቶስ ለሚጠሉትም እንጀራ ነውና ።

ዮሴፍ ጠዋቱ መከራ ነበረበትና ማታው አምሮለት በሰላም ተሸኘ ። ጠዋቱን በክፋት የተጓደዱ ወንድሞቹ ግን ማታው አላማረላቸውም ። በአባታቸውና በወንድማቸው በረከትና ጸሎት ኖሩ ። አባታቸውና ወንድማቸው እልፍ ሲሉ መዓቱ ያለ ከልካይ መፍሰስ ጀመረ ። በበደላችን ልክ መዓቱ እንዳይፈስ የሚከለክለው የቅዱሳን ጸሎት ነው ። እግዚአብሔር ቅዱሳኑ ልባቸው እንዳይሰበር ያጠፉትን ኀጥአን ያልፋል ። የቅዱሳን ጸሎት መዓት ከልካይ ነው ። እኛ ከተማ እየዘለልን በድንግልና በምንኩስና ጠፈር ታጥቀው በየገዳማቱ የተቀመጡት ለአንድ ነፍሳቸው ብቻ አይደለም ። የጸሎት ዘብ ለመሆንና ወገናቸውን ለማትረፍ ነው ።

ዮሴፍን የማያውቅ ንጉሥ ተነሣ ። የእስራኤልን መብዛት ለመቆጣጠር ንድፍ አወጣ ። ነገ ሕዝቡ እየበዛ ሲመጣ አልገዛም ሊልና ከጠላት ጋር ሁኖ ሊቆጣጠረን ይችላል ብሎ ሰጋ ። ጠላት ለቀጣይ ሃያና ሠላሳ ዓመታት አንዳንዴም መቶ ዓመታት ያቅዳል እኛ ግን የአምስት ዓመት ዕቅድ እንኳ የለንም ። ሄሮድስ የተወለደውን ሕፃን ሊገድል የፈለገው ከሃያ ዓመት በኋላ ዙፋኔን ይነጥቀኛል ብሎ ነው ። ሄሮድስ ግን የቀረው ዕድሜ ሦስት ዓመት ነበረ ። ለካ የምንገድለው ብዙ የምንኖር እየመሰለን ነው ። ፈርዖንም ሕዝቡን በባርነት ግብር ያዘ ። አዲስ የሚወለዱ ወንዶች ግን ከማኅፀን ደጃፍ ላይ እየታነቁ እንዲገደሉ ብሎ አዋጅ አወጀ ። በፈርዖን ዱላ እስራኤል ግብጽ መኖሪያቸው እንዳልሆነች ተገነዘቡ ። እግዚአብሔር ምቾትን በመንሣት የእኛ ካልሆነው ሰፈር ያስወጣናል ። ሁለተኛ በሰማይ ያለውን የቃል ኪዳን አምላክ አስታወሱ ። ክፉዎች ደጉን አምላክ እንድንጠራው ያደርጉናል ።

ለግብጽ አዋላጆች ትእዛዝ ተሰጠ ። ወንድ ሲወለድ ወዲያው አንቀው እንዲገድሉት ፣ ሴት ከሆነች ግን ውኃ ለመቅዳት ፣ እንጨት ለመስበር እንድትተርፍ ጥብቅ መመሪያ በቀጥታ በንጉሡ ተላለፈላቸው ። ንጉሡ ወርዶ የሚወለዱ ሕፃናት ላይ ጦርነት ከፈተ ። ፈርዖን ማለት ይላሉ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፡- “ግፈኛ ፤ ግፍ ሠሪ ፤ ሙት አስገባሪ ማለት ነው ። ላንድ ሰው መቃብር 200 ብር ይቀበል ነበረ ይባላል” ብለዋል ። /መጽሐፈ ሰዋስዉ ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ፤ ገጽ 733 ።/ እኛ ሰማንያ ሺህ ብር የደረሰው የመቃብር ሽያጫችን ምን ያሰኘን ይሆን  ዛሬም ሙት አስገባሪ ፈርዖን ነን ። የእስራኤል ልጆች በሥራ ጫናና በልጆቻቸው ኀዘን ተሰበሩ ። ያ ዘመን መሐን እልል ትበል የተባለበት ዘመን ነበር ። መሐንም ግን በጎረቤት ልጅ ታዝናለች ። ያሳደገችው ነውና ። እንደውም ብዙዎች መሐን የሚሆኑት በጣም ሩኅሩኅ ስለሆኑና ለልጅ ስለሚሳሱ ራሳቸውንም ልጁን አስጨንቀው ከጤና ዓለም እንዳይወጡ ነው ። እጅግም ርኅራኄ እስር ቤት ነውና ።

ንጉሡ ያዘዛቸው የዕብራውያን አዋላጆች ሲፓራና ፉሐ ግን እግዚአብሔርን ፈሩ ። ብዙ ወንዶች ሕፃናትን አዳኑአቸው ። ዛሬም የሚወለዱ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ሞት ግን ታውጆባቸዋል ። የሚታደጉ አዋላጆች ፣ የንጉሥን ቍጣ የማይፈሩ ጎበዞች ይኖሩ ይሆን  በአገራችን ልደት እንጂ ዕድገት አይታይም ። የሚወለዱ ነገሮች በነገሥታት ቅናት ወዲያው ታንቀው ይገደላሉ ። ስለዚህ አገራችን ሁልጊዜ በጅምር ናት ። ያለቀ ነገር እስቲ ጥሩ ብንባል መጥራት የሚያቅተን ይመስላል ። መጽሐፍም ልጅ ነው ። ጽንሰት ፣ እርግዝና ፣ ምጥና ልደት አለው ። ትልቁን መዝገበ ቃላት ለማሰናዳት ያሰቡት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በትንሹ መጽሐፋቸው “መዝገበ ፊደላት ሴማውያት” ላይ እንዲህ ብለዋል፡-

ይህን ጨቅላ መጽሐፍ የምታዩ ኹሉ ፣
ዐደራ ስለኔ ማሪያም ማሪያም በሉ ፤
በሆዴ ያለውን የትምርት ሽል ፣
አለጭንቅ እንድወልድ እንድገላገል ፤
ከኻያ ስድስቱ ወንዶች ፊደላት ፣
አርግዣለሁና መዝገበ ቃላት ።

መጽሐፍ እርግዝና ነውና አዋላጆች ያስፈልጉታል ። በርታ ፣ ግፋ ፣ ደርሷል ፣ ትንሽ ነው የቀረው እያሉ የሚያግዙ ያስፈልጉታል ። ሕፃኑን የወለደቸው ሳትሆን ያዋለዱት መጀመሪያ እንደሚያዩትና እንደሚያነሡት መጽሐፍም በረከቱ መጀመሪያ ለአንባብያን ነው ። እንደ ፈርዖን ጨቅላ ደራስያንን ፣ ለማነቅ የሳንሱር ሕግ ያወጡ ፣ አሳብ እንዲጨቆን የወረቀት ታክስ የጨመሩ ነገሥታት በዘመናችን አይተናል ። እግዚአብሔርን የሚፈሩ አዋላጆች በርታና ጻፍ ሲሉ ነገሥታት ደግሞ እንዳይታተም በመከልከላቸው የገዛ መጻሕፍቶቻቸውን በኀዘን ያቃጠሉ ምሁራንን ተመልክተናል ። ያ ዘመን አልፎ ያውም በቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ሲቃጠሉ አይተናል ። አንድ ሰው እንዳለው፡- “መጻሕፍት ሲቃጠሉ ቀጥሎ ሰው ይቃጠላል” የተባለው ደርሶ ብዙ ሰው ሲቃጠል ፣ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ አየን ። ብቅ የሚሉትን ማነቅ ፣ ፈርዖናዊው አዋጅ ዛሬም አለ ። አዋላጆች ግን እግዚአብሔርን ከፈሩ ፣ ምእመናን በርቱ ብለው ካበረታቱ ብዙ የመጻሕፍት ልጆች ይወለዳሉ ።

ይቀጥላል

የእግዚአብሔር ባሪያ/2
ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን መኰንን

https://t.me/Nolawii

እባክዎ ይህን ቻናል ይቀላቀሉ፣  ለሌሎች ወገኖቻችንም ያስተዋውቁ

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ