የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእግዚአብሔር ዓላማ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ ኅዳር 6/2006 ዓ.ም.
ዓላማ ራሳችንን የምናይበት፣ እግዚአብሔር እኛን የሚያይበት መድረሻ ነው፡፡ በዚህች ሕይወታችን ላይ አራት ወገኖች ዓላማ አላቸው፡-
1.   እግዚአብሔር
2.  ራሳችን
3.  የሚወዱን
4.  ሰይጣን
1.  እግዚአብሔር
 
እግዚአብሔር መነሻችንና መድረሻችን ነው፡፡ ዓላማ መነሻን የሚያሳውቅ፣ መኖርን ምክንያታዊ የሚያደርግ፣ ፍጻሜን የሚለካ ነው፡፡ የሰው ልጅ ኑሮውንና ፍጻሜውን ለመወሰን መነሻውን ማወቅ አለበት፡፡ መነሻውን ያላወቀ መድረሻውም ይጠፋዋል፡፡ “የመጣህበትን አትርሳ፣ የምትሄድበት እንዳይጠፋህ” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የሰው ልጅ መነሻ እግዚአብሔር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ የተካተተች ሕይወት ተቀብለናል፡፡ የተፈጠርንበት ዓላማና የምንኖርበት ዓላማ ፍጹም አንድነት አለው፡፡ የምንኖረው ለተፈጠርንበት ዓላማ ነው፡፡ በመፈጠራችን ላይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ባለ ዓላማው እግዚአብሔር ነው፡፡ የአንድ ሥሪት ዓላማ ያለው ሥራው ውስጥ ሳይሆን የሠሪው ልብ ውስጥ ነው፡፡ እኛም ፍጡር መሆናችንን ካመንን የእኛ ዓላማ ያለው እኛ ጋ ሳይሆን የሠራን ጌታ ጋ ነው፡፡ ስለዚህ ዓላማ የምንለው አይደለም ዓላማችን፡፡ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ዓላማ እርሱ ዓላማችን ነው፡፡ ዓላማ ኑሮን ይመራል፡፡ ፍጻሜን ያሳውቃል፡፡ ዓላማ ደስታ ይሰጣል፣ እግርን ተራማጅ ያደርጋል፡፡ ዓላማውን ያገኘ ሰው የመንገዱን ካርታ የጨበጠ በመሆኑ ያለ እንግልት በጊዜው ይደርሳል፡፡ 
2. ራሳችን
 
የአንድ ትልቅ መጽሐፍ አርእስትን አስቡ፡፡ ከመጽሐፉ የምዕራፍ ክፍሎች በአንዱ ውስጥ ያለውን ንዑስ ርእስ ደግሞ ለማሰብ ሞክሩ፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ የሕይወት ርእስ ነው፡፡ የሕይወት ራስ የሚለውን ቃል የሕይወት ርእስ ማለት እንችላለን፡፡ በትልቁ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የእኛ ዓላማ ንዑስ ርእስ ነው፡፡ ሕይወትን በአንድ ትልቅ መጽሐፍ መመሰል መልካም ነው፡፡ ደራሲው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ በዚህ ዓለም የምናሳልፈው 70 ና 80 ዓመት አንድ አንቀጽ የማይሞላ ወይም ከመቅድም የማይዘል ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓለም ኑሮአችን የዓይን ጥቅሻ፣ የእሳት ብልጭታ የሚያህል ነው፡፡ ሰፊው ኑሮአችን ያለው በሰማይ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው ከተባለ ሰባና ሰማንያ ዓመት በእግዚአብሔር ዘንድ የ2 ሰዓት 30 ቆይታ ነው፡፡ በርግጥ በዚህ ዓለም ላይ የምናሳልፈው ቆይታ በጣም አጭር ነው፡፡ ዘላለማዊ ሕይወታችን ላይ ባለ ዓላማ የሆነው እግዚአብሔር ይህችን ትንሽ ቆይታ መምራት የሚሳነው አይደለም፡፡ 
የተለያዩ ዓላማዎች ሊኖሩን ይችላሉ፡፡ ገንዘብ መጨበጥ፣ ሥልጣን ላይ መቆናጠጥ፣ ትዳር መመሥረት፣ ልጆች መውለድ … ዓላማችን ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን ንዑሳን ዓላማዎች ናቸው፡፡ ዋነኛ የተፈጠርንበት ዓላማ ግን አባቶች እንደ ነገሩን ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ነው፡፡ ይህ በአጭር ቃል የተነገረው ትልቅ ፍቺ ያለው ነው፡፡ በዚህ ዓለም ስሙን እንቀድሳለን፣ እግዚአብሔርን የሚያስከብር ኑሮ እንኖራለን፡፡ በወዲያኛው ዓለም ደግሞ ክብሩን እንወርሳለን፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ገንዘብ የወረሱ ደስ ሊላቸው፣ ዕድለኞች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ክብር ግን የሚወረሰው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስሙን ለሚቀድሱ ክብሩን ያወርሳቸዋል፡፡

3. የሚወዱን
 
እኛ በራሳችን ላይ ዓላማ ይኖረናል፡፡ የሚወዱንም በእኛ ላይ ዓላማ አላቸው፡፡ ከሁሉ የሚልቀው ግን እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ዓላማ ነው፡፡ እኛ ይህችን ሕይወት በአደራ ተቀብለናታል እንጂ በባለቤትነት የያዝናት አይደለችም፡፡ ባለቤቱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለገዛ ሰውነታችን የሚጠይቀን ሰውነታችንን በአደራ ስለ ሰጠን ነው፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ነን፡፡ እኛ የራሳችን አለመሆናችንን ብናውቅ ኖሮ በራሳችን ላይ ለማዘዝ አንፈቅድም ነበር፤ ሰዎችም እንዲያዙበት ክፍት አናደርገውም ነበር፡፡ በእኛ ላይ ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከራሳችን ይልቅ ለራሳችን የሚቀርበው አምላክ ነው፡፡ 
የሚወዱን እንድንሆንላቸው የሚፈልጉት ነገር አለ፡፡ ይህ በእኛ ላይ ያላቸው የወዳጆቻችን ዓላማ ነው፡፡ ነገር ግን ቀድሞ የሚያውቀን እግዚአብሔር በእኛ ላይ ዓላማ አለው፡፡ በራሳችን ላይ ባለ ዓላማ የሆነው ምናልባት ራሳችንን ካወቅንበት ጊዜ ጀምሮ አሊያም ለአካለ መጠን ስንደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ ዓላማ የምንለውም ነገር ዓላማነቱ በጣም መፈተሽ ያለበት መሆኑን አንረሳም፡፡ የሚወዱንም በእኛ ላይ ዓላማ አላቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ወላጆቻችን በእኛ ላይ ዓላማ አላቸው፡፡ ገና በማኅፀን ሳለን፣ ወይም ተወልደን ባዩን ጊዜ አሊያም ብልህነታችን የማረካቸው ወቅት ሊሆን ይችላል፡፡ እነርሱ ዓላማ ያደረጉት ደም መላሽ እንድንሆን፣ ከድህነት እንድናወጣቸው፣ ስማቸውን እንድናስጠራ፣ ዘመድ እንድንሆናቸው፣ እንድናኰራቸው ሊሆን ይችላል፡፡ በእግዚአብሔር ሚዛን ግን ይህ ሁሉ ዓላማ አይደለም፡፡ ዓላማችንን በእግዚአብሔር ዓላማ ውስጥ ካላገኘነው እውነተኛ አይደለም፣ ዓላማ ተብሎም አይጠራም፡፡ 
እኛ በራሳችን ላይ ዓላማ አለኝ ካልንበት ዘመን የወላጆቻችን ዓላማ ይቀድማል፡፡ ከወላጆቻችን ደግሞ የእግዚአብሔር ዓላማ ቀዳሚ ነው፡፡ ወላጆቻችን ዓላማቸው የጀመረው ገና በማኅፀን ሳለን ቢሆን እንኳ እግዚአብሔር ግን ዓላማ ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር፣ ከጊዜና ከቦታ በፊት በእኛ ላይ ዓላማ ነበረው፡፡ ዓለም ሳይፈጠር በዓላማ አየን፣ በመፍጠር ገለጠን፣ ትእዛዝ በመስጠት መራን፡፡ 
4. ሰይጣን
 
ሰይጣን በራሳችን፣ በወላጆቻችን ዓላማ ውስጥ የራሱን ዓላማ ያሳርፋል፡፡ የሰይጣን ዋነኛ ዓላማው የእርሱን ዓላማ ተግባራዊ እንድናደርግ ሳይሆን ለራሳችንም ሆነ ለሚወዱን ሰዎች ዓላማ ስንኖር ከእግዚአብሔር ዓላማ እንድንፈናቀል ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ዓላማ በሙሉነት አለመፈጸም ለሰይጣን ትልቅ እርካታና መግቢያ ነው፡፡ የሰይጣን ዋነኛ ዓላማው ባለጠጋ እንዳንሆን፣ ዝናን እንድናጣ አይደለም፡፡ እንደውም እነዚህን ነገሮች ሰይጣን ሊሰጠን የሚፈልጋቸው ነገሮች ናቸው፡፡ የሰይጣን ዋነኛ ዓላማ ለገንዘብ፣ ለትዳር ስንባዝን ዘመናችን በቶሎ አልቆ ለዘላለም የእርሱ እንድንሆን ነው፡፡ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ጋር የሚፎካከር በመሆኑ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ እንዳለው እርሱም ዘላለማዊ የክፋት ዕቅድ አለው፡፡ 
የእግዚአብሔር ዓላማ
 
የእግዚአብሔር ዓላማ ቅዱስ፣ ከፍ ያለ፣ ፍጻሜው ያማረ፣ ገዢ፣ ፀንቶ የሚኖር፣ የእኛን ዓላማ የሚጠቀልል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ በሕይወታችን ተግባራዊ ሲሆን ከኃጢአት እንርቃለን፣ ከፍ ባለ የሞራል ደረጃ እንራመዳለን፣ ፍጻሜአችን ያማረ ይሆናል፡፡ ዓላማችንን ዓላማው፣ ፈቃዳችንን ፈቃዱ እንዲገዛ ከሁሉ በላይ፡- ጌታዬ ሆይ በእኔ ላይ ያለህ ዓላማ ይፈጸም፣ ሁን እንዳልከኝ ኖሮ ማለፍ ይሁንልኝ ብለን መጸለይ ያስፈልገናል፡፡ የእኛ ዓላማ ባይፈጸም በእግዚአብሔር ዓላማ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ደግሞም ፍጡር መሆናችንን እንገነዘባለን፡፡ እንኳን እኛ የነገሡ ሰዎችም ተመኝተው ያልሆነላቸው ብዙ ነገር አለ፡፡ ሰው ማለት አቅሙ የተወሰነ ፍጡር ማለት ነው፡፡ 
እስከዚህች ቀን የደረስነው እንዲሁ አይደለም፡፡ በብዙ ትግልና ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈን ነው፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ሁሉ ከፍታና ዝቅታ ውስጥ አልተለየንም፡፡ ስንታመም ፈውሶናል፣ ስንራብ መግቦናል፣ ስንገፋ ደግፎናል፣ ስንረሳ አስታውሶናል ….፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ የደከመብን ሊጥለን አይደለም፡፡ የሚጥለውን ዋጋ የሚከፍልበት ማንም የለም፡፡ እኛም ለማንፈልገው ነገር ዋጋ አንከፍልም፡፡ እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር በእኛ ላይ ዓላማ አለው፡፡ ያየነውን ሳይሆን ያየልንን ለመውረስ ፈቃደኛ መሆን አለብን፡፡ 
የእግዚአብሔር ዓላማ በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ ደስተኛ ኑሮ እንድንኖር፡-
1.   ዓላማ ያለው ሕይወት እንደሚያስፈልገን ማመን
2.  ከእኛ ከወዳጆቻችንም ይልቅ የእግዚአብሔር ዓላማ ክቡር መሆኑን መረዳት
3.  እግዚአብሔርን በማስከተል የኖርንበትን ኑሮ ትተን እርሱን በማስቀደም መመላለስ
4.  በጸሎት ምሪቱን መጠየቅ ይገባናል፡፡  
                                                ምስጋና ለታላቅ ስሙ ይሁን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ