መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -1

የትምህርቱ ርዕስ | የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -1

የዘላለም አምላክ

የዘመን መወጠሪያ በእጁ ያለ ፣ ለህልውናው ጀመረ ፈጸመ ተብሎ የማይነገርለት ፣ ከጊዜ ውጭ ከዘመን ባሻገር የሚኖር ፣ ለመኖሩ በማንም የማይደገፍ ፣ ትላንት በአባቶቻችን ዘመን ፣ ነገ በልጆቻችን ዘመን የሚኖር ፣ ሺህ ዓመት በፊቱ እንደ አንድ ቀን የሆነ ፣ አባቶቻችንን የምናገኝበት ታሪክን የመራ ፣ ነገን የምናይበት የእውቀት መነጽር ፣ ሳንፈጠር የሚያውቀን ፣ ዓለምን ለቀን ስንሄድ አደራችንን የሚወጣ እርሱ እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ ይባላል ። ብዙ አማልክት የተባሉ ፣ የግሪክ አፈ ታሪክ የተሰየመላቸው ፣ ብዙ ጉልበትን ያንበረከኩ ርኵሳን ጣዖታት ዛሬ የሉም ፣ በሮም ተቀምጠው ራሳቸውን ያስመልኩ የነበሩ ቄሣሮች በእብደት ተቀጥተዋል ፣ አምላክነት ሲያምራቸው ሰው መሆን አቅቷቸው ተጠናቀዋል ። እግዚአብሔር ግን የዘላለም አምላክ ነው ። የማያልፍ ፣ ወረት የሌለበት ፣ የድሆች አባት ፣ የምስኪኖች ልብስ ነው ።

የዘመናት አምላክ

ዓለምን የፈጠረ ፣ ዘመንን የቆጠረ ፣ ከእርሱ በቀር ማንም የሌለ ፣ ሁሉን በዘመን የገደበ ፣ ለንጉሥም አንድ ቀንን የሚጨምር ፣ ታላቅነቱ እጅግ የሆነ ፣ ዕድሜ ሳይቸግረው ለኗሪ የሚናኝ ፣ ዘመን የሌለው ባለ ዘመን ፣ እኩያ የሌለው ሁሉን አክባሪ ፣ ምንጩ ቡሩክ የሆነ ፣ ትውልድን የሚያፈራርቅ ፣ ትዕቢተኞችን የሚያስታግሥ ፣ ፍጥረትን ለከንቱነት ፣ ሰውን ለመካሰስ ያልፈጠረ ፣ እመጣለሁ ብሎ ፍጥረትን በተስፋ ያስገዛ ፣ እንኳን የሰው የግዑዛኑና የእንስሳቱ ተስፋ ፣ ተናግሮ ቃሉን የፈጸመ ፣ ጉዳይ ገጠመኝ ብሎ ቀጥሮ ያልቀረ ፣ መጨረሻው ላይ ቆሞ መጀመሪያውን የሚናገር እርሱ የዘመናት አምላክ ይባላል ። እንደ እርሱ ያረጀ ፣ እንደ እርሱ አዲስ የሆነ ማንም የለም ። ብሉየ መዋዕል/በዘመናት የሸመገለ ፣ የዚህ ሁሉ መልከ መልካም ሥነ ፍጥረት ባለቤት የሆነ የዘመናት አምላክ ይባላል ። ዘመን ላስፈራው ፣ ነገ ምን ይሆናል ( የሚል ጭንቀት ላጠቃው የዘመናት አምላክ አለ ። ትላንትን ሊክስ ፣ ነገን ሊቀድስ ይችላል ። የነገሥታትን ፊርማ በፊርማው አዋጅን በአዋጅ ይሽራል ። የሞትን ደብዳቤ ቀይሮ የሹመት ያደርገዋል ። ሊገደሉ የተፈረደባቸውን በነጻ አሰናብቶ ገዳዮችን ሟች ያደርጋል ። ሳይመሽበት ምሽትን ለትዕቢተኞች የሚከፍል እርሱ የዘመናት አምላክ ይባላል ።

ይቀጥላል

ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ